አሸባሪ ቡድኑ በአማራና በአፋር የፈጸማቸውን ወንጀሎች የሚያጣራ ግብረ ኃይል ሥራውን ጀመረ

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በወረራ ገብቶ የፈጸማቸውን አሰቃቂና ዘግናኝ የወንጀል ድርጊቶችን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩን የፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ዳይሬክተር አቶ አወል ሡልጣን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሽብር ቡድኑ በለቀቃቸውና በወረራ ገብቶባቸው በነበሩ የአፋርና የአማራ ክልሎች ተንቀሳቅሶ የሚሠራ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ የምርመራ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ደረጃውን የጠበቀ፣ ገለልተኛና የወንጀል ድርጊቱን ይዘትና ስፋት ሊያሳይ የሚችል ዐቃቤ ሕጎችና ፖሊሶች በተለቀቁ አካባቢዎች ተገኝተው ምርመራ እያደረጉ ይገኛሉ፤ ከወንጀል ድርጊቱ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸውን ለማስረጃነት የሚጠቅሙ ግብአቶችን በማሰባሰብ ሰፊ የምርመራ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ ከፌዴራል ፖሊስና ከክልሎቹ የፍትህ ተቋማት ጋር የተቀናጀው የምርመራ ቡድኑ በጋራ ምርመራውን እያከናወነ የሚገኘው በደቡብ ወሎና በሰሜን ወሎ አካባቢዎች፣ በአፋር የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ በመገኘት ነው።

አንዳንዶቹ ወንጀሎች ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የሆኑ፣ በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚቀርቡና ዓለም አቀፍ ድንጋጌን የጣሱ፤ የዘር ጭፍጨፋ፣ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች በመሆናቸው ምርመራው ዓለም አቀፍ መሥፈርትን ያሟላ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

ምርመራው ዓለም አቀፍ መሥፈርትን ማሟላቱ ወንጀለኞቹ በየትም አካባቢ ቢገኙም ለማስቀጣት በሚያስችል ሁኔታ የማስረጃ ማሰባሰብ ሥራ እንዲሠራ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች በወረራ በመግባት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ሲያደርስ መቆየቱን አስታውሰው፤ ሰዎች ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑንና አሰቃቂ ወንጀሎችን ሲፈጽም መቆየቱንም አመልክተዋል።

ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ውጪ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጭምር ኢላማ በማድረግ ጥቃት ሲፈጽም እንደነበረ፤ ያስታወሱት አቶ አወል አሸባሪ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ሕግ ከተከለከሉ ተግባራት መካከል ንጹሃንን፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎችን እንዲሁም ሰላማዊ ሰዎች የሚገለገሉባቸውን ተቋማት ጨምሮ የጥቃት ኢላማ አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሸባሪ ኃይሉ የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ከመውጣቱ በፊትም በክልሉ ማይካድራን ጨምሮ በአማራ ክልል አጎራባች ወረዳዎች በርካታ ወንጀሎችን ሲፈጽም ነበር። በእነዚህ ቦታዎች የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን የተውጣጡ ባለሙያዎች በቦታው ተገኝተው የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ምርመራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply