አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ «ነጻ በወጡ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ፣ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ ታዝዟል»

ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ የተሰጠ መግለጫ ቁ.6
ታኅሣሥ 14 ቀን 2014 ዓም

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ ማምሻውን ባደረገው ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አፈጻጸሙን ገምግሟል፡፡ በግምገማውም በግንባር ለተገኘው ድል የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ሞያቸውንና ገንዘባቸውን ለሀገራቸው ሳይሰስቱ በመስጠት የፈጸሙት የደጀንነት ገድል አኩሪ መሆኑን ተመልክቷል፡፡ ለዚህ የሕዝባችን ከፍተኛ አስተዋጽዖ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዙ ምስጋና ያቀርባል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዙ የተገኙ ድሎቻችንን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፣ ለዚህም በማኅበረሰቡ፣በአስተዳደር አካላትና በጸጥታ አካላት መወሰድ የሚገባቸውን ተግባራት በመለየት የሚከተሉትን ትእዛዛት ሰጥቷል፡፡

  1. ከሕዝብ ችግር ለመጠቀም የሚፈልጉ አንዳንድ አካላት፣ ወደ ሀገር ቤት የሚመጣውን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ምክንያት አድርገው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ መነሣሣታቸው ተደርሶበታል፡፡ ይህ ደግሞ ድኻውን የኀብረተሰብ ክፍል ስለሚጎዳ በእነዚህ ሕገ ወጥ አካላት ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ቁጥጥርና ሕግ የማስከበር ተግባር እያከናወነ ነው፡፡ በመሆኑም በየአካባቢው በመሠረታዊ ፍጆታዎችና አገልግሎቶች ላይ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ያለ አግባብ በሚያከማቹ አካላት ላይ፣ የንግድ ቢሮዎችና የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዝዘዋል፡፡
  2. ከአሸባሪው ሕወሐት ነጻ በወጡት አካባቢዎች አስተዳደርን መልሶ የማቋቋምና መሠረታዊ የኅብረተሰብ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ያለው እንቅስቃሴ ወጥ በሆነ ሁኔታ እየተተገበረ አለመሆኑን ገምግሟል፡፡ በዚህም ምክንያት የጸጥታ ችግሮችና የወንጀል ተግባራት ነጻ የወጣውን ማኅበረሰብ እያማረሩት ነው፡፡ በመሆኑም የአማራ ክልል መንግሥት የየአካባቢውን አስተዳደር በአስቸኳይ በብቁ አመራሮች እንዲያደራጅ፤ መደበኛ የፖሊስ ኃይሎችም የተጠናከረ ሥራ እንዲጀምሩ እንዲያደርግ፣ እነዚህን ለማድረግ ባልተቻለባቸው ቦታዎች የሚንቀሳቀስ የመከላከያ ኃይል፣ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ፣ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ ታዝዟል፡፡
  3. አሸባሪው ኃይል ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች፣ ባደራጃቸው ሕገ ወጥ መዋቅሮች አማካኝነት፤ የቀደመው አስተዳደር ይጠቀምባቸው የነበሩትን ማኅተሞች በመጠቀምና አዳዲስ ሕገ ወጥ ማኅተሞችን በመቅረጽ ሕገ ወጥ መታወቂያዎችን መስጠቱ፤ የተለያዩ ሕገ ወጥ ሰነዶችን ማዘጋጀቱ ተደርሶበታል፡፡ በመሆኑም በየአካባቢው የተቋቋሙ የመስተዳድር አካላትና የጸጥታ ኃይሎች አሸባሪው ሕወሐት ያስቀረጻቸውን ማኅተሞች፣ መታወቂያዎችና ሌሎች ሰነዶች እንዲያመክኑ ታዝዘዋል፡፡
  4. ነጻ በወጡ አካባቢዎች ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሮችና ጠላት አንጠባጥቧቸው የሄዱ የጦር መሣሪያዎች በመኖራቸው ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሥጋት ሊሆኑ የሚችሉ አዝማሚያዎች መኖራቸው ተደርሶበታል፡፡ በመሆኑም የየአካባቢው ልዩ ኃይልና ፖሊስ በአስቸኳይ እነዚህ ጉዳዮች ሥርዓት እንዲያሲዙ ታዝዘዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ባልተጠናከሩባቸው አካባቢዎችም የመከላከያ ኃይል አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ ተሰጥቷል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ

Leave a Reply