በአፍሪቃ ቀንድ የፖሊሲ ኩዴታ – “የጎመን ምንቸት ውጣ”

“ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ ላይ የተነሳችው ዋናዋ ጉዳይ ወይም ክሬሟ ” ጣልቃ ገብነትን እናወግዛለን” የምትለዋ ቁልፍ ጉዳይ ናት። የቀንዱ አገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ከፈጸሙ ቀድመው የሚያደርጉት ነገር አንዱ ሌላውን እንዳይጎዳ መውሰን ነውና የተቃዋሚና ተላላኪ ወታደር የሚያሰማሩት ሃይሎች ላብ ላብ ቢላቸው አይፈረድባቸውም። የትህነግም ” ለጊዜው መገንጠሉ ቀርቶብኝ በነበረው ፌደራሊዝም እንድቀጥል አማልዱኝ” ለቅሶም የዚሁ አካል ስለመሆኑ የማይገባቸው ካሉ ” የቀድሞው ስብከት” ውጤቶችን ብቻ ናቸው።”

በፍቃዱ ዴሬሳ

“ራሱ መንግስት ሆኖ ትግራይንና የትግራይን ሕዝብ ከምመራት አገር ነጻ አውጣለሁ” በሚል አጀንዳ ሴራ አዝሎ ኢትዮጵያን እንድትፈረከስ አድርጎ የሰራት ትህነግ ከጠቀለለው ስልጣን ሲነሳና “በድርሻህ” በመባሉ ይህ ሁሉ መከራና ጣጣ ሊመጣ እንደቻለ የሚከራከር ካለ የጎደለበት ብቻ ነው። የትህነግን ክሩርፊያ ተከትሎ ዓለም አብሮ ያደመበት ምክንያት ደግሞ በትህነግ ወይም በትግራይ ፍቅር ሳይሆን በቀጣናው እየሆነ ያለው አዲስ አብዮት እንደሆነ ነገሩ እየተገለጠ ነው። አብይ አህመድ “ከምጡ በሁዋላ” እንደሚሉት።

አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡም፣ ሊመጡ ሲሉም፣ እንዲመጡም ሲደረግ አሜሪካ ነበረችበት። ስም ጠርታ እሳቸው ካልሆኑ ብላም ነበር። በለውጡ መፋፋምና መቋጫ ሰሞን የትህነግ ከፍተኛ ሰዎች አሜሪካ ሄደው “የፈለጋችሁትን እንታዘዛለን፣ ጥፋታችንን እናርማለን እርዱን” ሲሉ “በቃችሁ” በሚል ፊት ነስታ ያባረረች አሜሪካ፣ ተሟግታ ስልጣን ላይ እንዲወጡ ያደረገቻቸውን አብይን ለምን ጠመደች? ” ትህነግ “በመጠንህ፣ በመስፈሪያህና በገደብ ኑር” መባሉ? ከላይ እንደተባለው መልሱ የማይገባው ካለ አሁንም ” ልዩ ነህ” እየተባለ ሲሞላ የነበረ ብቻ ነው።

በጥቅሉ በአፍሪቃ ቀንድ አዲ ጽንስ ተጸንሶ ነበርና ሳይወለድ ለማጨናገፍ ሲታለም የተወረወረው ትህነግ ተገኘ። የጽንሱ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለማስወገድ ትህነግ አርጩሜ ሆነ። ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ መሪዎች፣ የዓለሙ ድርጅት፣ የፍናንፍንታም ማህበራት ሳይቀሩ ከተከፈላቸው ምናምንቴዎች ጋር ሆነ አደሙ። በተደራጀ፣ በተጠና መንገድ ኢትዮጵያን እንደ መጋጃ ደግሞ ደጋግመው አላመጡዋት። ሕዝብ አንድ ሆነና ሁሉንም ገለበጠ። ወዳጅ የተባሉት አገሮችም ዓለም ዓቀፉን ዘመቻ በጡንቻቸው መጠን እየመከቱ አዲሱን ሽል ከውርጃ ጠበቁት። ቀኑ ሲደርስ አፍሪቃ ቀንድ ላይ በላይ የተነባበረ ልዩ ዜና ይሰማ ጀመር። በገና ዋዜማ ” የዘንድሮውን የልደት በዓል የምናከብረው የመከራችን ዘመን እያከተመ፣ የችግራችን ቋጠሮ እየተፈታ፣ የሰቆቃችን ምንጭ ላይመለስ እየደረቀ ባለበት ወቅት ነው። መከራችንን ከኋላችን ጥለን ተስፋችንን አሻግረን እያየን የምናከብረው በዓል ነው” የተባልነው ከዚሁ ከዜናው ጋር ተያይዞ ይሆን?የጎመን ምንቸት ውጣ …

