“የበግ ቆዳ ያለው” የዓመት በዓል ገበያ ነበር። ብር በመያዝ በየመንደሩ እየዞሩ ” የበግ ቆዳ ያለው” ማለት የበዓል ዕለት አትራፊ ስራ ነበር። “የንብ ቆዳ ያለው” የተባለው ደግሞ በ1997 ቅንጅት በጠራው “ሱናሜ” የተሰኘ የመጨረሻ የምርጫ ቅስቀሳ ማሳረጊያ ሰልፍ ላይ ነበር። ቀደም ሲል ገዢው ድርጅት መጠነኛ ሰዎች የተገኙበትን ሰልፍ ” ማዕበል” ሲል በ”ምጡቁ” መሪው አማካይነት ሰይሞ ነበርና፣ ቅንጅት የጠራው ሰልፍ አገር ምድሩን ሲያጥለቀልቅ ነበር ” የንብ ቆዳ ያለው” እያሉ ሰልፈኞች እነ “ማዕበሎች” ላይ የተሳለቁባቸው። ቆዳ ሞቶ የተገፈፈ የሙቱ ሽፋን መሆኑ ልብ ይሏል። እናም እንደተባለው ሆኖ ታይቶ ነበር።

በወያኔ ሴራና በራሱ ድክመት ይህን ሃይልና የሕዝብ ሱናሚ በወጉ መጠቀም ያልቻለው ቅንጅት የተንኮታኮተውና ለተረት እንኳን እንዳይመች ሆኖ የቦነነው ራሱን ጭራ በማድረጉ ነበር። ነብሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ( የኔታ) ” ጭብጨባ ጭንቅላት ያሳብጣል” እንዳሉት፣ የትወሰኑ የቅንጅት አመራሮች በጭብጨባ ጭንቅላታቸው አብጦ፣ የተቀሩት ደግሞ ፖለቲካን ከቀናነት ጋር አብረው በመስፋት ከቀንድነት ይልቅ ጭራ መሆንን መርጠው መጨረሻቸው ወህኒ ሆነ።

ከወህኒ በሁዋላ በመታሰራቸው ብቻ ራሳቸውን ባለ ልዩ ሊሻን ያደረጉ ሌሎችን አገለሉ። ከቃሊቲ ማግስት ጀምሮ ተቧደኑና ከቀድሞው የከፋ ጥፋት ሰሩ። የኔታ ነብሳቸውን ይማረውና ይህን “እስርን ኒሻን ያደረጉ” ያሏቸው ቅንጅትን እንዴት እንዳነተቡት ለትምህርት ይሆን ዘንድ በወጉ ማብራሪያ መስጥታቸውን ማስታወስ አግባብ ይሆናል። ዛሬ ይህን ያነሳሁት ትናንት ይፋ የተደረገውን የምህረት ዜና ተከትሎ ከየአቅጣጫው የሚሰነዘረውን አስተያየት አስመልክቶ ሃሳብ ለመስጠት ነው።

በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአገር ውስጥ በአንድ ድምጽ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ” መሪዎቻችንን መርጠናል” በማለት በተደጋጋሚ ” ጣልቃ በመግባት የመረጥነውን መንግስት አትንኩብን” ሲል ከርሟል። ይህ መንግስት ሲመረጥ ተቃዋሚ ድርጅቶች ሳይቀሩ ምርጫውን አምነው ተቀብለዋል። በሌላ አነጋገር የዚህን መንግስት ቀንድነት ሕዝብ በአብላጫ ድምጽ ተቀብሏል። ከምህረቱ ዜና በሁዋላ ግን ሰላም ይውረድ፣ ድርድር ይካሄድ፣ እልቂት በቃ ሲሉ የነበሩትን ጨምሮ መንግስትን ” ጭራ ሁን” ሲሉ እየተሰሙ ነው።

