አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ወታደሮች ትልካለች ?

” ከዚህ ክፉ ሀሳብ ቢታቀቡ ይሻላቸዋል ” – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ከሰሞኑን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የጆ ባይደን አድተዳደር በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ ጋር በተያየ ወደ ኢትዮጵያ ወታደሮችን ሊልክ ነው ፤ ወታደሮችን ሊያስገባ ነው የሚሉ የተለያዩ መረጃ ሲናፈሱ ነበር።

በዚህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አስተያየት የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፥ አሜሪካ ወታደር ታስገባለች ለሚባለው ጉዳይ ለምን ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የለውም ብለዋል።

አምባሳደሩ ፥ ” በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ ጫና ለማሳረፍ ፣ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያሳስባቸው ምንም ነገር የለም፤ የአሜሪካን ጥቅም ህዝብም የሀገርን ጥቅም የሚጠብቅ አይደለም። ሁለቱንም ሀገሮች ግንኙነት ቁመናን የሚለካም አይደለም። እብደት ካልሆነ በስተቀር ” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለው ” ህዝባችን እያለ ያለው የኛ ጉዳይ ፣ የኛ ህልውና ፣ የኛ ነፃነት ሁሉ ነገር በእጃችን ነው ያለው እንጂ በእነሱ እጅ አይደለም ያለው ፣ በሌሎች እጅ አይደለም ያለው፤ በማንም እጅ ሊሆን አይችልም። ይህንን ህዝቡ በአንድ ትልቅ ድምፅ እየተናገረ ነው ” ብለዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሰላሙን ጉዳይ በተመለከተም ፥ “ይሄ ሀገር ተጭኖበት ካልሆነ በስተቀር ለሰላም ሁል ጊዜ የቆመ ህዝብ እና መንግስት ነው ፤ መንግስት ለሰላም ከአንዴም ሁለቴ እርምጃዎችን የወሰደበት ሁኔታ ነው ያለው። መጥተው እዚህ ስለ ሰላም የሚያወሩትም ሰዎች ስለሰላም ምንም አዲስ ነገር እየነገሩን አይደለም ይሄ የህዝባችን ፍላጎት ነው እሱ። ህዝባችን ለምንድነው የሚጭኑብን እያለ ነው፤ ግን ከህልውናችን በላይ ምንም ነገር የለም የሚል ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና ፤ [ አሜሪካኖቹ ወደ ኢትዮጵያ ወታደር የማስገባት ] እርምጃ ባይገቡበት ይሻላል ያሉ ሲሆን እነሱ ገብተው ሰላም የፈጠሩበት ሀገር ብዙም የለም ብለዋል።

” እዚህ በአካባቢያችን ሊቢያን፣ የመንን ፣ ሶሪያን ፣ ኢራቅን ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ራቅ ያሉ የኤዥያ ሌሎች ሀገራትን አይተናልና የሚፈጥሩት ነገር የለም። ይልቁን የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነትና የቆየ ግንኙነት ማበላሸት ነው የሚሆነው ይሄን መላልሰው ቢያስቡበት እና ከዚህ ክፉ ሀሳብ ቢታቀቡ ይሻላል ” ብለዋል አምባሳደሩ።

@tikvahethiopia

Leave a Reply