ዳኛው በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በማግለያ ክፍል እንዲቆዩ በመደራገቸው ምክንያት በእነ ጌታቸው አሰፋ ክስ መዝገብ ላይ ሊሰጥ የነበረው ብይን ለሌላ ጊዜ ተሸጋገረ
በእነ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ ላይ ዳኞች ተሟልተው ባለመገኘታቸው ምክንያት ተከሳሾች ባነሱት የዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።
በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ያሬድ ዘሪሁንና ሌሎች 24 ተከሳሾች ላይ እንደየጥፋተቸው በፈፀሙት ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠ መሆኑ ይታወቃል ።
ሆኖም ተከሳሾቹ በዋስ ወጥተን ክሳችን አንከታተል ብለው ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ዐቃቤ ህግ ዋስትናውን በፅሁፍ መልስ ልስጥበት በማለቱ ምክንያት ለታህሳስ 06/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ በዚሁ ተለዋጭ ቀጠሮ ዐቃቤ ህግ በዋስትና ጥያቄው ላይ የፅሁፍ መልስ መስጠቱ የሚታወስ ነው ።
አንደኛው የችሎት ዳኛ በገጠማቸው የግል ችግር ምክንያት ባለመገኛታቸው ችሎቱ ለታህሳስ 12/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ቢሰጥም አንደኛው ዳኛ ከዚህ በፊት በተከሳሾች ላይ በተሰጠው ብይንና ፍርድ ላይ አብዛኞቹን ቢስማሙበትም 5ኛ ክስን በተመለከተ በ2ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ላይ በአብላጫ ድምፅ ተበልጠው በልዩነት ያልተስማሙ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል። ስለሆነም በችሎቱ ይህ ዳኛ ባልተስማማሁበት ክስ ላይ ብይን ልሰጥ አልችልም በማለታቸው ጉዳዩን መርምሮና አይቶ ብይን መስጠት እንዲቻል ለታህሳስ 19/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደነበር መግለጻችን የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና በዚህም ቀጠሮ ከችሎቱ ዳኞች መካከል አንዱ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በማግለያ ክፍል እንዲቆዩ በመደራገቸው እና ችሎቱን በአንድ ዳኛ ብቻ ማስኬድ የማይቻል መሆኑን በመግለጽ በችሎቱ የተገኙት የችሎቱ መሐል ዳኛ መዝገቡን ለታህሳስ 27/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተውበታል።