” … ጥፋቱን ካደረሱ መካከል በዩኒቨርሲቲው የተማሩ ተማሪዎች አሉበት “

የወሎ ዩኒቨርሲቲን በአጭር ጊዜ ወደ መማር ማስተማር ስራ ለማስገባት እንደሚሰራ ተገልጿል።

ህወሓት ባደረሰው ዝርፊና ውድመት ወሎ ዩኒቨርሲቲ 10 ቢሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት እንደደረሰበት ተገልጿል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ለሸገር ኤፍ ኤም 102.1 በሰጡት ቃል ፥ ” ህወሓት ተሳቢ መኪና አቅርቦ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉትን ትልልቅ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች ፣ ላብራቶሪ ቁሳቁሶች ፣ የወርክሾፕ፣ የኢንጂነሪንግ ፣ የቴክኖሎጂ ፣ የህክምናና ጤና ሳይንስ ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ፣ የግብርና ኮሌጅ ቁሳቁሶችን ነቅሎ ጭኖ ወስዷል ” ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዜዳንት ዶ/ር መንገሻ ፥ ” ይህ የጥፋት ኃይል ዩኒቨርሲቲው በሚሊዮን ሚቆጠር ገንዘብ አውጥቶ የገነባቸውንና በጣም የሚጠቅሙ ቁሳቁሶች ዘርፎ መውሰድ አይደለም የሚገርመው ፤ መውሰድ ያልቻለውን ኢንስታሌሽን ( የኤሌክትሪክ ፣ የኢንተርኔት ፣ የወርክሾፕ) በአጠቃላይ በጣጥሶ ከሱ ቁጥጥር ውጭ የሆኑትን / በቀላሉ ትራንስፖርት ማድረግ የማይችላቸውን ባሉበት እንዲወድሙና ተቋሙ ወደፊት እንዳይጠቀምበት አድርጎ ነው የሄደው ” ብለዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ እጅግ ዘመናዊ የሚባል የአይሲቲ መሰረተልማት ካሉት ተቋማት አንዱ ሲሆን ህወሓት ወደ ዳታ ማዕከል በመግባት የሚጠቅሙ ኮምፒዩተሮችና መነቀል የሚችሉትን ትልልቅ ባትሪዎችንና ቺፖችን ነቅሎ ወስዷል።

ኢንስታሌሽን ጋር የተገናኙ ትልልቅ ቁሳቁሶች ባሉበት ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ ማውደሙን ዶ/ር መንገሻ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በሁሉም ካምፓሶች ብዙ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በገንዘብ ሲተመን 10 ቢሊዮን ብር ይደርሳል።

ጥፋቱን ካደረሱ የህወሓት ቡድን አባላት መካከል በዛው በዩኒቨርሲቲው የተማሪ ተማሪዎች መኖራቸውን ፕሬዜዳንቱ ተናግረዋል።

ዶ/ር መንገሻ ፥ ” በጣም የሚገርመው እኛው ተቋም የሰለጠኑ የተማሩ፣ የመጀመሪያ ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙ ተማሪዎች አሳብዶ እዚህ ቡድን ውስጥ አስገብቶ ይህን ተቋም በማፍረስ ሂደት ላይ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው በአካባቢው የነበሩ እራሳቸው እኛ እዚህ ተምረናል እያሉ ለፀጥታ ኃይሎች ቃል በቃል እንደነገሯቸው የኛ የፀጥታ ኃይሎች ምስርክነታቸውን ነግረውናል።

በጣም ሰፋ ያለ ቡድን ጠመንጃ የያዘ ቡድን ፣ መፍቻ የያዘ ቡድን እንደገና ጀሌ ቡድን በወረፋ እየመጣ ትልልቅ ተሳቢ መኪናዎችን ይዞ እየገባ መካኒክ እሱ የሚፈታውን ወደተሳቢ መኪና የሚጭን ጀሌ ጉልበት ያለው ጫኝ ይሄ ሁሉ ተደራጅቶ የመጣ ኃይል መሆኑን ነው በአካባቢው የነበሩ የተቋሙ የፀጥታ አባላት የአይን ምስክር ሆነው የነገሩን ” ብለዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ቀደመው የመማር ማስተማር ስራ እንዲገባ ለማድረግ የመንግስት ፣ የክልል እና የአካባቢው አስተዳደር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት እደሚተባበሩን እርግጠኛ ነን ያሉት ዶ/ር መንገሻ ” በእኛ ግምት መማር ማስተማሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሰን እናስጀምራለን” ብለዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ30 ሺህ ላይ ተማሪዎችን ሲያስተምር የነበረ የ2ኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዜዳንት ለሬድዮ ጣቢያው በሰጡት ቃል ተናግረዋል።

@tikvahethiopia

Leave a Reply