ትህነግ “መንግስትን ለመጣል መረባረቢያው ጊዜ አሁን ነው” ሌማትና መንግስት መገልበጥ አንድ ናቸው?

“የኢትዮጵያ ህዝቦች የፋሽስት ቡድኑ ቀይ ውሸት በማጋለጥና እድሜው ለማሳጠር የምትረባረቡበት ወቅት አሁን መሆኑ ተረድታቹሁ የድርሻቹ ልትወጡ ይገባል” የሚለው የትህነግ መግለጫ መጸዳጃ ቤት እንኳን ለመድረስ ጊዜ አይሰጥም። መላ ሰውነትን እንደ መተሬ ስለሚያናውጥ እንደ ትህነግ ወራሪዎች በየተገኝበት ሸረተቴ መቀመጥን የሚያስመኝ ነው። ወልደያ ሊያዝ ሰዓታት ሲቀር ነው ይህ ጥሪ ከትህነግ ” ለኢትዮጵያ ሕዝብ” ተብሎ የተላለፈው። ጥሪ አስተላላፊ ትህነግ፤ ጥርው ሕዝብ መንግስቱን ገልብጦ ትህነግን እንዲያነግስ፣ ማጀቢያ ክሊፖች በአማራና አፋር ክልል በትህነግ የተፈጸሙ እኩይ ተግባራት ….

ነጻ አስተአየት በመምህር ፍቃዱ ዴሬሳ ምስራቅ ሸዋ

ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በሚል ስያሜ የሚጠራውና መንግስት” የሚለውና በኢትዮጵያ ሕዝብ የመረጠውን መንግስት “የፋሽስቱ አብይ መንግስት”፣ሕዝብ እንደ አይኑ ብሌን የሚያየውንና ከዕለት ጉርሱ እየቆረሰ በየዕለቱ ስንቅና ድጋፍ የሚሰጠውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ” የአብይ ወታደሮች” በሚል የሚጠራው ትህነግ ከመቀለ ከሶስት ቀን በፊት ባወጣው መግለጫ መንግስት እንዳለቀለትና ይህን የተረዱ የውጭ ዜጎች አገር እየለቀቁ በመውጣት ላይ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር። ቃል በቃል እንዲህ ይነበባል።

ስለ ዋጋ ንረትና ኢኮኖሚ መዳከም ጠቅሶ ” …. የፋሽስት አብይ አሕመድ ውድቀት አይቀሬ መሆኑ በውል የተገነዘበው ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ፣የተለያዩ ተቋማት እና ሃገራትም ተወካዮቻቸው፣ አምባሳደሮቻቸውና ሰራተኞቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ አድርጓል።” ሲል ሰራዊታቸው ያለበትን የአሸናፊነት ደረጃ ያጎላል።

ተመድ ሰራተኞቹ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱን የጣለውን ገደብ ያነሳበት መረጃ ነው። ይህ ደብዳቤ የወጣው ልክ ትህነግ መግለጫውን ባወጣበት ቀን ዲሰምበር 17 ነው። መገጣጠም

ከስሙ ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ጠረን የሌለው፣ እንደ ስሙ ራሱንና የሚፈልጉትን ይዞ የማይሄድ፣ በሕዝብ የተጠላ፣ ለምን የሚጠላትንና ሊያፈርሳት ሌት ተቀን የሚያሴርባትን አገር ስም እንደሚያነሳ፣ የሴራው ሁሉ ጠንሳሽና አምራች ራሱ ሆኖ ሳለ ስለምን አዛኝ ለመምስል እንደሚደክም፣ እግሩ በረገጠበት ሁሉ እንደ ተምች የሚያወድም፣ ያገኘውን ሁሉ የሚያመነዥግ፣ ሰብስቦ የማይጠግብ፣ በምቀኝነት ላይ የተተከለ፣ የበታችነት ስሜት የሚያሰቃየው፣ ትህነግ ይህንን ሲል የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ በርካታ የውጭ ዜጎችና ኤምባሲዎች ይቅርታ እየጠየቁ ተመልሰው እየገቡ ነው። የዩኤስ አይ ዲ ሃላፊዎች ነገሩን ለማባባስ ወደ ኬንያ አምርተው የነበረ ሲሆን አሁን ለመመለስ ቪዛ ጠይቀው በገሃድ ይቅርታ ጠይቁ መባላቸውን እየመሰከሩ ነው።

