ሦስተኛው የቱርክ እና አፍሪቃ ግንኙነት ጉባኤ « ለጋራ እድገት እና ብልጽግና የጎለበተ ወዳጅነት»

ለሁለት ቀናት በሚዘልቀው የቱርክ አፍሪቃ ትብብር ጉባኤ ቱርክ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ከፍ እንደምታደርገው ተገለጠ። ከፊታችን ዐርብ እስከ ቅዳሜ ድረስ ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ በሚካኼደው ጉባኤ የ39 ሃገራት ሚንሥትሮች እና 13 ፕሬዚዳንቶች ለመሳተፍ ከወዲሁ ማረጋገጫ መላካቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። «ለጋራ እድገት እና ብልጽግና የጎለበተ ወዳጅነት» በሚል መሪ ቃል በሚካኼደው የሁለት ቀናት ጉባኤ የቱርክ ርእሰ-ብሔር ሬቺፕ ጣይብ ኤርዶሃን ቅዳሜ ዕለት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል። ጉባኤው ቱርክ ከአፍሪቃ ጋር ያላት ንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ላይ ያተኩራልም ተብሏል። ቱርክ በተለይ በፀጥታ እና ደኅንነት ዘርፍ ከአፍሪቃ ጋር የምታደርገው ግንኙነት እየተጠናከረ መኼዱን የዜና ምንጩ አክሎ ጠቅሷል።

ቱርክ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለይ በደኅንነቱ ዘርፍ ይበልጥ ከፍ ማድረግ እንደምትሻ እና አፍሪቃውያን ሃገራትም ከቱርክ ወታደራዊ የጦር መሣሪያዎችን የመግዛት ፍላጎታቸው መጨመሩ ተገልጧል። ለአብነት ያህልም፦ ቱርክ የጦር መሣሪያዎች ሽያጭ በተለይም ሰው አልባ ደምሳሽ ጢያራዎች (ድሮኖች) ከኢትዮጵያ፤ ሞሮኮ፤ ቱኒዝያ እና አንጎላ ጋር እንደምታከናውን የጠቀሰው የዜና ምንጩ ግብይቱ በርካሽ ዋጋ ስለሆነ አፍሪቃውያን ሃገራት ፍላጎታቸው ጨምሯል ብሏል።

ምዕራባውያን ሃገራት ቱርክ ሰው አልባ ደምሳሽ ጢያራዎችን ወደ ኢትዮጵያ ልካለች ይላሉ። በአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልእክተኛ ጄፍሬ ፌልትማን በቅርቡ ወደ ግብፅ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ሲጓዙ ወደ ቱርክም አቅንተው ነበር፤ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ለመነጋገር። እዚያም ከቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሴዳት ኦይናል ጋር መነጋገራቸውን ቱርክ አንካራ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሴ ገልጧል።

ቱርክ ከአፍሪቃ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ታደርጋለች በተባለው ወታደራዊ ትብብር ዓለም አቀፍ ጫና ቢበረታባትም ሽያጩን በማከናወን ላይ ትገኛለች ብሏል የዜና ምንጩ። በዚሁ ጉዳይ ላይ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ቃል አቀባይ ኅዳር ወር ውስጥ ተጠይቀው ሲመልሱም «ኢትዮጵያ እነዚህን ድሮኖች ከፈለገችው መግዛት ትችላለች» የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። ለኢትዮጵያ ሰው አልባ ደምሳሽ ጢያራዎችን ቱርክ ስለመሸጧ አለያም ስላለመሸጧ ያለችው ነገር ግን የለም።

ከጥር ወር እስከ ኅዳር ድረስ ባሉት ጊዜያት የቱርክ መከላከያ እና በረራ ወደ ኢትዮጵያ የላከው ከ$235,000 ዶላር ወደ $94.6 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ግንኙነቷን ከምንጊዜውም በላይ ያጠናከረችው ቱርክ ጎረቤት ሶማሊያ ውስጥ የጦር ሰፈር አላት። via – DW

Leave a Reply