በሮቢት 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙ 20 የተናጠልና የጅምላ መቃብሮች ተገኙ

በራያ ቆቦ ወረዳ በሮቢት ከተማ በሮቢት 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የተፈጸሙ 20 የተናጠልና የጅምላ መቃብሮች ተገኙ። አሸባሪው ቡድን ትምህርት ቤቱን የጦር ካምፕ፣ ምሽግና የመቃብር ስፍራ አድርጎታል።

የሮቢት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጥበቃ ሠራተኞች አቶ ይመር አየለ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች ቡድን እንደገለፁት አሸባሪው ቡድን ሮቢት ከገባበት ሐምሌ 20 ጀምሮ ትምህርት ቤቱ የጦር መሪዎቹ ማዘዣ ካምፕ፣ የሕክምና ማዕከልና የቀብር ስፍራ አድርጎ ሲገለገልበት ቆይቷል፡፡

በሦስት ሥፍራዎች ከ20 በላይ የጅምላና የተናጠል ቀብሮችን ፈጽሟል፡፡ የሽብር ቡድኑ በትምህርት ቤቱ ላይ የቤተ ሙከራ ቁሳቁሶች፣ ኮምፒውተሮች፣ ፕላዝማዎች፣ የተማሪ ሰነዶችና ንብረቶችንም አውድሟል።

ትምህርት ቤት የልጆች አዕምሮ የሚታነጽበት እንጂ የመቃብር ስፍራ አይደለም የሚሉት አቶ ይመር፤ አሸባሪው ቡድን ግን ትውልድን በእውቀት የሚያንጸውን ትምህርት ቤት የመቃብር ስፍራ አድርጎት ለኢትዮጵያም፣ ለትውልድም ያለውን ጥላቻና ገዳይነት አሳይቷል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊ ሥነልቡና ቢኖራቸው ልጆች የሚያድጉበትን፣ ወጣቶች የሚለወጡበትን ትምህርት ቤት ወደ መቃብር ስፍራ አይለውጡትም ነበር ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን በሄደበት ሁሉ ትምህርት ቤቶችን የሚያፈርሰው፣ የሚዘርፈው፣ የጦር ካምፕና የመቃብር ስፍራ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ትውልድ እንዳይማርባት፣ አገር የሚያሳድግ ሳይሆን አገር የሚያፈርስ ዜጋ እንዲፈጠርባት፣ የወጣቱን ትምህርት የመማር ቅስም ለመስበር ያለመ ተግባር ነው የፈፀሙት።

ኢትዮጵያውያንን ሊለያዩና ሊያንበረከኩ ሳይሆን የበለጠ ለአንድነታቸውና ለተሻለ እድገታቸው እንዲተባበሩ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ ህብረተሰቡም ይሄን ተገንዝቦ አሸባሪ ቡድኑን ማጥፋትና የተሻለ አንድነቱን ማጠናከር ይኖርበታል፡፡

የሽብር ቡድኑ በትምህርት ቤቱ ጊቢ ውስጥ የፈጸመው ተግባር ሰቅጣጭና ከሰው ልጅ የማይጠበቅ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱን ወታደራዊ ካምፕ አድርጎ ተጠቅሞታል፡፡ ከካምፕነት ባለፈ የተዋጊዎቹ የሕክምና ማዕከል አድርጎት ስለነበር፤ የሚሞቱበትን በዚሁ ጊቢ ውስጥ ቀብሯቸዋል፡፡ ከሌሎች አከባቢ የሚያመጣቸውን አስከሬኖችም ጭምር በዚሁ ቀብሯል፡፡

የሽብር ቡድኑ የትምህርት ቤቱን ንብረትና ለመማር ማስተማሩ አጋዥ የሆኑ ቁሳቁሶችን መዝርፏል፣ ትምህርት ቤቱንም የመቃብር ስፋራ ማድረጉ ትምህርት ቤቱ ለአከባቢው ህብረተሰብ አገልግሎት እንዳየስጥ ለማድረግ ያለውን ክፉ ምኞት ያሳየበት መሆኑን የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ጀማል አመረ ተናግረዋል።

ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ተገቢው የስነልቡና ምክር ሊደረግላቸው እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

በወንድወሰን ሽመልስ ሮቢት (ኢ ፕ ድ )

Leave a Reply