እንደ ግሪክ ያሉ ኤምባሲዎች ” አሜሪካ ያለችውን ሰምተን ነው” በሚል በገሃድ “አገሪቱ ሰላም ነች” በሚል ጥፋት መስራታቸውን አምነው መመለሳቸውን መስክረዋል። መንግስትን ” ውሸታም” የሚለውን ትህነግን ወይስ ባለ ጉዳዮቹን?

አስገራሚው መግለጫ ” የትግራይ ሰራዊት በራሱ ፍላጎት የለቀቃቸው አንዳንድ የሰሜን ሸዋ እንዲሁም ኮምቦልቻ እና ደሴ ከተማዎችን በውግያ እንደያዘ አስመስሎ መዋሸቱ ሳያንስ ሰሞኑ ደግሞ በዚሁ ገባሁ፣ ተራራ ያዙኩኝ፣መንገድ ቆረጥኩኝ፣ ወዘተ” እንደሚል ያትትና መሳሪያ እንኳን የሌላቸው ገጀራ በመያዝ አስልፎ ማስጨረሱንና የትግርያ ሃይሎች ሰማኒያ ሺህ የሚደርስ ወይም ከዚያ በላይ ሃይል እንደገደሉ በጅግንነት ያውጃል።

ሲጀመር ለምንና ለማን በአማርኛ እንደሚጽፉ፣ ዜና እንደሚያዘጋጁና እንደሚያሰራጩ በውል ያልተረዱት የትህነግ ተገዳላዮች “አንዳንድ የሰሜን ሸዋ” አካባቢን ወደው መልቀቃቸውን ሲያስታውቁ አሁን ድረስ በእጃቸው የሚገኙት የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች የትኞቹ እንደሆኑ አላስታወቁም። ምን አልባትም ተበጣጥሶ መውጪያ ስላጣው ወራሪ ሃይላቸው እያወሩ ከሆነ ምላሹን ለትግራይ ምስኪን ወላዶች መልስ የማፈላለጊያ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሸዋ ምድር ላይ ወራሪ የሚባለው ሃይል ከምድር ስር ካልሆነ ሌላ አድራሻ እንዳለው አይታወቅም። ካለ አብረን እናጣራለን።

ደሴና ኮምቦልቻም በፈቃዳቸው እንደለቀቁ ሲያስታውቁ በዚያው ቀን “የአትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት በቆቦ ግንባር ቀደም ብሎ የዞብል ከፍተኛ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ የነበረ ሲሆን፣ በራያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉትን ከፍተኛ ቦታዎችን ጨምሮ ተቆጣጥሯል፡፡በዞብል ደቡብ አቅጣጫ ደግሞ የጉራ ወርቄ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የነበረው የወገን ጦር አሁን ደግሞ የጉራ ወርቄ ከፍተኛ ሰንሰለታማ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ በማጽዳት፣ ቀደም ብሎ የተቆረጠውን የወልድያ መቀሌ መሥመር አሰፋፍቶ፣ ወደ ወልድያ በቅርብ ርቀት እየገሠገሠ ይገኛል” የሚል ዜና አብስሮ ነበር። ከአንድ ቀን በሁዋላም ወልደያን በጁ ማስገባቱን ከነዋሪዎቹ የሰርግና ምላሽ ትዕይንት ጋር ቲርሊርቪዥን አሳይቷል።

