አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በዋግ ምድር በንጹሃን ላይ የፈጸመው ግፍ፡፡

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ንጹሃንን በግፍ መግደል፣ ማሰቃየት፣ ንብረት ማውደምና መዝረፍ ያደገበት ግብሩ ነው። በአማራ ላይ አወራርዳለው ያለውን ሂሳብም ንጹሃንን በመግደል የጥላቻ ጥጉን አሳይቷል። የሽብር ቡድኑ በዋግ ቆዝባና ጭላ በቆየባቸው ቀናት ያደረገውም ይህንኑ ነው፤ ንጹሃንን ያለምክንያት በግፍ ገድሏል።

አማረ ዳኘው የ28 ዓመት ወጣት ሲኾን የሶስት ሕፃናት አባት ነው። ከንግድ ሥራ ሌላ ምንም የማያውቅ ንጹህ ለፍቶ አዳሪም ነው። የወላጅ አባቱ ጧሪ፣ የእህቶቹ እና ወንድሞቹ ብቻ ሳይኾን የልጆቻቸው ወንድምም፣ አባትም እንደነበር ቤተሰቦቹ ነግረውናል። ቤተዘመዱን ብቻ ሳይኾን የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር ባጋጠመው ጊዜ ፈጥኖ በመድረስ ባለችው ሞተር ሳይክል እርዳታ የሚሰጥ የአካባቢው አለኝታ እንደነበርም ገልጸውልናል።

ባለቤቱ ወይዘሮ ደስታ መላሽ እንደነገሩን በሽብር ቡድኑ እና በወገን ጦር መካከል በነበረው ውጊያ የተጎዱ የወገን ታጋዮች መኖራቸውን ሰምተው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በጋራ በመኾን ውጊያ ወደ ተካሔደበት ቦታ ሄዱ። ከሰዓታት በኋላ ሌሎች ጓደኞቹ ሲመለሱ አቶ አማረ ቀረ። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ የተወሰኑ የሽብር ቡድኑ አባላት አቶ አማረን ወደ ቤቱ በመውሰድ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ጠየቁት። ሟችም ሁለት ሽህ ብር ሰጣቸው።

የሰጣቸው ገንዘብ እንደማይበቃቸው እና እንዲጨምራቸው በማስፈራራት ጠየቁት። በዚህን ጊዜ ባለቤቱ ወይዘሮ ደስታ ባለቤታቸውን ከሞት ለመታደግ በአደራ የተቀመጠ 20 ሺህ የሚጠጋ ብር አንስተው ሰጧቸው። ጨካኞቹ ግን አቶ አማረን በዚህ አልተውትም፤ አንቀው ወደ ጫካ ወሰዱት እንጂ። በዚህ ጊዜ የተደናገጡት ባለቤታቸው ተከትለው በመሔድ የሽብር ቡድኑን አባላት ተማጸኗቸው።

የሽብር ቡድኑ አባላትም ምንም እንደማይኾን እና ለጥያቄ እንደሚፈለግ ነገሯቸው። ባለቤታቸው ግን የሽብር ቡድኑ በሰጧቸው ምላሽ በመጠራጠራቸው የአካባቢውን የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ይዘው ዳግም ለመማጸን እንደገና ተመልሰው ሄዱ። መገለጫቸው ጭካኔ የኾነው የሽብር ቡድኑ አባላት እምነት ብሎ ነገር የላቸውምና በጭካኔ ገደሉት።

የሽብር ቡድኑ አባላት የገደሉት አቶ አማረን ብቻ ሳይኾን ልጆቹን ያላሳዳጊ፣ ወላጅ አባቱን ደግሞ ያለ ጧሪ አስቀርተዋቸዋል። የሽብር ቡድኑን በጋራ በመቆም መታገል እንደሚገባም ገልጸዋል። በሚችሉት ኹሉም እንደሚደግፉ ወይዘሮ ደስታ ገልጸዋል።

የሟች አባት አቶ ዳኘው ወልዴ የ76 ዓመት አዛውንት ናቸው። ሟች ልጃቸው ጧሪያቸው አንደነበርም ነግረውናል። ያስቀመጠውን ብር እና የንብረቱን መጠበቂያ ሽጉጥ ከቀሙ በኋላ ወደ ጫካ በመውሰድ በጥይት በጭካኔ በግፍ መግደላቸውን ገልጸውልናል። የዜጎች ሞትና ስደት እንዲቆም ኢትዮጵያውያን በጋራ መሰለፍ እንዳለባቸው ነው ያስረዱት።

የሟች እህት ወይዘሮ ጣፈጡ ዳኘው ወንድማቸውን ለመጠየቅ ከሰቆጣ ተነስተው ሲመጡ በሽብር ቡድኑ በግፍ ተገሎ አስከሬኑን ነበር ያገኙት። ሟች የራሱን ልጆች ብቻ ሳይኾን የቤተሰቡን ልጆችም አሳዳጊ፣ ለፍቶ አደር እንደነበር ነግረውናል። በወንድማቸው መገደል ቁጭት ያደረባቸው የሟች እህት የሽብር ቡድኑ ዳግም የአማራን መሬት እንዳይረግጥ በሚችሉት ኹሉ ለመታገል ቆርጠው ተነስተዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

Leave a Reply