ሃይሌና ፈይሳ በግንባር ለመስለፍ ቃላቸውን ለኢትዮጵያ አጸኑ፤ ሃይሌ “አፍሪካውያን ከጎናችን ቁሙ” ብሏል

አትሌት ፈይሳ ለሊሳን ተከትሎ “በግንባር መሰለፍን ጨምሮ ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ” ሲል ጀግናው ሃይሌ ገብረስላሴ ቃሉን ለኢትዮጵያ ማጽናቱን አስታወቀ። አገሩ በደቦ የተከፈተባትን ዘመቻ በማስታወስ መላው አፍሪቃውያን ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ በኢትዮጵያና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ በዓለም አደባባይ ኦሊምፒክ ሰፈር ይፋ በማድረግ ትህንገን በማስወገዱ ትግል ላይ ሃይልና ነዳጅ የከለሰው ለሊሳ ፈይሳ “እኔም ከመሪዬ ጋር እዘምታለሁ! ” ለማለት ጊዜ አልፈጀበትም። እውነት በተናገረ እንደተቀጠፈው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፣ በግልጽ በኦሮሞ ስም ከትህነግ ጋር የሚወሳወሱትን ” አቁሙሙ” ሲል የተናገረው ፈይሳ ” እዘምታለሁ” ሲል በገሃድ መናገሩ ክብርን አስችሮታል።

እሱን ተከትሎ “በግንባር መሰለፍን ጨምሮ ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ” ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ማስታወቁን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ይፋ አድርጓል።

Image

“ለእናት ሃገሬ በምፈልገው ልክ ምንም አላበረከትኩም አሁን ግን እኔ ሞቼ በኔ ላይ የሃገሬ ታሪክ ከፍ ብሎ እንዲወራ ስለምፈልግ ለአገሬ ዘምታለው” ፈይሳ ሌሊሳ

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ በኢትዮጵያ የተደቀነው አደጋ አፍሪካን የማንበርከክ ዓላማ ጭምር ያነገበ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሙከራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት መሆኗን የገለጸው ኃይሌ፤ ኢትዮጵያን በማንበርከክ የጥቁር ሕዝቦችን አኩሪ ታሪክ ለመቀማት የተቀናጀ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ ክብር ወደ ግንባር መዝመታቸው አገሩን ከሚወድ መሪ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን እና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተል ጥሪ አቅርቧል። መላ አፍሪካዊያን ትግሉ የሁሉም ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን በመገንዘብ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርቧል፡፡ “ኢትዮጵያን ብለን ተሸንፈን አናውቅም፤ ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ ናት” ሲል ነው አትሌት ኃይሌ የተናገረው።

በአንድ ወቅት የጎበኛት የቱሪስት መናኸሪያ የነበረችውን የሶሪያዋ አሌፖ ከተማ በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ምክንያት ወደ ፍርስራሽነት መቀየሯን ጠቅሷል።

Feyisa Lilesa: ′Athletes need to speak out′ | Africa | DW | 25.08.2016

“በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን በአገራችን ላይ ይህን መፍቀድ የለብንም” ያለው አትሌት ኃይሌ፤ “ከዚህ አንጻር ከደጀንነት ባሻገር በግንባር በመሰለፍ ጭምር አገሬ በምትፈልገኝ ቦታ ለማገልግል ዝግጁ ነኝ” ብሏል፡፡

የአሁኑ ትውልድ አባቶቹ አድዋ ላይ የሰጡትን ነጻነት አሳልፎ መስጠት እንደሌለበት ገልጾ፤ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን ተነስተዋል፤ ማንም ሊያቆማቸው አይችልም ነው ያለው፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ለዓለም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

ኢትዮጵያዊያን በግንባር ከመዝመት ባሻገር በደጀንነትም በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸውም አትሌት ኃይሌ አስገንዝቧል። በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከዚህ ቀደም ከሚሰሩት በእጥፍ በማከናወን በጦርነቱ የጠፋውን ሃብት መተካት አለባቸው ነው ያለው፡፡

“የዕለት ተዕለት ተግባራችን አሸባሪው ህወሓት ያወደመውን ሃብትና ለወደፊት ለመልማት ያለንን ውጥን ታሳቢ ያደረግ መሆን አለበት” ሲል ገልጿል።

Leave a Reply