የአፍሪካና የካሪቢያን ዳያስፖራ ምሁራን ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጣልቃ እንዲቆም ጠየቁ

የአፍሪካና የካሪቢያን ዳያስፖራ ምሁራን ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንዲያቆሙ ጠየቁ ። የአፍሪካና የካሪቢያን ዳያስፖራ ምሁራን ምዕራባውያን የጥቁር ህዝቦች የነጻነት አርማ በሆነችው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን እንዲያቆሙ ጠየቁ።የአፍሪካና የካሪቢያን ዳያስፖራ ምሁራን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወይይት አካሂደዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ኢትዮጵያ የቅኝ ገዢዎችን ፍላጎት በጽኑ በመታገል የራሷን ነጻነት አስከብራ የቆየች አፍሪካዊት ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ በአድዋ የተገኘው ድል ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነጻነትና የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ መጎልበት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡አብዛኛው አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ በአንድነት የሚያሰባስብ አህጉራዊ ድርጅት አዲስ አበባ ላይ እንዲመሰረት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና እንደነበራትም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ለተካሄደው የመድልዎ ስርዓትን የማስወገድ ትግል፣ ኔልሰን ማንዴላን ከማሰልጠን ጀምሮ የኢትዮጵያን ፓስፖርት እስከ መስጠት ድረስ ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጽኦ ማድረጓንም አስታውሰዋል፡፡በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ምእራባውያን አፍሪካን የመቀራመት ዝንባሌያቸው ሌላ ቅርጽ እየያዘ መምጣቱን የገለጹት አምባሳደር ተፈሪ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ጥቁር አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የምእራብ ሀገሮች ጣልቃ ገብነትና የዓለም አቀፍ ብዙኃን መገኛኛዎች ኢትዮጵያን የማጠልሸት ዘመቻ በማውገዝ፣ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም እና የጥቁር ህዝቦችን አንድነት ለመግለጽ በኢትዮጵያ “ግሎባል የጥቁር ህዝቦች ታሪክና ውርስ ማዕከል” ለማቋቋም የተወሰነው ውሳኔ ታሪካዊና የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ እንደገና እንዲያብብ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የምእራባውያንን ጫና በአንድነት መመከት ይገባልም ነው ያሉት፡፡የአፍሪካና የካሪቢያን ዳያስፖራ ምሁራን አሰባሳቢ እና የቲሲዲ ኮንሰልታንት ባለቤት አቶ ጸጋዬ ጫማ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አፍሪካውያንን ይበልጥ እያሰባሰበ በመምጣቱ በምእራባውያን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገሮች ላይ የሚደረጉ አስፈላጊ ያልሆኑ ጣልቃ ገብነቶችን ለመቋቋም በመላው ዓለም ያሉ ጥቁር ህዝቦች በአንድነት መነሳት አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ማእከል አድርጎ ሊመሰረት ሙሉ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ግሎባል የጥቁር ህዝቦች ታሪክና ውርስ ማእከል አፍሪካውያን ምሁራን በጋራ የነጻነት አርማ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ አንድነታቸውን በማጠናከር ለተቀረው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ቀጣይ ትግል ወሳኝ ምእራፍ ይከፍታል ብለዋል፡፡የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የምእራቡ አለም በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ኢትዮጵያን በማፍረስ የአፍሪካውያን እንዲንበረከኩ ለማድረግ የሄዱበት ርቀት ለእኛ ለአፍሪካውያን እውነቱን ለምናውቀው መፍትሄው በአንድነት መቆም እና መነሳት ብቻ ነው ብለዋል፡፡ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንጂ ከምእራቡ አለም እየተሰፈረ የሚሰጥ መፍትሄ አፍሪካን ለድህነት እንጂ ለብልጽግና አላበቃም ኢትዮጵያም ችግሯን እንድትፈታ የቆየና ታሪካዊ ስርአት ያላት በመሆኑ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሊተው ይገባል ብለዋል፡፡

See also  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ - ሰርጎ ገቦችን ሕዝብ እየጠቆመ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር መዝመታቸው ህዝቡን የሚወድ መሪ የመጨረሻ ውሳኔ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ለሰላም ከዚህ በላይ ዋጋ ሊከፈል አይችልም ብለዋል።በውይይቱም ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የህግና የሚዲያ ባለሙያዎች ፣ የጥቁር ፖለቲከኞችና የጥቁር ህዝቦች መብት ተሟጋቾች፣ የመንግስት አካላት፣ የታሪክ አዋቂዎችና የጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል መባሉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ሲል ኦቢኤን ዘግቧል።

Leave a Reply