ወደ አገር ቤት ለሚመጡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ተዘጋጅተዋል

ወደ አገር ቤት የሚመጡ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያዩበት መድረክ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ሌሊሴ ነሜ አስታወቁ።

ኮሚሽነሯ ባለፉት አራት ወራት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ሌሊሴ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጥሪ ወደ አገር ቤት የሚገቡ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያዩባቸው መድረኮች እየተዘጋጁ ነው።

መድረኮቹ በኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ያሉ አቅሞችን ማየት የሚያስችሉ እንደሆኑም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ዳያስፖራው መዋዕለ ንዋዩን ለማውጣትና በአገሩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሳተፍ ሲመጣ የሚስተናገድበት ራሱን የቻለ ዴስክ መክፈቱንም ገልጸዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው በመምጣት በአገር በቀል ኢንቨስትመንቶች ውስጥ እገዛ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል መኖሩንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ዳያስፖራው ያልተነኩ የአገሪቷን የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የውጭ ባለሃብቶችን ኢንቨስትመንቶችና ተያያዥ ስራዎች እንዲጎበኝ ይደረጋል ብለዋል።

ኮሚሽነር ሌሊሴ በተጨማሪም ወደ አገር ቤት ያልገቡ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በተለያዩ መንገዶች እያሳወቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለዚህ ስኬትም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከዳያስፖራ ኤጀንሲና ከክልሎች ኢንቨስትመንት ቢሮዎች ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሟትም በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት መጀመራቸውን ነው የገለጹት።

በአማራና በአፋር ክልሎች በነበረው ጦርነት ስራ አቁመው የነበሩ የኢንቨስትመንት መስኮችን በማስተባበር ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነር ሌሊሴ አስታውቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply