ከመመሪያው ውጭ በህገወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ተመላላሽ መንገደኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ኮሚሽኑ አሰጠነቀቀ

የግል መገልገያ እቃዎችን በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ለማስገባት ለመንገደኞች የተፈቀደውን መመሪያ ተገን አድርገው ከመመሪያው ውጭ በህገወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ተመላላሽ መንገደኞች በመንግስትና በህጋዊው ነጋዴ ላይ ጫና እያደረሱ በመሆኑ ኮሚሽኑ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሰታወቀ።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣በመንግስት ገቢና በንግድ ስርዓቱ ላይ ጫና እያደረሱ በመሆኑ ኮሚሽኑ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል።

የዓለም አቀፍ መንገደኞች ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይዘዋቸው ስለሚመጡና ከቀረጥ ነጻ ስለተፈቀዱ ብሎም ስላልተፈቀዱ የግል መገልገያ እቃዎችን ለመወሰን መመሪያ ቁጥር 51/2010 ጸድቆ ስራ ላይ መዋሉን ጠቅሰዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት መሰረት ከመመሪያው ዓላማ ውጭ አንዳንድ ተመላላሽ መንገደኞች በህገወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው መንግስት በዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ እንዲያጣና በንግድ ስርዓቱም ላይ ፍትሀዊ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

በህገወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ተመላላሽ መንገደኞች የሚያደርጉት የገንዝብ ዝውውር በህጋዊ የፋይናንስ ተቋማት የሚከወን ባለመሆኑም ህገወጥ የገንዝብ ዝውውር እንዲስፋፋ፣ የኑሮ ውድነት እንዲባባስና የንግድ ስርዓቱም እንዲታወክ እያደረጉ መሁኑንም ጠቁመዋል፡፡

መመሪያውን ተላልፈው የተገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ወደ ህጋዊ የንግድ መረብ እንዲገቡ ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። በእነዚህ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ከሌሎች የጸጥታ አካላትም ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት መመሪያውን ሽፋን በማድረግ በዚህ ህገወጥ ንግድ ላይ የመንግስት ሰራተኞች ፣ የአየር መንገድ አስተናጋጆች እና የኮሚሽኑ ሰራተኞች ተሳታፊ መሆናቸወን ጠቁመው በእነዚህ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። (ኢ ፕ ድ)

See also  ሱዳንና ኢትዮጵያ በቁልፍ ጉዳዮች መስማማታቸው ተሰማ- "የትህነግ መጨረሻ ግልጽ እየሆነ ነው"

Leave a Reply