ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ያለውን ጭፍን ጥላቻና ለህውሓት ያለውን እውር ፍቅር ሊያወርሰን የሚሞክረው አቶ ልደቱ አያሌው

አቶ ልደቱ አያሌው አሜሪካ ወደምትባል ሩቅ አገር ከሄደ በኋላ የሚሰነዝራቸው ሐሳቦች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካውም ሩቅ እየሆኑ መጥቷል፡፡ በዚህ ሰሞንም ኢትዮ 360 ላይ ቀርቦ የሰነዘራቸውው ሐሳቦች ከአስተሳሰብ ጠለል በታች የወረዱና እውነትን የሚክዱ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹንም ለመጠቃቀስ ያህል፡-

አቶ ልደቱ ከህወሓት ጋር የሚደረገው ጦርነት የአገርን ፍርሰት የሚያቀላጥፍ እንጂ ኢትዮጵያን ከመበታተን የሚያተርፍ ነው ብሎ አያምንም፡፡ አገር እያፈረሰ ያለው ብቸኛ ሃይልም በዶክተር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት እንጂ በዶክተር ደብረ ጽዮንና በጌታቸው ረዳ የሚመራው የሽብር ድርጅት ነው ብሎ አያስብም፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ባሁኑ ሰዓት ከዓለም አገራትና መንግሥታት ጎራ ብቻዋን ተሰልፋ ቀጣይነቷን ለማረጋገጥ እየጣረች ያለችው ኢትዮጵያ ብትሆንም…. የአቶ ልደቱን ታማሚ ልብ የሚያንሰፈስፈው ግን ብቸኛዋ አገር ሳትሆን ብቸኛ መስሎ የሚታየውና በሽተኛው የሽብር ቡድን ነው፡፡

እናም አቶ ልደቱ ስለ አገሩ ሲያስብ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጎን በወዳጅነት መንፈስ ተሰልፋ በስውር ስታጠቃትና ስታዳክማት የምትታየው ሲሆን፣ በህውሓት በኩል ተሰልፎ አሸባሪውን ወደ ሥልጣን በመመለስና አገር በማፈራረስ ሊጠቅመን የሚፈልገው ውጫዊ ሃይል ግን አይታየውም፡፡ ምዕራቡ ዓለምም ሆነ ግብጽና ሱዳን ከማን ጎን እንደተሰለፉ ማወቅ አይሻም፡፡ የፌደራል መንግሥቱ ኢሳያስ ከተባለ ዋነኛ የኢትዮጵያ ጠላት ጋር ሕብረት ፈጥሮ የእራሱን አገር እያቆሰለ መሆኑን ሲናገር የኦነግ ሸኔን እና የትሕነግን ጥምረት ግን አገር የመታደግ ዘመቻ አድርጎ ይመለከተዋል፡፡ በመሆኑም አገር ወዳድ በመሆኑ የተነሳ አጋር ካጣው ድርጅት ጋር ድርድር በማድረግ የወልቃይትን መሬት ሰጥተን ብሎም ከሱዳን ጋር የሚገናኝበትን ኮሪደር ከፍተን ኢትዮጵያን እንታደግ ዘንድ ይመክረናል፡፡

ሲቀጥል ደግሞ የጥላቻ ፖለቲካን ስናስብ ከአቶ ልደቱ እና ከአንዳንድ ጥቅመኛ ኤሊቶችና ፖለቲከኞች ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ህውሓትን እንደሚጠየፍ እሙን ነው፡፡ አቶ ልደቱም ይሄንን ሐቅ በሚዛኑ ሰፍሮ በመውሰድ ፈንታ ህውሓትን የሚጠላ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ትግራይን እንደሚጠላ ቆጥሮ ኀዘኑን ከገለጸ በኋላ ኢትዮጵያውያንን ሲያወግዝ ይሰማል፡፡ በሌላ መልኩ ግን የትግራይ ኤሊትና አሸባሪው ድርጅት በአማራም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ ሲነዙት የኖሩት የጥላቻ ስብከት አይታወሰውም፡፡ እና ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያውያን ህውሓትን የሚጠሉበት ምክንያት ምንድን ነው? እኔስ ህውሓትን የምወድደው ለምንድን ነው›› ብሎ እራሱን አይጠይቅም፡፡

