እንደ ባህሪው መፍትሄውም የተለያየው የሃገራችን የፖለቲካ ችግር


(ፍቱን ታደሠ – opinion )

ጥቂት የፖለቲካ ቡድኖች የ110 ሚሊዮን ህዝቦችን ሃገር ለማፍረስ ነፍጥ አንስተው በመታገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን የፖለቲካ ቡድኖች የሚያመሳስላቸው ነገር ከቀላል እስከከባድ መሳሪያ ታጥቀው የሚዘምቱት በሰላማዊ ህዝብ ላይ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ አርሶአደሮች፣ ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን የእነዚህ ቡድኖች የግድያ ኢላማ ናቸው፡፡ የትግራይ ወራሪ ኃይል በይፋ ጦርነት ከመጀመሩም በፊት በወለጋና በቤንሻንጉል ዘግናኝ የሆኑ የዘር ማጥፋት (Genocide) ጭፍጨፋዎች ሲካሄዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ጭፍጨፋው ትንሽ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ደግሞ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ንፁሃን የሚገደሉት በዘራቸው ምክንያት ነው፡፡

የትግራይ ወራሪ ኃይል የከፈተው ጦርነትም ሆነ የኦነግ ሸኔ እና የቤንሻንጉል ታጣቂዎች በንጹሃን ላይ እያደረሱት ያለው ጭፍጨፋ መቆም ይኖርበታል፡፡ ወያኔ ሲደመሰስ በወለጋና በቤንሻንጉል ክልል ያለው ችግርም ከወያኔ ጋር አብሮ ይከስማል የሚል መሬት ላይ ያለውን እውነታ የማይገልጽ ትንታኔ ሲሰጥ እንሰማለን፡፡ የወያኔ ጉዳይ ከእነዚህ ፍጹም የተለየ ነው፡፡ የወያኔ አላማ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ታላቅ የሚላትን የትግራይ መንግስት መመስረት ነው፡፡ ይህንን ቅዠቱን እውን ለማድረግ የመንግስትን አቅም ለማዳከም ይጠቅሙኛል የሚላቸውን ነፍጥ ያነሱ እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ ተቃዋሚዎችን በፋይናስና የጦር መሳሪያ በማቅረብ መንግስትን እረፍት እንዲነሱለት ያደርጋል፡፡ ወያኔን በማጥፋት እነዚህ ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ ግን ፖለቲካውን በአግባቡ አለመረዳታችንን ያሳያል፡፡ በወለጋና በቤንሻንጉል ላለው ችግር ጉዳዩን በአግባቡ በማጤን ፖለቲካዊ መፍትሄ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያን ዘላቂ ሠላምና የህዝቦቿን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚቻለው በዋናነት ሃገራችንን አፍርሶ ህዝቦቿን የመበተን አላማ ይዞ ጦርነት የከፈተብንን የትግሬ ወራሪ ኃይል የውጊያ አቅሙን አንኮታኩቶ መቅበር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ቡድን አላማው ኢትዮጵያን አጥፍቶ በፍርስራሹ ላይ የራሱ ቅዠት የሆነችውን ታላቋን ትግራይ መገንባት ስለሆነ መቼም ቢሆን ይህንን አላማውን ለማሳካት እየወደቀ እየተነሳም አገራችንን እረፍት መንሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ እንዲህ ያለ አጥፊ አላማ ካለው ቡድን ጋር አሁን በሚገኝበት ሁኔታ ወደ ድርድር መግባት ለወራሪው ቡድን መታረጃ ቢላ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው፡፡ ወራሪው ኃይል በአሁኑ ወቅት ድርድር እጠየቀ ነው፡፡ የአማራና የአፋር ክልሎችን በወረራ ይዘው ደብረሲና በደረሱ ጊዜ የወራሪው ቡድን የጦር መሪ ሌተናል ጄነራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ “አሸንፈናል፤ ጦርነቱ አልቋል ከማን ጋር ነው የምንደራደረው? ከዚህ በኋላ ድርድር አይኖርም፡፡” በማለት ሲመፃደቅ እንዳልነበረ ዛሬ ደግሞ አከርካሪው ተመትቶ ተምቤን ዋሻ ሲወሸቅ የድርድር ጥያቄ ማንሳት ጀምሯል፡፡

