አፕል “ስልክህን ራስህ” ጠግን አለ

አፕል ፈቃደኛ የሆኑ ደንበኞች ድርጅቱ ያዘጋጀውን መመሪያ በመከተል ራሳቸው ስልካቸውን መጠገን የሚያስችላቸውን ፕሮግራም አስተዋወቀ።

በአውሮፓውያኑ 2022 መጀመሪያ አካባቢ በአሜሪካ ይፋ የሚሆነው ይህ ፕሮግራም ባትሪ እና ስክሪን መቀየር እንዲሁም በቅርብ የተሰሩ የአይፎን ምርቶችን ካሜራም ለማስተካከል ይረዳል ተብሏል።

ነገር ግን አዲሱ የአፕል የጥገና ስቶር ከ20 በላይ የስልክ እቃዎችን እና መገልገያዎችን ነው የሚሸጠው።

ይህ የሆነው በቅርብ ሳምንታት ስልክን በራስ ማስተካከል መጀመር አለበት የሚል ቡድን ጫና ማሳደር መጀመሩን ተከትሎ ሲሆን ቡድኑ እውቀቱ እና ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች እንዲሁም አነስተኛ የኤሌክትሮኒክ መሸጫዎች በቀላሉ ስልኮችን ማስተካከል መቻል አለባቸው ይላል።

”ራስ አገዝ ጥገና እውቀቱና ልምዱ ያላቸው ቴክኒሺያኖች እና ተጠቃሚዎች ኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችን እንዲጠግኑ ይረዳል” ብሏል አፕል ባወጣው መግለጫ።

ነገር ግን በርካታውን ቁጥር የሚይዙት ተጠቃሚዎች ፈቃድ ያላቸውና በመጠገን ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ጋር ሄደው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቻቸውን እንዲያስጠግኑ ይመከራል ተብሏል።

የአፕል ከፍተኛ ኃላፊው ጄፍ ዊሊያምስ ”ታማኝ የሆኑ የአፕል መገልገያዎችን ማቅረብ መቻላችን ደንበኞች ያለምንም ስጋት የጥገና መገልገያዎችን በቀላሉ እንዲገዙና እንዲጠቀሙ ይረዳቸዋል” ብለዋል።

”ምርቶች ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ አድርጎ መስራትና ሲበላሹ ደግሞ በቀላሉ እንዲጠገኑ ማድረግ ተጠቃሚዎች ለከፈሉት ገንዘብ ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኙና መሳሪያዎቹን ለዓመታት እንዲጠቀሟቸው ያደርጋል” ይላል ድርጅቱ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሰል የጥገና አገልግሎቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ አይደለም በማለት አፕል ሲቃወም ቆይቷል።

በበይነ መረብ አማካይነት ደንበኞች ስልኮቻቸውን መመሪያዎቹን በመከተል እንዲጠግኑ አገልግሎት የሚሰጠው ‘አይፊክስኢት’ የተሰኘው ድረገጽ የአፕል ምርቶችን መጠገን አስቸጋሪ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን ይህንን ውሳኔ ተከትሎም ድርጅቱ ”ይህ ቀን ይመጣል ብለን አልጠበቅንም ነበር” ሲል በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

“አፕል ለረጅም ጊዜ ደንበኞች ስልካቸውን ራሳቸው እንዲጠግኑ ማድረግ አደገኛ ነው ሲል ቆይቷል። አሁን ደግሞ ጫናው ሲበረታ እና የአገልግሎቱ ፍላጎት ሲጨምር ሀሳቡን ቀይሯል” ብሏል ድርጅቱ።

አፕል እንዳለው ደንበኞች ይህንን አገልግሎት ሲጠቀሙ በአፕል እውቅና የተሰጣቸው ከ5 ሺሕ በላይ ጠጋኞችን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ 2800 ግለሰብ አገልግሎት ሰጪዎችንም መጠቀም ይችላሉ።

ቢቢሲ እንደዘገበው አፕል ይህንን ለማድረግ የተገደደኩት የራስ አገዝ ጥገና ፍላጎት በመጨመሩ እና የአፕል ምርት የሆኑ መጠገኛ እቃዎችና አገልግሎቶች ዋጋ ባለፉት ዓመታት በእጥፍ በመጨመሩ ነው ሲል ዋላታ ድርጅቱን ጠቅሶ መረጃ አጋርቷል።

Leave a Reply