ወልደያ ስትለቀ፣ ወደ በሰቆጣ ለመሹለክ ወደ ላይሊበላ የገባውና እዛው ግድም አንዴ ወደ ጋሸና አንዴ ወደሌላ እንደ ሸማኒ መወርወሪያ ሲንፈራገጥ የነበረው ሃይል ምን ደረሰበት? የሆነውን የሚያውቅ ያውቀዋል። በተለይ ትህነግ ጠንቅቆ ይረዳል። “ላንቃቸውን እናዘጋቸዋለን” እያለ ላንቃው እስኪነቃ ድረስ ይለፍለፍ የነበረው ጌታቸው ረዳ እንደወትሮ መቀደድ እንኳን ቢቀር ለመተንፈስ አስኪያንቀው አቅም እስኪያጣ ድረስ መዘጋቱ ምን እንደሆነ አመላካች ነው።

ነገሩ ሁሉ ዛሬ ተቀይሮ፣ ጉዞና ወደ አዲስ አበባ መሆኑ ቀርቶ ወደ መቀለም እንደተፈለገ መመልስ የማይቻልበት ሆኗል። ካለ ምንም ማጋነን ካሁን በሁዋላ በጦርነት ትህነግ ሊቀይረው የሚችለው ቅንታት ጉዳይ የለም። ባዶ ቤት ተድርጎ የነበረው መከላከያ ሙሉ ሆኗል። ደጀኑ የሚዝል አይመስልም። መንግስት ሙሉ የህዝብ ድጋፍ አለው። ክልሎች በሙሉ አንድ አቋም ላይ ናቸው። ኦሮሚያ በትራክተር ማረስ ይሻለናል ብሎ ከወዲያ ወዲህ ሊወራጭ የሚሞክረውን የሸኔ ሃይል እየመነጠረ ነው። አፋርና አማራ ክልል ከትህነግም ሆነ ከትህነግ ደጋፊዎች ጋር ውል ቀደዋል። እናም ትህነግ አሁንም ምን ለማድረግና ማንን ለመምራት አስቦ ስለ ኢትዮጵያ እንደሚያወራ መረዳት አይቻልም። ግራ በመጋባት ስሜት ውስጥ ነው እንዳይባል በዚሁ እዳሪ አሳቡ ኖረበት።

ባስቸኳይ የሚከተለው ይሁን

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ነጻ የማውጣት አሳቡ የሚተገበርና የምሩን ከሆነ ስፍራው ትግራይ፣ ህዝቡም የትግሬ ሕዝብ ብቻ ነው። የትግሬ ሕዝብ ሲባል ” እስካሁን ኢትዮጵያ በድላናለች፣ እንዳንማር፣ እንዳንነግድ፣ እንዳንሰራ፣ እንዳንሾም፣የቀበሌና የመንግስት ቤት እንዳንይዝ፣ ሕንጻ እንዳንገነባ፣ ሆቴል እንዳንከፍት፣ በትራንስፖርት መስክ እንዳንሰማራ፣ በውጭ ንግድ አስመጪና ላኪ እንዳንሆን፣ በንኮችና ኢንሹራንስ እንዳናቋቁም፣ክሊኒክና ሆስፒታል እንዳንከፍት፣ …” በሚል ከሌሎች የአገሪቱ ሕዝብ ተለይተው የተጨቆኑና በትህነግ መሪነት ነጻ ለመውጣት የተስማሙትን ማለቴ ነው። የማይሳማሙ ጥቂቶች ከሆኑ በአብላጫ ድምጽ ይገዛሉ ወይም ሌላ አማራቻቸውን ይፈልጋሉ “ከሁለት” ጉዳይ አንዱን በመምረጥ፤