በርግጥ የሁሉም ጦርነቶች ማብቂያ ድርድር ነው፡፡ ድርድር ግን ጦርነት ቀስቃሹ ቡድን በውጊያ ሲሸነፍ ጌዜ ወስዶና አቅሙን አደርጅቶ ዳግም አንሰራርቶ እንዲነሳ የሚያደርግ መሆን የለበትም፡፡ በአለም ላይ በርካታ ወረራም ሆነ ግጭቶች በድርድር ስም ተሸፋፍነው እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ዳግም ጦርነት ያገረሸበትና የሚሊዮኖችን ህይወት የቀጠፈበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የጦርነቱ ቀስቃሽ የነበረችው ጀርመን የጠላቶቿ ኃይል አመዝኖ በጦርነቱ ስትሸነፍ ተኩስ አቁማ የድርድር ጥያቄ አነሳች፡፡ በድርድሩም የተደራዳሪዎቹን ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ እራሷን ለሰላም ተገዢ አስመስላ በመቅረቧ ጦርነቱ አለቀ ተብሎ ሁሉም አገራት ሠላማዊ ኑሯቸውን ሲጀምሩ ጀርመን ግን አላማዋ የሆነውን የአርያን ዘር የበላይነት ለማስፈንና ከአለም ላይ መወገድ አለባቸው ብላ በምታስባቸው ህዝቦች ላይ ደግሞ ጄኖሳይድ ለመፈፀም የሚያስችላትን የጦር ዝግጅት ማድረግ ጀመረች፡፡ ጊዜው ሲደርስ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ቀሰቀሰች፡፡ ጀርመን በድርድር ስም አድፍጣ 6 ሚሊዮን አይሁዶችን ጨምሮ 85 ሚሊዮን ህዝብ ያለቀበትና ዓለምን ያወደመ ጦርነት በመክፈቷ ቁጭት ያደረባቸው የዓለም አገራት ዘረኛዋንና ወራሪዋን ጀርመን በጦርነት አከርካሪዋን ሰብረው ካንበረከኳት በኋላ ጀርመንን በድርድር ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ እንድትታገድ አድርገዋታል፡፡
የትግሬ ወራሪ ኃይልም አላማው ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁን በድርድር ፋታ ካገኘ ዳግም አቅሙን አደራጅቶ ከዛሬው የከፋ ጥፋት ከማድረስ አይመለስም፡፡ ስለዚህ ወራሪውን ኃይል የገባበት ቦታ ገብቶ መደምሰሱ ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ በአማራና በአፋር ክልል የተደመሰሰው፣ የተማረከውና በህይወት ተርፎ ወደ ትግራይ የሸሸው የወያኔ ተዋጊ ኃይል ቁጥሩ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ወታደራዊ ባለሙያዎች ያውቁታል ተብሎ ያታመናል፡፡ ምክንያቱም በጦርነት አሸናፊ ለመሆን ጠላት ያሠማራውን የሰው ኃይልና የጦር መሣሪያ አይነትና መጠን ማወቅ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡

በዚህ መሠረት ወያኔ ትግራይ ውስጥ አሁን ያለው የሰው ሃይልና መሣሪያ ከእኛ የጦር መሪዎች የተሰወረ አይሆንም፡፡ አመራሮቹም ቢሆኑ ሠራዊታቸው መሸሽ ሲጀምር እነሱም መቀሌን ለቀው ለክፉ ጊዜ ወዳዘጋጇቸው ዋሻዎች እንደሚሸሹ እሙን ነው፡፡ አሁን ባለው ተነሳሽነትና ቁጭት ሠራዊታችን እነዚህን ወንበዴዎች ቀብሮ ውጊያውን ለማጠናቀቅ ጊዜ የሚወስድበት አይሆንም፡፡ የወያኔ አስተሳሰብ ግን ከ30 ዓመታት በላይ ህዝቡ ውስጥ የተረጨ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ የተቋረጡት የመሰረተ ልማት አውታሮች ተለቀው ከጦርነት ነጻ በሆነ ሁኔታ ከትግራይ ህዝብ ጋር ምክክርና ድርድር ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡
በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ክልሎች ግን ከአባ ገዳዎችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚጠየቁት ተለይተው ለፍርድ እንዲቀርቡና ታጣቂዎችም ትጥቃቸውን ፈተው ለድርድር የሚቀመጡበት ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊቀርብ ይገባል፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄው በማንነታቸው ምክንያት ተወልደው ካደጉበትና ንብረት ካፈሩበት አካባቢ ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያው የሚገኙትን ዜጎችም ዋስትና የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል፡፡

Leave a Reply