ልክ የዛሬ ወር፣ አሜሪካ “አዲስ አበባን ለቃችሁ ውጡ” እያለች አታሞ ስትደልቅ፣ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግይ ኢትዮጵያ ለመጎብኘት ስዲስ አበባ ሲገቡ አነፍናፊዎች ቻይና ኤርትራ እንደምትገባ በጎንዮሽ ሲያሙ ነበር። ቀይ ባህር ላይ እንዳሻት ለመሽከርከር ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ለማስወገድ አልማ ሱዳንና ትህነግን ስትቀልብ የከረመችው አሜሪካ፣ እንደ ጎመን ምንቸት “ውጪ” ልትባል የመጨረሻው ፊሽካ ሊነፋ ባለቀ ሰዓት ውስጥ እንደምንገኝ አመልካች የሆነው ዜና ከኬንያ ተሰምቷል።

ሱዳን እንኳን የአሜሪካ ባሪያ ልትሆን በውሉ መስከን አቅቷት እየተናጠች ነው። እንደምሰማው ከሆነ ኢትዮጵያና ኤርትራ በፈለጉ ሰዓት ከፍና ዝቅ የሚያደርጉት ሃይል አላቸው። በተለይ ኢሳያስ ሱዳን ውስጥ መናኘት ከፈለጉ ማንም ሊያግዳቸው እንደማይችል የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ትህነግም ቢሆን እንኳን አሜርካንን ሊታዘዝና ሊያሸርግድ ቀርቶ ለራሱም ማጣፊያ እንዳጠረው እየታየ ነው። በድብዳቤ፣ በቃለ ምልልስ፣ በቲውተር “እባክችሁን አደራድሩን” በሚል የጣር ጭህኸት ላይ ናቸው። Press Tv Francias’s “አማፂያኑ የህወሓት ሠራዊት በወረራ በያዛቸው ከተሞች የፈፀመዉ ግፍ የሕዝብን የቁጣ ማዕበልን ቀስቅሶ የመተላለፊያ ቀዳዳዉን መድፈኑ አሜሪካንን ተስፋ አስቆርጧል” ሲል አሜሪካ የቀድም ሹሞችን በመቀየር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አዲስ የወዳጅነት ንግግር እንደምትጀምር አምላክቶ ነበር። ሌሎች ምልክቶችም መያየታቸውን አስፍሮ ነበር። የዚህ ዜና ፍንጭ ውጤት ይሁን ሌላ ፊልትማንን አሜሪካ ለማንሳት መወሰኗ ተሰምቷል።

አሜሪካ አዲስ አሳብ ላይ እንዳለች ቻይና ኤርትራ ገብታ የምጽዋንና የአሰብን ቁልፍ ተረክባለች። ይህ ብቻ አይደለም ጣልቅ ገብነትን በጋራ ለመከላከል ቻይናና ኤርትራ ተስማምተዋል። ጣልቃ ገብነትን ለመቋቋም መስማማት ማለት ምን ማለትይሆን? ዝርዝሩ ወደፊት የሚያት ይሆናል። እዚህ ላይ ኢትዮጵያና ኤርትራ ገና መተቃቀፍ ሲጀምሩ የተፈራረሙት የመጀመሪያ ውል የወታደራዊና የድህነት ስምምነት ነው። ውሎ አድሮ ደግሞ ሶማሌ ግብታለች። አሁን ቻይና ኤርትራ ጉዳይዋን ጨርሳ ኬንያ ግብታ በቀጠናው የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት በኩል አስተዋጽኦ ለማበርከት በማሰብ ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንደምትሾም ይፋ አድርጋለች። ይህ ዜና በአፍሪቃ ቀንድ ያለውን የአዲሱን ምጥ መገላገያ የሚያፋጥን ተደርጎ ተወስዷል። ሌሎችን የዛኑ ያህል ቢያኮማትርም።

“የአፍሪካ ቀንድ አገራት የራሳቸውን እጣ ፈንታ እንዲወስኑ እና የሰላም ጉባዔ እንዲጠሩ እንሰራለን” ሲሉ ኬንያ በተሰጠ የጋራ መግለጫ ላይ ይፋ ያደረጉት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አፍሪቃ ቀንድ አገራት ከጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆኑ ቻይና አስፈላጊውን ሁሉ እንደምታደረግ አመልክተዋል። በሌላ አነጋገር አጀንዳና ቀይረው የአሜሪካ የቀድሞ መድብ ላይ እንደሚቀመጡ አስታውቀዋል።