See also  ታሪክን የሁዋሊት - በእውቀቱ ስዩም

በበኩሌ አቶ ልደቱ ለህወሓት ያለው ፍቅር ከአገር የተለየ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ባላውቅም፣ ኢትዮጵያውያን ግን ትሕነግን የሚጠሉበት ምክንያት የጥላቻ ፖለቲካን ገርስሰው አንድነታቸውን እና ፍቅራቸውን መጎናጸፍ ስለሚሹ ነው›› ብዬ አምናለሁ፡፡ ህውሓትን የሚጠሉት ሕዝቦችን የሚነጣጥል ሐውልት ሲተክልና በስሑት የታሪክ ትርክት ብሔር ብሔረሰቦችን ሲያገዳድል የኖረ የጥላቻ አባት መሆኑን ስለሚረዱ ነው›› የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
በአገር ማዕቀፍ ውስጥ ተሰባስበው ህውሓትን የሚታገሉ ሁሉ የጥላቻን ዛፍ ገርስሰው ፍቅርንን እና አንድነትን ማስፈን የሚመኙ ሲሆኑ፣ ከትሕነግ ጋር ግንባር ፈጥረው አገራቸውን የሚወጉት ደግሞ ኢትዮጵያን ማፍረስና አንድነትን መደምሰስ የሚሹ ናቸው፡፡ ለማስረጃም ያህል የኦነግ ሸኔን እና የትሕነግን የጥምረት አጀንዳ ገለጥ ብናደርገው ‹‹አሃዳዊ በሚል የጭፍጨፋ ኮድ አማራን ማጥፋት›› እና ‹‹የዘር ፖለቲካን ማስፋፋት›› ከሚሉ ዓላማዎች ውጭ ቅንጣት ታክል የፍቅር ትርክትና ጤናማ ግንኙነት በውስጡ አናገኝበትም፡፡
የትሕነግና የኦነግ ጥምረት የኦሮሞን እና የአማራን፣ የትግራይን እና የአፋርን ሕዝብ ደም በማፋሰስ የሕዝቦችን የዘመናት ወንድማማችነት መበጣጠስ ከሚል ግብ ውጭ ሌላ አጀንዳ የለውም፡፡ ይሄንንም የሚያውቁ ኢትዮጰያውያን ሁሉ እኒህ የሰላም ጸሮች ካልከሰሙ በቀር በኢትዮጵያ ምድር ላይ ፍቅር ሊኖር እንደማይችል አምነው በአገር የመታደግ ዘመቻው ላይ የሚሳተፉና የሚደግፉ ሆነዋል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በባለፈው አንድ ዓመት ህውሓት ሲያደርጋቸው የነበሩ አረመኔያዊ ድርጊቶች በጤነኛ ልብ ሲታሰቡ ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን የሚፈጥሩ መሆናቸው ነው፡፡ ምድራቸው ላይ ወረራ ፈጽሞ መነኩሴዎችን ሲደፍር፣ ሰዎችን ቀርቶ ከብቶችን በጥይት ሲገድል፣ ሚሊዮኖችን ሲያፈናቅል እና በትሪሊዮን የሚቆጠር ሐብት ሲያወድም የከረመን አሸባሪ የጥፋቱ ገፈት ቀማሽ የሆኑት አፋሮችና አማራዎች ቀርቶ ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ አለመጥላት ስለማይቻላቸው ነው፡፡ አቶ ልደቱ ግን የትውልድ ቀየውን ወርሮ ከላሊበላ አየር መንገድ ጋር በርካታ ተቋማትን ሲዘርፍና ሲጨፈጭፍ የከረመው አሸባሪ የግሉን ሆቴል ስላልነካበት ሊጠላው አልተቻለውም፡፡

