እንዳይደም፤ እንዳይራዘም !

“ በዚህ ወር ራስ አሊ ከጉና ተነስቶ በነፋስ መውጫ ሰፈረ፤ ክፋው እና ወሌ ቀርጨምን(የጦር አዛዦች?) ከብዙ ሰራዊት ጋራ ወደ ገረገራ ሰደዳቸው፤ በጋሸናም ሰፈሩ፤ በዚያም ከደጃዝማች ወልደገብርኤል ጋራ ተጋጠሙ፤ ደጃዝማች ወልደገብርኤል አሸነፋቸው፤ አንድ ሰው እንኳን ሳያስቀር (ፈጃቸው) “

Opinion by (በእውቀቱ ስዩም)

በሁለተኛው ያለም ጦርነት ጀርመን ኔዘርላንድን ወረረች:: ወራሪም ተወራሪም ነጭ ናቸው:: የሁለቱም አገሮች ካንድ ኩሬ የተቀዱ ቋንቋዎች ይናገራሉ:: ሂትለር ግድ አለው? ኔዘርላንድ በሰማይ በምድር አጣድፎ ጨመደዳት :: ለአራት አመታት ገደማ በቆየ የናዚ ጀርመን ጥጋብ የወለደው አገዛዝ ብዙ ሰዎች በጥይትና በረሀብ አለቁ ::

ከሰማንያ አመታት በሁዋላ አውሮፓ ውስጥ ራሴን አገኘሁት ፤ አንድ ቀን ኔዘርላንድ ውስጥ የሚኖረው ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተወልድ ቤቱ ምሳ ጋብዞኝ ሲያበቃ በመኪና ወደ ፍራንክፈርት (ጀርመን) ሸኘኝ ፤ ኔዘርላንድ እምታልቅበት፥ ጀርመን እምትጀምርበት ድንበር ላይ መድረሴን ሲነግረኝ የሰማሁትን ማመን አቃተኝ ፤ የግንብ አጥር የለ፤ ጠመንጃ የወደረ ወታደር የለ፤ ፍተሻ የለ፤ በቃ ከሳሎን ወደ ምኝታ ቤት ዘው ብሎ እንደ መግባት ነው:: የሰው ልጅ በዚህ ደረጃ መሻሻል ይችላል? አንድ ታዋቂ የታሪክ ጸሀፊ የሁለተኛው አለም ጦርነትን Inferno ብሎ ይገልጸዋል፤ ገሀነም እንደማለት ነው፤ በደረጀ መኪና ውስጥ ሆኘ የማካልላት አውሮፓ ግን ምድራዊ ገነት ነበረች፤ ተሰውሮ ቆይቶ ነው እንጂ ለካ ከገሀነም ወደ ገነት የሚያደርስ መንገድ አለ! ደነቀኝ!

አሜሪካን አገር ወዳጆቼ ሲናፍቁኝ ብቅ የምልበት ሰፈር እስክንድርያ ቨርጂኒያ ይባላል፤ የዛሬ መቶ ስድሳ አመት ገደማ እዚህ አካባቢ ቅልጥ ያለ ርስበርስ ጦርነት ነበር፤ ዛሬ አሜሪካኖች የጦርነት አራራ ሲነሳባቸው ወይም ጉልበታቸውን ማሳየት ሲያምራቸው ድንበራቸውን እያለፉ ባህር እየተሻገሩ የግፍ ጦርነት ላይ ይሳተፋሉ :: ብዙ ጊዜ ሳይቸግራቸው ጦርነት እየቀላወጡ ያልቃሉ፤ ጭምት ህዝብ ያሳብዳሉ፤ የሰከነ አገር ያደፈርሳሉ፤ ያም ሆኖ ርስበርስ ጦርነት በቤታቸው ዝር እንዳይል ማድረግ ተሳክቶላቸዋል:: አባቶቻቸው የተጋደሉበትን ቦታ ዛሬ ወደ ሚውዝየምነት ቀይረውታል፤ ይሄም ገረመኝ!

