ለንጮ ባቲ – አሜሪካ ቢሾፍቱ የተከሰከሰው ቦይንግ አውሮፕላን ጥቁር ሳጥን ላኩ ስትል አብይ አሕመድ ከልክለዋል

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሆነው ሲሰሩ የነበሩትና አሁን በሳውድ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በጆሯቸው የሰሙትንና የሚያውቁትን እውነት በመዘርዘር አሜሪካ ለምን ኢትዮጵያን እንደነከሰች ለሕዝብ ይፋ አደረጉ። ቢሾፍቱ የተከሰከሰውን አውሮፕላን የአደጋ ሳጥን እንዲያስረክቡ አብይ አሕመድ ተጠይቀው ፈቃደኛ አለመሆናቸው አንዱ ምክንያት መሆኑንንም አመልክተዋል።

“የአሜሪካና የኢትዮጵያ አለመግባባት እንዴት ተጀመረ?” የሚለውን እንዲያስረዱ አዲስ ዘመን ጥያቄ ያቅረበላቸው አምባሳደር ሌንጮ ባቲ፣ “አሜሪካኖቹ በዓለም ላይ ተፈርተውና ተከብረው መኖር እንዳለባቸው ጽኑ አቋም አላቸው። እናም በሌሎች አገሮች እንደለመዱት ተከፋይ ውሾች እየቀጠሩ መኖርን ይሻሉ” ሲሉ ባህሪያቸውን አስቀድመው እንደመንደርደሪያ አንስተዋል።

ቀደም ብለው “አብይ፣ አብይ… ” እያሉ አስጩኸው ብዙም ሳይቆዩ “ደፈረን” ያሉዋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጥላሸት መቀባት፣ ማጣጣልና ከስልጣን የሚወገዱበትን ሴራ ማሴር የጀመሩት የፈለጉት ባለመሆኑ እንደሆነ በዝርዝር ያስረዱት አምባሳደሩ፣ “ውሾች” ሲሉ የገለጿቸውን ተላላኪዎች ” አገር የሚያምሱ ሆዳሞች” ብለዋቸዋል።
በቅድሚያ የጠ/ሚ አብይ አህመድና የዶናልድ ትራምፕ ሚስጥራዊ የስልክ ውይይት ምን ይመስል እንደነበር ያወሱት ሌንጮ ባቲ፣ “የኢትዮጵያ ቦይን አውሮፕላን ብሾፍቱ በተከሰከሰበት ወቅት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደውለው ብላክ ቦክሱን ላክ ብለው ነበር” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ግን ” ብላክ ቦክሱ ወደ ፈረንሳይ እንዲላክ ተደርጓል” የሚል መልስ ነበር የመለሱት።

አምባሳደር ሌንጮ ይፋ ባደረጉት መረጃ የአደጋ ዝርዝር መረጃ ጠቋሚው ጥቁር ሳጥን ወደ አሜሪካ ቢላክ ኖሮ ቦይንጉ የተከሰከሰው በአብራሪው ጥፋት እንደሆነ ተደርጎ ነገሮች ተድበስብሰው ይቀሩ እንደነበር መረዳት እጅግ ቀላል፣ ውጤቱም ምን ያህል አስደንጋጭም ሊሆን እንደሚችል አንባቢያን እንዲያስቡት የሚጋብዝ ይሆናል።

የአሜሪካንና የምዕራቡ ሀገራት በኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት ቀድሞም የነበረ እንደሆነ አመልክተው ወደ አሁኑ ጉዳይ የተመለሱት አምባሳደር፣ የአባይ ግድብን ድርድር አስመልክቶ ትራምፕ ጫና ያደረጉት ለኢትዮጵያ ብለው እንደነበር ግለጸው “ድርድሩን የማትቀበሉ ከሆነ በሚሳይል ልትመቱ ትችላላቹህ” ሲሉ ማስፈራራታቸውን አመልክተዋል። ይህን ጊዜ አብይ አሕመድ ” ከማን ሀገር መሪ ጋር እየተነጋገርክ እንዳለ ታውቃለህ፤ ከኢትዮጵያ መሪ ጋር ነው እየተነጋገርክ ያለኸው ይምቱንና እንተያያለን” ሲሉ እሳት ጎርሰው እንደመለሱ አምባሳደሩ ይፋ አድርገዋል።

ከኤርትራ ጋር የተደረገው ዕርቅና የሰላም ግንኙነትን በአሜሪካና ምዕራቡ ዓለም እንዳልተፈለገ፣ ኤርትራን ለሰላሳ ዓመታ በተለያዩ ጉዳዮች ነክሰው ይዘው መቆየታቸውን፣ ከሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነትና በቀጠናዊ ትስስር ውስጥ ኤርትራን፣ ኢትዮጵያን፣ ጅቡቲንና ሶማሊያን የሚያዋጣ ጥምረት መፈጠሩ አንድ ላይ ምቾት እንዳልሰጣቸው ሌንጮ ባቲ አስረድተዋል።

“አሜሪካና ምዕራባውያን ከዚህ በፊት ሰምተውትና አይተውት በማያውቁት ደረጃ ብሔራዊ ኩራትና በራስ መተማመን ያለው መንግስት መመስረቱን ሊቀበሉት አልቻሉም” ሲሉ ያስታወቁት አምባሳደር ሌንጮ ባቲ፣ ጦርነቱ የዚሁ ነጸብራቅና የውክልና ስለመሆኑ በመረጃ አስደግፈው አስረድተዋል። “ይህ ጦርነት እንዳይከስት ብዙ ጥረት ተደርጓል፤ ግን ይፈለግ ስለነበር አልሆነም” ብለዋል። በአሜሪካ አይዞቹህ ባይነት የተደረገና እየተደረገ ያለ መሆኑንንም አመልክተዋል።

“አንድ ሀገር በጣም ውጤታማ የሚሆነው ህዝቡ ሲግባባ ፤ በዕድገት የሚያምንና ሀገሪቱን ለማሳደግ የሚፈልግ መሪ ሲኖር ፣ ከህዝብ ጋር የተዳመረ መንግስትና ሲፈጠር ነው” በማለት የተናገሩት ሌንጮ ባቲ ሁሉንም ጫና መቋቋም የተቻለውም ይህ በመኖሩ እንደሆነ አመልክተዋል። አያይዘውም “የአሜሪካን የእጅ አዙር ጦርነት አሸንፈው ከሚወጡ ሀገራት እትዮጵያ አንዷ እንደምትሆን መነሻቸው ሕዝብ ነው። መድረሻውም የህዝቡ ድል ነው” ብለዋል።

አምባሳደር ለንጮ ባቲ ” ዛሬ ኦሮሞን ነፍጥ አሲዞ ወደ ጫካ የሚያስገባ ምድራዊ ምክንያት የለም” በማለት በኦሮሚያ ነፍ አንስተው ሕዝብን በማሸበር ላይ ያሉትን ማውገዛቸው ይታወሳል።

Leave a Reply