በተረፈ ሰሜን እዝ ተወግቶ ጦርነቱ እስኪጀመር ድረስ ‹‹የትግራይ ሕዝብና ህውሓት የተለያዩ ናቸው›› የሚለው አስተሳሰብ ሲንጸባረቅ የነበረው ከኢትዮጵያን እንጂ ከትግራይ ልሂቃን እንዳልነበረ አቶ ልደቱን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የትሕነግ ልሂቃንማ በሕይወት የሌለውን የአጼዎቹን ሥርዓት ከመቃብር ቆፍረው በማውጣት ብሎም ለአማራዎችና ለዜግነት ፖለቲካ አራማጆች በመስጠት ‹‹ያለፈው ሥርዓት አይመለስም›› በሚል ፉከራ በሕይወት የነበረውን ሕዝብ ሲያስጨፈጭፉ ነበር፡፡

See also  ሰበር ዜና - ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሃዋርያቶች መንገድ ችግሩን ለመፍታት ተስማማች

አሁንም ቢሆን አቶ ልደቱ በአንደበቱ ፈንታ ጭንቅላቱን ቢጠቀም አፋርን እና አማራን ሲያወድም ከርሞ ወደ ክልሉ ከተመለሰው መንጋ ይልቅ እጅግ መራር በደል ሲፈጸምበት የከረመው ሕዝብ ልብ ውስጥ የፍቅር መንፈስ መኖሩን ይረዳ ነበር፡፡ ከተቻለ አራት ኪሎ ገብቶ መንገስ፣ ካልተቻለ አገር ማፍረስና የዜጎችን አንገት ማስጎንበስ በሚል አስተሳሰብ ሸዋ ድረስ የመጣውን ሕዝባዊ ወራሪ እስከ አድዋና ተንቤን ድረስ ሄዶ በመምታት ፈንታ ራያ ላይ ጦርነቱ ሲቆም እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አፋሮችና አማራዎች ዝምታን የመረጡት የህውሓትን መደምሰስ እንጂ የትግራይ ቤቶችን መፈራረስና የንጹሐንን ደም መፍሰስ ስለማይሹ መሆኑን ይገነዘብ ነበር፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ በምክንያታዊነት ፈንታ ስሜታዊነትና ደም ፍላት የሚንጸባረቅበት ኢትዮጵያውያን ለህውሓት ያላቸው ጥላቻ ሳይሆን አቶ ልደቱ ለኤርትራና ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ያለው የጥላቻ መንፈስ ነው፡፡ ምንም እንኳን ኢሳያስ ከህውሓት ጎን ተሰልፎ ኢትዮጵያን በመውጋት ፈንታ እገዛ ሲያደርግላት በዐይናችን ብንመለከትም አቶ ልደቱ ግን ያላንዳች ተጨባጭ ማስረጃ ‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ የፕሬዝዳንት ኢሳያስን ያህል ታሪካዊ ጠላት የላትም›› የሚል ጥላቻውን ሊያወርሰን ይፈልጋል፡፡

እና ደግሞ የሃያ ሰባት ዓመቱ ግፍ አንሶት ‹‹የማዋርደው ብሔርና የማፈርሰው አገር አለኝ›› በሚል ፉከራ ወረራ ፈጽሞ ባደረሰው ውድመት አርባ ዓመት ወደ ኋላ የመለሰንን አረመኔ ቡድን ‹‹አገር የሚታደግ የቁርጥ ቀን ልጅ አድርጎ ‹‹ህውሓትን ባለመጥላት ኢትዮጵያን እንታደጋት›› የሚል ጥሪ ያቀርብልናል፡፡

እናም ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች በመነሳት አቶ ልደቱ ከገሃዱ ሐቅ ባፈነገጠውና ግላዊ ጥቅም በተጫነው በዚህ አስተሳሰቡ የታመመውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ማባበስ እንጂ መፈወስ ስለማይቻለው ፖለቲካውን ትቶ ልቡን ቢታከም ጥሩ ነው እላለሁ፡፡


(አሳዬ ደርቤ ለድሬ ቲዩብ)

Leave a Reply