ጉዳዩን ለማንሳት ያህልና ሃቁን ለመነጋገር እንጂ መነሻው ስህተትና ሌላ ዓላማ ያነገበ ስለሆነ መፍትሄውም ጠማማና ለሕዝብ የሚበጅ እንዳልሆነ አምናለሁ። ቢሆንም ከለውጡ በሁዋላ ቀስ እየለ በስውር ሲቆመር የነበረው ሴራ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ደርሷል። እንደ አማራ ክልል ባይሆንም በትግራይ መሰረተ ልማት ተጎድቷል። ሰዎች ሞተዋል። የጦርነት አስከፊ ውጤቶች ታይተዋል። ለዚህ ሁሉ መነሻ ምክንያት የሆነው የአገር መከላከያ መታረድና በክደት መመታቱ የፈጠረው ክፍተት ጉዳቱን ከፍ ሊያደርገው ችሏል። ይህ በድንብ በሰከነና ከራሳቸው ጋር በታረቁ ወገኖች ጊዜውን ጠብቆ ይፋ የሚሆን የኢትዮጵያ ጥቁር ታሪክ ነው። መከላከያ ላይ የሆነው እንዲሁ ዝም ተብሎ የሚረሳና የሚድበሰበስ፣ እንደ ተራ የሳት እራት ቢራቢሮ ሞት የሚወሰድ አይሆንምና!! ፍትህ የመከላከያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ወንጅል የፈጸሙ፣ ያስፈጸሙ፣ የተላላኩና የከዱትን እንዲሁም ሌሎች ጀሌዎችን ያካትታል። ኢትዮጵያ ይህን የመፋረድ ህጋዊና ህገ መግስታዊ ስልጣን አላት። በመጯጯህ የሚሆን ነገር የለም። በመጯጯህ ቁስልን መደበቅ አይቻልም።

በቀጣይ አስቀድሞ ዝግጅት ያደረገውና ሁለት ሚሊዮን የሚሆን ሃይል እንዳለው ያስታወቀው ትህነግ አማራና አፋርን ወረረ። ትህነግ በወረራ በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ ምን እንዳደረገ ባልዘረዝርም ከየት የመጣ እንደሆነ ግልጽ ያልሆነ በበሉበት ሌማት ላይ፣ በቢሮዎችና ማምለኪያ ስፋራዎች ውስጥ መጸዳዳት፣ ንብረት ማጋየት፣ የእምነት ተቋማትን ማርከስ፣ የደቦ ወሲብ መፈጸም፣ አዛውንቶችን መድፈር፣ ባልን ገሎ አስከሬን አሳቅፎ ማክረም፣ ድመት፣ ውሻ፣ ላም መግደል ወዘተ … መሰረተ ልማቶች ማፍረስ፣ ሃኪም ቤት፣ የትምህርት ተቋማትና አገለግሎት መስጫዎችን መዝረፍ፣ ከዘረፋ የተረፉትን ማውደም፣ ከትቅም ውጭ ማዋል… የነዋሪዎችን ሱቅ፣ ድርጅት፣ ቤት፣ ሃብት…. የገበሬዎችን እርሻ፣ ከብቶች፣ እህል፣ እንሳት … ምን የቀረ ነገር አለ እንዳልሆነ ተድጓል። ይህ ማንም ሊክደው የማይችል የተባሳ ሁሉ ጠባሳ ነው። ምክንያትና ሰበብ የማይቀርበበት፣ “ተገድጄ” የሚል ድኩማን ምክንያት ተናግሮ የሚያመልጡበት እንደማይሆን ይህዝብ ስሜት ያሳብቃል። ሁሉም በሚባል ደረጃ ተጥይፏል። ውስጡ ተቆጥቷል። ባዩት ግራ የተጋቡና ምን አይነት ስሜት እንደሚሰማቸው መረዳት ያልቻሉ ጥቂት አይደሉም። እንግዲህ ፍትህ ሲባል ትግራይ ሆነ የተባለው ብቻ ሳይሆን በአፋርና አማራ ክልል የሆነውንም ያካትታል። ሂሳብ የሚወራረድ ከሆነ አፋርና አማራም በፍትህ ሂሳብ ማወራርድ ከፈለጉ መከራከር አይቻልም። ክርከር ከተነሳም የሃይል ጉዳይ እንጂ ሌላ አማራጭ አይኖርም። ይህ በገሃድ እየተነገረ ያለና በፓርቲም ደረጃ መግለጫ እየወጣበት ያለ ሃቅ ነው።

ሃቁ ይህ ከሆነ ከሁሉም ወገን ፍትህ ይበየን ዘንዳ ሕዝብ ድጋፍ ማድረግ አለበት። በደለኞች ለህግ ተላልፈው እንዲሰጡ መግፋት አለበት። አገርና ህዝብን ለይተው እንዲጠቃ ባደራጁ፣ ባሰታተቁ፣ ዕቅድ ባወጡና ባዘመቱ ላይ ፍትህ እንድትቆምባቸው ህዝብ በፊትለፊት መጠየቅ አለበት። ሚዲያዎችም ይህን ሃቅ ይዘው በደለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ መወትወትና ህዝብን ማነሳሳት ይጠበቅባቸዋል። ይህ እስካልሆነ ድረስ አብሮ መስነበት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የሚያመላክቱ ጉዳዮች እየታዩ ነው።

በዚሁ መርዛማ የዘር ፖለቲካ ሳቢያ ቤተሰብ ፈሷል። ልጆች ተበትነዋል። ሰሞኑን ዓማራ ክልልና አፋር የሆነውን ያዩ የመረረ ቃላት እየወረወሩ ነው። ቃል እንደሚተግን ሁሉ ” ሁለት ስለት ያለው ጎራዴ” ነውና ሞራል በሚነካ ደረጃ መዘላለፉ ቀጥሏል። ይህ አካሄድ ብዙ ጉዳያችንን እንዳያበላሽ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በትህነግ ፍቅር ያበዱትም ቢሆን ቢያንስ አየሩን፣ ንፋሱን፣ ጎርፉንና ውሽንፍሩን በመረዳት አካሄዳቸውን ሊገመግሙ ይገባል። ነጭ ሁሌም ካሸናፊ ጋር ነው። ከትግሬ ወይም ከአማራ ወይም ከኦሮሞ … የሚል ማህተም የላቸውም። ትናንት ” ውጡ” ሲሉ እንዳልነበር ዛሬ አፍረው ” ግቡ” እያሉ ነው። ይህን በማወቅ ለተረፈው ሕዝብ ቀጣይ ህይወትና ተስፋ ማሰብ ማስቀደም አግባብ ይሆናል።

ዘወትር እያማተቡ፣ “በስመ አብ በስመ ወልድ፣ በሰመ መንፈስ ቅዱስ ” ብለው ከህያው አምላክ የስድብ ባርኮትን ለምነው የሚያታልሉና ሕዝብን ከሕዝብ የምታነሳሱ የዪቲዩብ ሳንቲም ለቃሚ ነጋዴዎች፣ ሲቀዘቅዝ የአማራ ነጻ አውጪ መሪና አደራጅ፣ ሲፋጅ የአማራ ክልል መንግስት ደጋፊ መስላችሁ ጸብን የምትረጩ አይናቸሁን በጨው ያጠባችሁ ካድሬዎችም ቢበቃችሁ፣ ቢያንስ ለዚህ ምስኪን ህዝብ ስትሉ ብትጠግቡ፣ ልክ እንደ እናንተ ልጆች በየገተሩ ድሪቶ አሮባቸው ለሚታዩ ምስኪኖች ብታዝኑ፣ የምስኪን ደሃ ገበሬ ቤተሰቦችን ምስል እያሰራጫችሁ ንግድ ወዴት እየወሰደ መሆኑንን አትዘነጉትምና ምን አለበት ስራ ብትቀይሩ ….