የአፍሪቃ ቀንድ አገራት ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ናቸው። ከሱዳን በቀር አራቱ አገሮች ወድጃ ናቸው። ሱዳንም ብትሆን ችግር ካላመጣት በሁዋላ እንደማይሆን ሲገባት ወደ እቅፉ እንደምትመጣ ይታመናል። በዚህ መነሻ ከሱዳን ውጪ ያሉት አገሮች እንደ ቻይና ዕቅድ ወደ ፖለቲካዊ ስምምነት ከመጡ የጋራ ራስን የመከላከል ስልት መንደፋቸው አይቀርም። ለዚህም ይመስላል ሰሞኑንን ኬንያ የሚመላለሱና የመሸጉ የተቃዋሚ አመራርና ወታደራዊ ተላላኪዎች ላብ ላብ እያላቸው በየብሎጉ የተቃውሞ ሙሾ ሲያሰሙ የከረሙት። እንግዲህ ይህ የሚታየው የዕቅዱ ትግበራ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ስለሚሆን ብዙም ሳይቆይ ግልጽ እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ ላይ የተነሳችው ዋናዋ ጉዳይ ወይም ክሬሟ ” ጣልቃ ገብነትን እናወግዛለን” የምትለዋ ቁልፍ ጉዳይ ናት። የቀንዱ አገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ከፈጸሙ ቀድመው የሚያደርጉት ነገር አንዱ ሌላውን እንዳይጎዳ መውሰን ነውና የተቃዋሚና ተላላኪ ወታደር የሚያሰማሩት ሃይሎች ላብ ላብ ቢላቸው አይፈረድባቸውም። የትህነግም ” ለጊዜው መገንጠሉ ቀርቶብኝ በነበረው ፌደራሊዝም እንድቀጥል አማልዱኝ” ለቅሶም የዚሁ አካል ስለመሆኑ የማይገባቸው ካሉ ” የቀድሞው ስብከት” ውጤቶችን ብቻ ናቸው። ይህ እንደ ጠሃይ ወለል ብሎ የሚታይ ገሃድ ጉዳይ ነውና።

በአፍሪቃ ቀንድ በተለይም በቀይ ባህር ፖለቲካ የኢትዮጵያ ዳግም መሪ መጨበጥ አቅላቸውን ( ካላቸው ነው) አሳጥቶ የአንድ ቀበሌ ወሮበላ ደጋፊ እስከመሆን የደረሱት አሜሪካኖች፣ ዛሬስ ምን ያስባሉ? አይናቸውን በበረኪና ታጥበው ” አዲስ አበባ ታውካለች፣ አማጺያን ሊይዟት ነውና ለቃችሁ ውጡ” በሚለው ግልብ ፖለትካቸው ይቀጥሉበታል? ወይስ ማሻሻያ ያደርጋሉ?

ከታማኝ ምንጮችና ከአንዳንድ ለፖሊሲ አውጪዎች ቅርብ ከሆኑ ወገኖች የሚሸቱ መረጃዎች አሜርካ ከትህነግ ጋር መጓዙ እንደማያዋጣት የማመኗን ጉዳይ ነው። ከዛም በላይ አሜሪካ ሁሌም ከአሸናፊ ጋር ናት። በተጨማሪም ሱዳን ላይ እየከሸፈባት ሲሆን የቻይናን ሩጫና የአፍሪቃ ቀንድን የፖለቲካ ጨዋታ ፍጥነት መከተል የቻለች አይመስልም።

ፕሬስ ቲቪ እንደሰጠው ፍንጭ፣ አሜሪካ አዲስ አሳብ በአሮጌ ወኪል ማራመድ እንደማይቻል ስለምታውቅና ባህሏም ስለሆነ የፌልት ማን መነሳት ምን አልባትም የአዲሱ አሳብ መጀመሪያ ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ። በዴሞክራሲ ምህላ፣ በሰብአዊ እርዳታ ካባ፣ እንዲሁም በዓለሙ የገንዘብ ተቋማት ክርን አማካይነት የፖለቲካ ጫና የምትፈጥረው አሜሪካ በምንም ተዓምር የአፍሪቃ ቀንድን መክሰር አትፈልግምና የአቋም ለውጧ ፈጥኖ እንደሚሰማ እሙን ነው።

በኢትዮጵያና ኤርትራ ጠንሳሽነት በቀይባህር ላይ የሚተከለው አዲስ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ትሥሥር ቻይና ከገባችበት ሊቆም የሚችል አይሆንምና ኢትዮጵያ ከተረባረቡባት መንጋጋዎች ፈልቀቃ ወጥታ የጀመረቸው የድል ጉዞ በውስጥ የፖለቲካ እርቅ ለማገዝ የሚደረገው እንቅስቃሴ እጅግ ቀናነትን፣ በጎነትን፣ ከምንም በላይ ለምስኪኑ ህዝብ ሰላምና መጪው ትውልድ ሲባል መቻቻል የነገሰበት እንዲሆን ሁሉም ወገን ሊረባረብ እንደሚገባ በስፋት እየተነገረ ነው። ውሎ አድሮ የበጎ ዜናዎች ጎርፍ እንደሚያጎርፍብን በማመን ሰላም እላለሁ።

መምህር ፍቃዱ ዴሬሳ – ይህ ነጻ አስተያየት የጸሃፊውን አሳብ ብቻ የሚያንጸባርቅ ነው።


Leave a Reply