“…እኝህን ሴት የደፈሩት የ16 ዓመት ልጃቸውን በሌላ ክፍል ውስጥ በመዝጋት ነበር”

ዕድሜያቸው 50 ዓመት በላይ እንደሆኑ የሚገመቱት እናት አንድ 16 ዓመት ልጅ አላቸው።

ይህንኑ እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚሳሱለትን ልጃቸውን ለወግ ለማዕረግ ለማብቃት ደፋ ቀና ይሉ ነበር። 

ይኖሩበት በነበረው ሸዋ ሮቢት ከተማ በየሰው ቤት እየሄዱ እንጀራ እየጋገሩ፣ የተገኘውን የቀን ሥራ እየሰሩ ነበር ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሯቸውን የሚመሩት።

እኝህ እናት አሁን በሕይወት የሉም። ሲደክሙለት፣ ሲሳሱለት የነበረውን አንድ ፍሬ ልጃቸውን ጥለው ወደማይመለሱበት ዓለም ሄደዋል። አካሄዳቸው በርካቶችን ያሳዘነ ነበር።

ለፍተው የሚያድሩባት የሸዋ ሮቢት ከተማ በህወሓት አማጺያን ተይዛ በነበረበት ወቅት ነበር ሞት ያስመረጣቸው ድርጊት የተፈፀመባቸው።

አማጺያኑ ከተማዋን ለመቆጣጠር ሲቃረቡ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለማትረፍ ሰላም ነው ወዳሉት አካባቢ ሸሽተዋል። የቀሩት መሸሻና መጠጊያ የሌላቸው አሊያም የሚመጣውን እዚሁ ቀያችን ላይ እንጋፈጥ ያሉ ነበሩ።

እኝህ እናት ከልጃቸው ጋር ተከራይተው በሚኖሩበት ግቢ ውስጥ ብቻቸውን ቀርተዋል።

ኅዳር 11 ቀን ከተማዋ በህወሓት ኃይሎች እጅ ገባች። ከዚያ በኋላ ለ11 ቀናት ማለትም ከተማዋ ኅዳር 22/ 2014 ዓ.ም በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ተመልሳ እስከምትገባ ድረስ በእርሳቸው ላይም ሆነ በከተማ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደነበር የሚያወቅ አልነበረም።

የከተማዋ ፖሊስ ጽ/ቤት ተወካይ ኮማንደር አሕመድ መሐመድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እኝህ ለፍቶ አዳሪ እናት በቡድን በተፈፀመባቸው አስገድዶ መድፈር ሳቢያ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን የሰሙት በከተማዋ በሴቶች ላይ ስለተፈፀሙ ጥቃቶች መረጃ ሲያሰባስቡ ነበር።

ፖሊስ አገኘሁ ባለው መረጃ መሠረት አማጺያኑ እኝህን ሴት የደፈሩት የ16 ዓመት ልጃቸውን በሌላ ክፍል ውስጥ በመዝጋት ነበር።

“በቁጥር ስድስት የሚሆኑት ጥቃቱን ከፈጸሙባቸው በኋላ የልጄን ፊት እንዴት ብዬ አያለሁ፤ እሱስ የእኔን ፊት እንዴት ብሎ ያያል በማለት ገመድ ቋጥረው፤ የራሳቸውን ሕይወት በእጃቸው ነጥቀዋል” ብለዋል ኮማንደር አሕመድ ከልጃቸውና ከአካባቢው ነዋሪዎች አሰባሰብነው ያሉትን መረጃ ዋቢ አድርገው።

የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በከተማዋ በሚገኝ የሙስሊም መቃብር መፈፀሙን ኮማንደሩ አረጋግጠዋል። 

“ለፍተው ያሳደጉት የ16 ዓመት ልጃቸውም ‘ለነፍሴ ያለ ሰው’ አስጠግቶታል” ይላሉ። 

በተመሳሳይ የእድሜ ክልል ያሉ እናትን ጨምሮ በሌሎች ቀበሌዎች በሴቶች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሟል ያሉት ኮማንደሩ፤ ዝርዝር መረጃዎችን እያሰባሰቡ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራ እና አፋር ክልል ጥቃት በመክፈት ተቆጣጥረዋቸው በነበሩ አካባቢዎች በሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች እና ትንኮሳዎች መፈጸማቸው ተዘግቧል። 

ድርጊቱ ከተፈፀመባቸው ሴቶች መካከል ከ18 ዓመት በታች ያሉ ህጻናትም እንደሚገኙበት ክልሉ ያወጣው መረጃ ያሳያል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አስናቁ ደረስ፣ ህወሓት ተቆጣጥሯቸው በነበሩና በተለቀቁ አካባቢዎች “አሰቃቂ የመድፈር ጥቃቶች” መፈጸማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢሮው በክልሉ ሦስት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች በአካል ተገኝቶ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን የገለጹት ኃላፊዋ በርካቶች “በተፈጸመባቸው ጾታዊ ጥቃት ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥፍተዋል፤ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ያብራራሉ። 

ኃላፊዋ እንዳሉት የዳሰሳ ጥናቱ ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የተካሄደ ሲሆን በሰሜን ጎንደር ደባርቅ እና ዳባት ዙሪያ፣ በደቡብ ጎንደር ታች ጋይንት፣ ላይ ጋይንት እና ነፋስ መውጫ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በሴቶች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተመልክቷል።

በእነዚህ አካባቢዎች ብቻ 147 ሴቶች የመድፈር ጥቃት እንደተፈጸመባቸውና 116 የሚሆኑትን በአካል አግኝተው ለማነጋገር እንደተቻለ ወ/ሮ አስናቁ ይገልጻሉ። ከእነዚህ መካከል 19ኙ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ከ12 እስከ 80ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ መሆናቸውንም በዳሰሳ ጥናቱ ማወቅ ተችሏል ይላሉ ኃላፊዋ።

የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ከደኅንነትም ሆነ ከህክምና ሥነ ምግባር አንጻር አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽም በአካባቢዎቹ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። 

“ከተደፈሩት መካከል ነፍሰ ጡር ሴቶች ይገኙበታል” 

ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የሆነው የነፋስ መውጫ ከተማ በርካታ ተጎጂዎች ሪፖርት የተደረገበት ነው። 

የህወሓት ኃይሎች በከተማው ነሐሴ 06/2013 ዓ.ም የገቡ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ቆይተዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሙላው ጤናው ለቢቢሲ እንደገለፁት በነፋስ መውጫ ከተማ ብቻ 73 ሴቶች የመድፈር ጥቃት የተፈጸመባቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል አራቱ እናቶች፣ ሁለቱ ደግሞ ነፍሰ ጡር ናቸው።

“እነዚህ እንደተደፈሩ ራሳቸው መረጃ የሰጡ ናቸው” ያሉት ከንቲባው፤ ራሳቸውን የደበቁ ስለሚኖሩ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል ሲሉ ያክላሉ። 

ሪፖርት ካደረጉት 73 ሴቶች መካከል 28 የሚሆኑት በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን የገለጹት አቶ ሙላው፣ በውጭ አገር ከሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ጋር በመተባበር ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች መካከል “በተደረገላቸው ምርመራ ሁለቱ የኤችአይቪ ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን፤ አንዷ ደግሞ ለአዕምሮ ጤና ችግር ተዳርጋለች” ብለዋል።

ባለፈው ወር ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት በነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪ የሆኑና ያናገራቸው 16 ሴቶች በህወሓት አማጺያን የመደፈር ጥቃት እንደተፈፀመባቸው አመልክቷል።

እነዚህ ሴቶች በህወሓት ኃይሎች መሳሪያ ተደቅኖባቸው እንደተደፈሩ፣ ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው እንዲሁም አካላዊ ጥቃት እና ስድብ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ካነጋገራቸው የመድፈር ጥቃት ከተፈጸመባቸው አስራ ስድስት ሴቶች መካከል 14ቱ ጥቃቱ በቡድን እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል።የህወሓት አማጺያን በደቡብ ጎንደር የመድፈር ጥቃቶች መፈጸማቸውን አምነስቲ አመለከተ 

የዳሰሳ ጥናቱ ባልሸፈናቸው አካባቢዎችም በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት መፈጸሙ ተዘግቧል።

የህወሓት ኃይሎች ከነሐሴ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ መስከረም 1/2014 ዓ.ም ድረስ በቆዩበት መቄት ወረዳ የመድፈር ጥቃት መፈጸማቸውን የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። 

በወረዳው የፍላቂት ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ይበልጣል ጌታ አካባቢው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በህወሓት ኃይሎች የተደፈሩ ሴቶች በሆስፒታሉ መታከማቸውን ገልጸዋል።

“ስምንት ሴቶች የአስገድዶ መደፈር ደርሶባቸው በፍላቂት ሆስፒታል ሕክምና ተደርጎላቸዋል” የሚሉት አቶ ይበልጣል፣ በዚሁ ወረዳ “ሦስት ሴቶች ደግሞ አስገድዶ መድፈር ከተፈጸመባቸው በኋላ ሕይወታቸው አልፏል” ብለዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በተለያየ የእድሜ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን በመጥቀስ “የካህናት ሚስቶች” ሳይቀሩ የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውንም አቶ ይበልጣል ተናግረዋል። 

አቶ ይበልጣል “እስካሁን ባለን መረጃ በወረዳው በአጠቃላይ 32 ሴቶች የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። ቁጥሩ ግን ከዚህም ሊበልጥ ይችላል” ብለዋል። 

