የሱዳን ጦር ሠራዊት የራሱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሾም ምዕራባዊያን አገራት አስጠነቀቁ

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ የሱዳን ጦር ሠራዊት የራሱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሾም ምዕራባዊያን አገራት አስጠነቀቁ

አሜሪካ፣ ኖርዌይ፣ ብሪታኒያ እና የአውሮፓ ሕብረት የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች እራሳቸው የሚፈልጉትን ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰይሙ ከሆነ በአገሪቱ ያለው ቀውስ ይባባሳል ብለዋል።

በጦር ኃይሉ መሪዎች ላይ ሕዝባዊው ተቃውሞ በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ ሠራዊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሾም ከሆነ አገሪቱን ወደባሰ ግጭት ሊያመራት ይችላል ሲሉ ምዕራባውያኑ አገራት ባስተላለፉት ማስጠንቀቂያ ገልፀዋል።

አገራቱ ጨምረውም በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የሚመለከታቸው ሲቪል ፖለቲከኞች ሳይሳተፉበት የሚሾምን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደማይደግፉ በመግለጽ ሠራዊቱ በተናጠል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሾም አስጠንቅቀዋል።

ላለፉት ሦስት ዓመታት የሱዳን የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሐምዶክ ላይ ባለፈው ጥቅምት አጋማሽ ላይ በጄነራል አል ቡርሐን መሪነት መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ ይታወሳል።

ሱዳናውያንና የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ መፈንቅለ መንግሥቱን መቃወማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥቂት ሳምንታት የቁም እስር በኋላ ወደ ሥልጣን ቢመለሱም ተቃውሞው ሳይገታ ቆይቶ ባለፈው እሁድ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።

ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ሥልጣን ወደ ሕዝቡ ተመልሶ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ በሲቪል መሪዎች እንድትተዳደር ሲጠይቁ የቆዩ ቢሆንም ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ ከጥቅምት ወር ወዲህ ቢያንስ 56 ተቃዋሚ ሰልፈኞች ተገድለዋል።

በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው ከተወገዱ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ወደ ኃላፊነታቸው ተመልሰው የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ የሥልጣን መልቀቅ ውሳኔ የሱዳን መንግሥት ሙሉ ለሙሉ በጦር ሠራዊቱ ቁጥጥር ስር እንዲገባ ያደርገዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ለወራት የቀጠለው የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎች እንደሚሉት ዋነኛ ጥያቄያቸው ጦር ሠራዊቱ ሥልጣን በሲቨሎች ለሚመራ መንግሥት አስረክቦ ከመሪነት መንበሩ ገለል እንዲል ነው።

ሱዳንን ሰላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በፈላጭ ቆራጭነት የመሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተቃውሞ ስትናጥ ቆይታለች።

ከአልበሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ ሥልጣን በአገሪቱ ጦር ሠራዊትና በሲቪል ፖለቲከኞች መካከል ተከፋፍሎ የሽግግር መንግሥት ቢቋቋምም ሁለቱ ወገኖች ሳይስማሙ ተቃውሞው ቀጥሎ ቆይቷል።

ሕዝባዊውን ለውጥ የመሩት ኃይሎች ጦር ሠራዊቱ ከአገሪቱ የመንግሥት ሥልጣን ውጪ ሆኖ ሲቪል አስተዳደር እንዲቋቋምና ሱዳን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖራት ግፊትና የተቃውሞ ሰልፎች ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት በተደረሰውና ባልተከበረው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት መሠረት የሱዳን የሽግግር መንግሥት መሪ ጄነራል አል ቡርሐን ሥልጣናቸውን ለሲቪል ፖለቲከኞች ማስረከብ የነበረባቸው መፈንቅለ መንግሥት ባደረጉ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኅዳር ወር ላይ ነበር።

ጄነራሉ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት ፖለቲከኞች ሰላማዊ ሰዎችን በፀጥታ ኃይሎች ላይ እያነሳሱ በመሆናቸው የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት ለመከላከል ነው ሲሉ የእርምጃቸውን ተገቢነት ገልጸው ነበር።

ጄነራሉ ሱዳን አሁንም በሽግግር ሂደት ላይ እንደሆነችና አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሻገር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

ለወራት ወታደራዊውን መንግሥት በመቃወም በሱዳን ጎዳናዎች ላይ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የቆዩ ሱዳናውያን በጦር ኃይሉ ላይ እምነት ስለሌላቸው ጄነራሎቹ ከመንግሥታዊ አስተዳደር ሥልጣን እንዲገለሉ እየጠየቁ ነው።

ጥቅምት ወር ላይ በጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ቀውስ ያባባሰው ሲሆን፣ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ጦር ኃይሉ በሕዝባዊ ትግል የመጣውን ለውጥ ጠልፏል በሚል ይከሳሉ።

BBC

You may also like...

Leave a Reply