በጦርነቱ ምክንያት ከ8 ሺህ በላይ ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ተጠፋፍተዋል

 ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው በአሸባሪው ቡድንና በፌደራል መንግስት መካከል ባለው ጦርነት ሳቢያ  8 ሺህ 419 ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር መጠፋፋታቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ያመላከተ ሲሆን እስካሁን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተገናኙት ዘጠኝ በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።

አስቀድሞ የጦርነቱ ቀጠና በነበረው የትግራይ ክልል 7 ሺህ 165 ህጻናት ከነቤተሰቦቻቸው መጠፋፋታቸውን ኋላም ጦርነቱ በተስፋፋባቸው አማራ ክልል 1 ሺህ 215 እንዲሁም በአፋር 39 ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው የተጠፋፉ ህጻናት መመዝገባቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።ከእነዚህ ህጻናት መካከል በትግራይ 331፣ በአማራ 397 ያህሉ በቀይ መስቀልና በሌሎች ተቋማት ትብብር ከቤተሰቦቻቸው የተገናኙ ሲሆን በአፋር ህጻናቱ እስካሁን ቤተሰባቸውን  ማግኘት  አልቻሉም።

ከቤተሰቦቻቸው ከተጠፋፉት ህጻናት መካከል 4 ሺህ 311 ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ የአብዛኞቹ እድሜም ከ10 አመት በታች ነው ብሏል- ሪፖርቱ።ወደ ቤተሰቦቻቸው ከተቀላቀሉ ህጻናት መካከልም 387ቱ ሴቶች ሲሆኑ አሁንም ከቤተሰቦቻቸው ለመገናኘት በተለያዩ መጠለያ ማዕከላት ሆነው ከሚጠባበቁት መካከል 2580 ያህሉ ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል።
ህጻናቱን ከቤተሰቦቻቸው ለማገናኘት  የሚደረገው  ጥረት  ተጠናክሮ መቀጠሉን ነገር ግን አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ጦርነቱ የቀጠለ መሆኑ ሂደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ህጻናቱ በየሚገኙባቸው ማእከላት ከሚደረግላቸው ሰብአዊ ድጋፍ ባለፈ የስነልቦና ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸውም ተጠቁሟል። via addis admass


Leave a Reply