ህወሓት በተዋጊዎቹ ተፈጽመዋል ስለተባለው ጥቃት በዝርዝር ያለው ነገር ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት ላይ ጥያቄ እንዳለው ገልጾ፤ ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል። 

“ለፊስቱላ እና ለአዕምሮ ሕመም የተጋለጡ አሉ”

ወ/ሮ አስናቁ ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች ለአካላዊ ጉዳት እና ለከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግር ተዳርገው እንዳገኟቸው ተናግረዋል።

በዳሰሳ ጥናቱ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ከተመለከቱት 147 ሴቶች 21ዱ የከፋ ችግር አጋጥሟቸው ሆስፒታል መግባታቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል 18ቱ ሕክምና ተደርጎላቸው በአካባቢያቸው በሚገኝ የጤና ተቋም ክትትል እንዲያደርጉ ተነግሯቸው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል።

ለከፋ የአካል ጉዳት የተዳረጉ ህጻናትን ጨምሮ አምስት ሴቶች ግን አሁንም በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ ወ/ሮ አስናቁ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አብዛኞቹ ሴቶች የተደፈሩት በቡድን ነው ያሉት ኃላፊዋ ለፊስቱላ የተጋለጡ እንዳሉም ተናግረዋል። 

ለፊስቱላ ከተጋለጡ መካከል በሰሜን ጎንደር ጭና አካባቢ የተደፈረች ህጻን እንደምትገኝበት ኃላፊዋ አስረድተዋል።

“በትክክል መረጃ አላገኘንም እንጂ ላልተፈለገ እርግዝና እና ለተላላፊ በሽታ የተጋለጡ እንዳሉ ሰምተናል” ሲሉም አክለዋል።

ፊስቱላ በተራዘመ ምጥ፣ በመደፈር፣ በያለእድሜ ጋብቻ ሳቢያ በሁለት የሰውነት ክፍሎች መካከል፣ ውስጣዊ ክፍልና ውጫዊ ክፍል፣ የሚፈጠር ቀዳዳ ነው። 

ለፊስቱላ የተጋለጡ ሴቶች ሽንትና ሰገራቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው ለተለያዩ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች ይዳረጋሉ።

ከዚህም ባሻገር አብዛኞቹ ሴቶች ጥቃቱ የተፈፀመባቸው በልጆቻቸው፣ በባለቤታቸው፣ በቤተሰብ አባላቸው ፊት በመሆኑ የሥነ ልቦና ጉዳቱ የከፋ መሆኑን አስረድተዋል።

“በሸዋ ሮቢት ራሳቸውን እስከማጥፋት የደረሱት እናትም ‘የልጄን ፊት እንዴት አያለሁ’ ብለው ነው” ሲሉም ኃላፊዋ ምሳሌ ጠቅሰዋል።

እንዲያገግሙ ምን እየተሰራ ነው?

ጦርነት ጥሏቸው ከሚያልፉ ጠባሳዎች መካከል አንዱ በህጻናትና በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ነው።

ለተጎጂዎቹ ተገቢ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች ስለማይኖሩ ብዙዎች ጉዳታቸውን አምቀው ይዘው እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ይቆያሉ።

ሲከፋም በደረሰባቸው በደል ይህችን ምድር ተጠይፈው እድሜያቸውን በራሳቸው እጅ የሚያሳጥሩም አሉ።

ከሥነ ልቦናው ጉዳት ባሻገርም ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች፣ ላልተፈለገ እርግዝና ተዳርገው ሕይወታቸው ይመሳቀላል። 

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለአደጋ ለተጋለጡ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ከማቅረብ ባሻገር የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን የመደገፍ ሥራ በበቂ ትኩረት እንዳላኘ ይጠቅሳሉ።

ወ/ሮ አስናቁ በአካባቢዎቹ የጤና ተቋማት በመውደማቸውና በአማጺያኑ ቁጥጥር ሥር ስለነበሩ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች በጊዜው መድረስ አለመቻሉን ተናግረዋል። 

ይሁን እንጂ አካባቢዎቹ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ የከፋ የጤና ችግር አጋጥሟቸው ወደ ሕክምና ተቋም ሄደው ካገኟቸው 116 ሴቶች መካከል 114 ለሚሆኑት ከሦስት እስከ አምስት ቀናት የዘለቀ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በቅርብ ባሉ ባለሙያዎች የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊዋ “ለጊዜው ይህንን የጤና ተቋማት እንዲሰሩ ትኩረት አድርገን እንሰራለን” በማለት ተናግረዋል።

በሴቶቹ ላይ ከጾታዊ ጥቃት ባሻገር ንብረታቸው የተዘረፈባቸውም እንዳሉ በማንሳትም የገንዘብና የዓይነት ድጋፎችን መደረጉን ኃላፊዋ አክለዋል።

Source BBC Amharic

Leave a Reply