ያለ ፍቃድ የባንክ ስራን ሲሰራና የማታለል ወንጀል ሲፈፅም የነበረው ተከሳሽ ተፈረደበት

ተከሳሽ አረጋ ነጋ ያለ ፍቃድ የባንክ የሀዋላ ስራ ሲሰራና እጣ ደርሷችኋል በማለት አጭር የፅሁፍ መልዕክትና ኢሜሎችን በመላላክ የማታለል ወንጀል በመፈጸሙ ክስ ሊመሰረትበት ችሏል፡፡
ተከሳሽ አረጋ ነጋ ኤምቤሌ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 (1) (ሀ)፣ 692(1) እና የባንክ ስራ አዋጅ ቁጥር 592/2000 አንቀፅ 3 (1) እና 58 (1) ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ በፈፀማቸዉ ሁለት ወንጀሎች በዐቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተበት ሲሆን፤ በክሱ ዝርዝር ተከሳሹ ምንም አይነት ህጋዊ ስልጣን ሳይኖረው የግል ተበዳይን በ2012 ዓ.ም የኮካኮላ ኩባንያ በለንደን ከተማ ባከናወነው አለም አቀፋዊ የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ በተበዳይ የሞባይል ስልክ ቁጥር ላይ ዕጣው ለሚያስገኘው 5 መቶ ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ ሽልማት የተመረጡ በማስመሰል አሳሳች አጭር የፅሁፍ መልዕክትና ኢሜሎችን በመላላክ ተከሳሽ በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘው የኮካኮላ ካምፓኒ በኢትዮጵያ ወኪል እንደሆነ በመግለፅ ተበዳይ የተሳሳተ እምነት እንዲያድርበት ካደረገ በኋላ ይህንን ሽልማት ለማግኘት አስቀድሞ ለህጋዊ ፍቃድና ለአገልግሎት ክፍያ የሚሆን 62 ሺህ ብር በባንክ እንዲያስገባ ማድረጉን የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

በሌላ ክስ ደግሞ ተከሳሹ አረጋ ነጋ የባንክ ስራን ለመስራት የሚያስችል ህጋዊ ፍቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሳይኖረው በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ መላክ ሲፈልጉ በሳውዲ የሚኖሩ ግብረአበሮቹ ሊልኩ የሚፈልጉትን ገንዘብ በመቀበል ተከሳሽ እንዲላክላቸው የተባሉትን ሰዎች ስም፣ አድራሻና የገንዘብ መጠኑን በሚደረግለት ገለፃ መሰረት ተከሳሽ አዲስ አባባ የሚገኙ የገንዘብ ተቀባዮች በአካል በመስጠት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ገንዘብ ተቀባዮች በተለያየ ጊዜ 348 የሀዋላ መልዕክቶችን በመላክ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በማስተላለፍ ይህ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተላለፈውን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ተልኮ ቢሆን ኖሮ ሀገሪቱ ታገኝ የነበረውን 2.2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ያሳጣ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል።

ዐቃቤ ህግም በተከሳሽ ላይ ያቀረባቸውን ሁለት ክሶች በማስረጃ በበቂ ሁኔታ ያስዳ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ እንከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ አረጋ ነጋ በዐቃቤ ህግ የቀረበበትን የሰው እና የሰነድ ማሰረጃዎች ማስተባበል ባለመቻሉ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ በ10 ዓመት ፅኑ እስራትና በ1 መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡


Leave a Reply