በኢትዮጵያ በታሪክ ጸሀፊዎች “ የመሳፍንት ዘመን” ተብሎ የሚጠራ ጊዜ ነበር፤ 1791 ገደማ ደጃዝማች ወልደገብርኤል የተባለ መስፍን፥ የጎንደርን ቤተመንግስት ለመግባት ከሚወዳደረው ራስ አሊጋዝ ከሚባለው የየጁ መስፍን ጋራ ተዋጋ ፤ 1791 -92 የጦርነቱን ውሎ የዘገበው የዘመኑ ጸሀፊ እንዲህ ይላል፤-
“ በዝ ወርኅ ተንስአ ራስ አሊጋዝ እምጉና ወሰፈረ በነፋስ መውጫ ወፈነዎሙ ለክፋው ወለወሌ ቀርጨም ምስለ ብዙኀ ሰራዊት መንገለ ገረገራ ወሰፈሩ በጋሸና ፤ ወበህየ ተጻብቡ ምስለ ደጃዝማች ወልደ ገብርኤል ወሞኦሙ፤ ለደጃዝማች ወልደገብርኤል ፥ወኢያትረፈ አሀደ ብእሲ “
ትርጉሙ-“ በዚህ ወር ራስ አሊ ከጉና ተነስቶ በነፋስ መውጫ ሰፈረ፤ ክፋው እና ወሌ ቀርጨምን(የጦር አዛዦች?) ከብዙ ሰራዊት ጋራ ወደ ገረገራ ሰደዳቸው፤ በጋሸናም ሰፈሩ፤ በዚያም ከደጃዝማች ወልደገብርኤል ጋራ ተጋጠሙ፤ ደጃዝማች ወልደገብርኤል አሸነፋቸው፤ አንድ ሰው እንኳን ሳያስቀር (ፈጃቸው) “

ይህ የርስበርስ ጦርነት ከተካሄደ ሁለት መቶ አመታት አልውታል፤ ቱፓክ ሻኩር ባንድ ዜማው But some things will never change ሲል የኛ ነገር ታይቶት ይሆን እላለሁ፤ የጦርነት ባህላችን አለመለወጡ ብቻ አይደለም የሚገርመው! ሁለቱ መሳፍንት ሰራዊት የተጋደሉባቸው “ ጉና፤ ነፋስ መውጫ፤ ገረገራ፥ ጋሸና “ የሚባሉት ስፍራዎች ዛሬም የጦርነት ውሎ ይዘገብባቸዋል፤ ምናልባት ለውጥ የሚባል ነገር ካለ፤ የጦር መሳርያው አይነት ሳይሆን አይቀርም፤ ነፍጥ በዲሽቃ ፤ ፈረስ በታንክ ናዳ ፤ በቦንብ ተተክቷል ::

የሆነ ዘመን ላይ ከሚጢጢ ሰላም በሁዋላ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ጦርነት ይከፈታል፤ አሸናፊው ለጥቂት ዘመናት ድሉን እያጣጣመ ይቀመጣል፤ ተሸናፊው ደግሞ ቁስሉን እየላሰ፥ የሚያንሰራራበትን ምቹ ጊዜ እየጠበቀ ያደፍጣል፤ እንዲህ ነው የኖርነው::

በቅርቡ፥ ምናልባት የጥቂት አመታት ሰላም እምናገኝ ከሆነ አንድ የቤት ስራ እንሰራበት! ያለፈው ጦርነት እንዳይደገም መላ ማፈላለጊያ እናድርገው፤ አገራችን በየርምጃው የምትንገዳገድበት ያስተዳደር ዘይቤ እንደገና ይመርመር! ክልሎች የተሳሰሩበት ውል በድጋሜ ይጤን! የግጭት መፍቻ እሴቶቻችን ለምን እንደከሸፉ እንጠይቅ፤ የሚለወጠው ይለወጥ ! የሚታደሰው ይታደስ!

Leave a Reply