በመጨረሻ ትህነግ ቁርጥ አቋም ያዝ። “ፍትህ ተጓደለብኝ” ካልክ፣ “ፍትህ አጓድለሃል” የሚሉህና ማስረጃ የሚያቀርቡበህ አካላት አሉና፣ ፍትህ እንዲበየንልህ ሳይሆን ባጠፋኸው መተን ፍትህ እንደሚበየንብህ በመረዳት የድሃ ልጆችን ከማስጨረስና ከነጮች አምኮ ተላቀቅ። መገንጠል መብትህ ነውና በህጋዊ መንገድ ከፍትህ መልስ ጠይቅ። ስልጣን ላይ በነበርክበት ሶስት አስርተ ዓመታት አፍነኸው የቆየኸው የውልቃይት ጠገዴ ጉዳይ በአገሪቱ ህግ መሰረት በህግ የሚወሰን ነውና ይህን አምነህ ተቀበል። አንተ የዛኔ ፍትህ ላይ ቆመህ ከምትደንስ ሕዝብ የሚለውን አድምጠህ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ይህ ሁሉ ባልሆነ ነበርና ዛሬ ከቁጭትና ቀረርቶ በመውጣት የህግን አግባብ ተከትለህ ተሟገት። ለማይሆን ጉዳይ በሃጢያት ላይ ሃጤያት አትደርብ። ህዝብ ነገ ዞሮ እንዳይገናኝ የዕርም ግምብ አትከምር።

እስከሚገባኝ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ በትህነግ ላይ ያላቸው አቋም አንድ ነው መባል የሚቻልበት ደረጃ ላይ ነው። እንደቀደመው ዓይነት የሚዲያና የፖለቲካ ድራማ ዛሬ መዝናኛ፣ የቲክ ቶክና ማህበራዊ ገጽ መቀለጃ ከመሆን የዘለለ ፍሬ አያስገኝምና ለመጪው ትውልድ የሚያስቡ የትግራይ ተወላጆች ሊነሱና ዘመኑንን ወደ ሚመጥን የመረጃ ልውውጥ ሊሸጋገሩ ይገባል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ነገሩ ” እንደው ባንገቴ” ሆኖ ይቀራል። ስለሆነም እንደ ሕዝብ አብሮ የቀሩ እንጥፍጣፊ ነገሮች ካሉ እነሱኑ አደርጅቶ አብሮ ለመቆየት እንዲቻል የነዚህ ሃይሎች መነሳት ግድ ነው። ድጋፍም ያሻቸዋል፣ መለያየትም ከሆነ በወጉ እዲሆን፣ ልክ ከኤርትራ ጋር እንደሆነው አይነት ሊሆን እንደማይችል ከወዲሁ በመረዳት በሰላም ለመሸኛኘት ቅድመ ዝግጅቱ በኮሚሽን ደረጃ ቢቋቋም። ጽህፈት ቤቱንም ትግራይ ቢያደርገና የትግበራ ስልት ነድፎ ቢንቀሳቀስ ይመረጣል። አስቀድሜ እንዳልኩት ሁለት አይነት ጨዋታ የሚፈቅድ አካል አይኖርምና ፍቺም ሆነ የኢትዮጵያን ህግና ደንብ አክብሮ መኖር በኩል ደረጃ ታይተው ቢተገበሩ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ሁሉም ያርፋል። የወደመበትም ይገነባል። ነጮቹም ቁማራቸውን አቁመው ትግራይን በመልሶ ግንባታ ለማገዝ ልዩ ፍላጎት ካላቸው የተሻለ አማራጭ ይሆንላቸዋል። ኢትዮጵያም የራስዋን ጉዳይ ከሚመስሏት ጋር ታራምዳለች። ስልጡን ትውልድ ሲመጣ በመነጋገር ግንቡ ሊፈርስ እንደሚችል በመገመትና በመመኘት እሰናበታለሁ። በቀጣይ ” እንዴት ይህን ያህል ወረራ ተፈጸመ” በሚለው ሙግት እመለሳለሁ።

ከአዘጋጁ – መምህር ፍቃዱ ዴሬሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከታታይ ጽሁፍ እያዘጋጁ ይልካሉ። ሃሳቡ እየሳቸው እንጂ የአዘጋጁን አመለካከት አይወክልም። ምላሽ መሳፍ ለሚፈልጉ መድረኩ ክፍት ነው


Leave a Reply