አሜሪካ ይፋ ያደረገችው የሽብር ዝርዝር ዕቅድ ተቃውሞ አስነሳ “አዲስ አበባ ተሽብር ጥቃት ቢደርስ ተጠያቂዋ ራስዋ ናት”

አሜሪካ አሸባሪዎች ያለቻቸውን በስም ሳትጠራ የጥፋት ዕቅድ ዝርዝር ይፋ ከማድረጓ በፊት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደርና ሕዝብ በጭንቀት መንግስት ላይ እንዲነሳ ለማስቻል በርካታ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይፋ ሲደረግ ሰንብቷል። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ የታሰበው ሂሳብ እንደከሸፈ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ኤምባሲው ይህንን ዝርዝር ዕቅድ ለምን አወጣ? እነማን ይከተሉታል? ቀጣዩ ድራማስ ምንድን ነው? “በዚህ ደረጃ ፍርሃቻ ካለ ለምን አገር ለቀው አስቀድመው አይወጡም?” የሚሉት ጉዳዮች መነጋገሪያ ሆነዋል። “ይህን የእቅድ ዝርዝር ማወቃቸው በራሱም ጠርጥር” የሚያሰኝ እንደሆነ እየተጠቆመ ነው። ሳማንታን ፓወር ” ሃይላችንን እናሳያለን” ማለታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ግንባር ማምራታቸው የፈጠራውን ታላቅ መነሳሳት ተከትሎ አሜሪካ ይፋ ያደረገችው የሽብር ዝርዝር ዕቅድ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የመንግስት የጸጥታ ሃያላት መረጃ በማግኘት ሰርጎ ገቦችንና መሳሪያዎችን፣ የጸጥታ ሰራተኞችን መለያ ልብስና የተደራጀ የሽብር መረብ ሲያከሽፉ ” የጅምላ እስር ተፈጸመ” በሚል ዘርን መሰረት ያደረገ ጥያቅት እየተፈጸመ እንደሆነ በመጥቀስ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት እነሱ መሆናቸውን ያነሱ ” አዲስ አበባ ላይ የሽብር ጥቃት ከተፈጸመ በማን እንደተፈጸመ የሚታወቅ በመሆኑ ሕዝብ በቁጣ እንዳይነሳ እንሰጋለን” ሲሉ የከተማ ውስጥ ግጭት እንዳይነሳ እያሳሰቡ ነው። ይህን የሰሙ በሌላ በኩል “ሕዝብ በያለበት የአገሩ ወታደር ከመሆን በዘለለ ዘርና ጎሳ የለየ የጠላት ፖለቲካ ቁማር ውስጥ መግባት አይገባም” በሚል ሃሳቡ የሚመከን ተራ ማስፈራሪያ መሆኑንን እየተናገሩ ነው።

የጦር ግንባር ዜና ሲቀየርና በሁሉም አቅጣጫ መከላከያ እየገፋ መሆኑ በሚነገርበት፣ ላሊበላና ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች ነጻ መውጣታቸው በሚሰማበት በአሁኑ ወቅት፣ አዲስ አበባ የተቀመጠው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ጠቅሶ ያሰራጨው የማስጠንቀቂያ ወሬ በራሱ ሽብር መሆኑንና አንድ ነገር ቢፈጸም ራስዋ አሜሪካን እጇ ሊኖርበት እንደሚችል እየተገለጸ በዚሁ መነሻ ነው። አንዳንዶች በዚህ ደረጃ ስጋት ያለው አገር ኤምባሲ “አዲስ አበባ ምን ይሰራል?” ሲሉ እየጠየቁም ይገኛሉ።

ለዚህ የሽብር ማሳሰቢያ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት!…“ሰውዬው በሕልሙ የጠላቱ ቤት ሲቃጠል ያያል። ይሄንንም ሕልሜ ጠብ አይልም ብሎ ያወራል። ሶስት ቀን ቢጠብቅ አልተቃጠለም። በመጨረሻ ሕልምህ ውሸት ነው ከምባል ብሎ የጠላቱን ቤት ራሱ አቃጠለው ይባላል። የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ እንደዚያ ይሆን?” ሲሉ ሕዝብ አይኑን አሜሪካ ላይ እንዲተክል አሳስበዋል።

የአብን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ በቲውተር አምዳቸው ” አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አገሪቱን የማተራመስ ሚና ብቻ ነው” ሲሉ ክፉኛ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ አያይዘውም ” አሜሪካ የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለማየት እውነተኛ ፍላጎት ቢኖራት ኖሮ ትርጉም ያለው ሚና መጫወት ትችል ነበር ” በማለት ሊሆን የሚገባ ነበር የሉትን አመልክተዋል። የሚያሳዝነው ግን አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ እየተከተለች ያለው ፖሊስ ማተራመስ ብቻ እንደሆነ ደግመው ጠቁመዋል።

ኤምባሲው አዲስ አበባ እምብርት ላይ ሆኖ ባሰራጨው ወሬ በስም ያልተራቸውንና “አሸባሪዎች” ያላቸው ሃይሎች ጥቃት የሚፈጽሙበትን ቦታ ዘርዝሯል። በዝርዝሩ መሰረት ዲፕሎማሲያዊ ተቋማትን፣ የቱሪስት ቦታዎችን፣ የመጓጓዣ ማዕከሎች፣ የገበያ ማዕከሎችና ሞሎች፣ የምዕራብ አገራት ንግድ ተቋማት፣ ሬስቶራንቶች፣ ሪዞርቶችን፣ የአካባቢ የመንግስት ተቋማትና ሌሎች የህዝብ መገልገያ ቦታዎችን የተነጣጠረ ጥቃት እንደሚሰነዘር አስፈራርቷል። ጥቃቱ በመጠነኛ ማስጠንቀቂያ ወይም ያለምንም ማስጠንቀቂያ ሊፈጸም እንደሚችል ዕቅዱን ይፋ አድርጓል። ይህን ሁሉ የሽብር እቅድ የዘረዘረው ኤማባሲው የአሜሪካ ኤምባሲ የጥቃቱ ኢላማ ስለመሆኑ ያለው ነገር የለም።

ይህ ሁሉ የሽብር ጥቃት እንደሚሰነዘር የጠቀሰው ኤምባሲው “የአሜሪካ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ በውጭ አገር ዜጎች ከሚዘወተሩ አካባቢዎችን ራሳቸውን እንዲያርቁ ይበረታታሉ” ብሏል። በዚህ ደረጃ ፍርሃት ካለ ኤምባሲውም ሆነ ዜጎቹ ለምን ሙሉ በሙሉ አገር ለቀው እንዲወጡ እንደማያደርግ ለአብዛኞች ግራ ነው። በጅቡቲ ያለው የአሜሪካ ጦር ዜጎቹን ለመታደግ ዝግጁ ነው መባሉ ግን የድራማው አመላካች እንደሆነ አብዛኞች አመልክተዋል።

ከዚህ ዝርዝር ዕቅድን ይፋ ካደረገ የአሜሪካን ኤምባሲ ወሬ ተከትሎ የአብን ሊቀመንበር “በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ ከደረሱት ውድመቶች ጀርባ TPLF ብቻውን እንዳልሆነ እንረዳለን” ሲሉም አሜሪካንን በስም ባይጠቅሱም አማራን በማውደም በኩል ጥምረት መኖሩን ባልተለመደ ሁኔታ በግልጽ በማህበራዊ አውድ ገፃቸው ጽፈዋል።


…….

Leave a Reply