ዛሬ ግን የደስታ ቀናችን ነው…

አብርሆትን ለአብርሆት

ድሮ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንቀላለድ “ለእኔ ብር ሰጥተህ መጻሕፍት ባሉበት በኩል እንዳትልከኝ” እለው ነበር:: ከመጻሕፍት ፍቅር የተነሳ ነው:: ከመጻሕፍት የተጣበቅን ሰዎች እኛ ያላነበብነው መጽሐፍ ስናይ የራበው ሰው ምግብ ሲያይ እንደሚሆነው እንሆናለን:: አያድርስ ነው!

ዛሬ ግን የደስታ ቀናችን ነው… ለአንባቢያን እና አንባቢ መሆን ለሚሹ ሁሉ!

የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ እያለሁ አዘውትረን ወደ ወመዘክር ከወዳጆቼ ጋር እንሄድ ነበር:: ለላፕቶፕ መሰኪያ ለማግኘት ጠዋት መሄድ ግድ ይላል – እርሱ ካልሆነ ቦታ ሁሉ ተይዞ ማከፋፈያ ፍለጋ መዞር ነው:: የአማርኛ መጻሕፍት ማንበቢያው ደግሞ ያናድደን ነበር:: ከሚገኘው መጻሕፍት የለም የሚባለው ይበልጣል:: በዚያ ላይ ያለውንም ለመጠቀም ችግር ነበር:: አንድ መጽሐፍ ጀምረን ‘ነገ እንቀጥለዋለን’ ብለን አስቀምጠን እንሄዳለን… በማግስቱ ከቦታው የለም:: ምን ሆነ? አንዱ ሌላ እርሱ ብቻ የሚያውቀው ቦታ ደብቆት ሄዷል! ለምን ይደብቃል? መጻሕፍቱ ውሱን ስለሆኑ እና ነገ ሌላው እንዳይቀድመው ስለሚሰጋ:: አናሳዝንም ወይ?

ከዚህ ሁሉ ጉድለት ጋርም ቢሆን ግን የምንወዳት ቤተመጻሕፍት ናት! ዛሬ በተለምዶ “ወመዘክር” የምንላት ባለውለታችን እፎይ ልትል ነው:: እነሆ አብርሆት ቤተመጻሕፍት ሊመረቅ ነው!

አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት 1.15 ቢሊዮን ብር ፈስሶበት በተንጣለለ ሰፊ ቦታ ላይ የሰፈረ ኢንተርናሽናል ጥራቱን የጠበቀ ላይብረሪ ነው:: አቅሙም አስደማሚ እንደሆን እየተነገረ ነው:: 1.4 ሚሊዮን ገደማ መጻሕፍት አሉት… ይህም 240,000 በላይ በስስ ቅጂ የተዘጋጁትን እና 300,000 የሚጠጉትን ጥናታዊ ጽሑፎች ሳይጨምር ነው:: የብሬል መጻሕፍት ክምችትንም ለዓይነ ስውራን አንባቢያን ይዟል::

በአንድ ጊዜ ከ 2000 በላይ አንባቢያን የሚያስተናግድ ሲሆን ስምንት የመጻሕፍት መሸጫ ሱቆች ፣ የስብሰባ አዳራሽ ፣ ካፍቴሪያ እና የተለየ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች የሚያነቡበት የመጽሐፍ ክፍልም አካቷል!

በውጭ ሀገራት የምንቀናባቸውን አይነት ቤተ-መጻሕፍትን እውን ለማድረግ ከአሳብ ማመንጨት አንስቶ በየደረጃው በግንባታ ሒደቱ ለተሳተፋችሁ ሁሉ የላቀ ምስጋና ይድረሳችሁ! አብርሆት ለሀገራችን አብርሆትን የሚያመጣ ትውልድ ሲያፈራ ያሳያችሁ!

✒️ Fresenbet G.Y Adhanom

Leave a Reply