የኢትዮጵያ ነቅርሳ የሆነው ትህነግ እጅግ ሰፊና አዕምሮን የሚፈታተን በደል መፈጸሙ እሙን ነው። የፈጸመው ወንጀል ዓይነቱ፣ ይዘቱና የተፈጸመበት አግባብ ከመጨረሻ ግቡ ጋር አብሮ ሲሰላ የሚፈጥረው ስሜት በቃላት የሚገለጽ አይደለም። ይህ እንዲሆን ያደረጉ ዋናው የቂም ዘመቻ መሃንዲሶች በህግ ሊጠየቁ ይገባል። ይህ እውነት ነው። ሊስተባበልና ሊሸፋፈን የሚችልም ጉዳይ አይሆንም። በተመሳሳይ እነዚህ የዘመን መርገምት የሆኑ የትህነግ መሪዎች ሃሰትና ጥላቻ ሰብከውት፣ “ልትጠፋ ነው” ብለው አስፈራርተውት፣ ሌላ አማራጭ ሃሳብ እንዳይሰማ ዘግተውበት፣ የተለይ አሳብና ዓላማ ያላቸውን አሳደው፣ በራሳቸው አምሳልና ነብስ እንዲያስብ አድርገው ያፈጠሩት ምስኪን ሕዝብ ተለይቶ ሊታይ ይገባል።

በትግራይ በርካታ ዜጎች ችግር ላይ መሆናቸው፣ ሁለት ሚሊዩንና ከዛ በላይ ህዝብ ለዓመታት በዱቄትና ዘይት እርዳታበምግብ ለስራ መርሃግብር ከመኖራቸው አንጻር ዛሬም ለከፋ ቀውስ መጋለጣቸው፣ በጦርነቱ ሳቢያ ህክምናን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች ማጣታቸው የሚካድ አይደለም። በዚህ መጠን ይህን ሁሉ ችግር የደፋባቸውና እንደ ሰብአዊ ጋሻ የያዛቸው፣ ለወደፊትም ተጨማሪ ችግር የሚያመርትላቸው ትህነግ መሆኑ ሳይታበል የተፈታ ቢሆንም ለህዝቡ ማዘን ከመንግስትም፣ ከህዝብም ይጠበቃል። አለያ የትህነግን ዓላማና አካሄድ መድገም ወይም ደጋፊው መሆን ይሆናል። ይህን ነቀርሳ በእሱ አምሳል በማሰብ ማስወገድና መገላገል ስለማይቻል በብርቱ የደህንነት ጥንቃቄ ውስጥ በመሆን ሃሳቡን ማሸነፍ ግድ ነው።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “ትህነግን ብቻ ሳይሆን አመለካከቱንም እናጠፋለን” ሲል የተናገረውን ታላቅ መሪ አሳብ ለማጽናት በየደረጃው የሚወሰዱ አግባብነት ያላቸውን የመንግስት ውሳኔዎች ረጋ ብሎ መመርመር ዛሬ የዜጎች ሁሉ ግዴታ ነው። ትችትም ካለ በጥንቃቄና እጅግ ጨዋነት በተሞላው መንገድ መሆን ይገባዋል። እኔም ይህን እንድጽፍ ያነሳሳኝ ይህ ጉዳይ ነው።

ማንም መተንፈስ ብቻ የሚችል ሰው እንደሚረዳው ዛሬ ኢትዮጵያ ውጊያ እያደረገች ያለችው ከዓለም ታላላቅ አገሮች፣ መሪዎች፣ ተቋማት፣ እርዳታ ሰጪዎች፣ ሚዲያዎች፣ ሴራ አምራቾች፣ የአገር ውስጥ እፉኝቶች፣ ቅጥር ነብሰ ገዳዮች፣ ተላላኪዎችና በደፈናው በየቦታው ከሚሹለከለኩ ተላላኪዎች ጋር ነው። ይህ ሁሉ የተቀነባበረ ዘመቻ ለዚህ ከሃጂና ነቀርሳ ሃይል ጉልበት እንደሆነው መረዳት አለመቻል “አውቆ የተኛ” እንዲሉ ካልሆነ ሌላ ምላሽ የለውም። ሊኖርም አይችልም።

ከጅምሩ ትህነግ በራሱ የልብ ትርታ ላይ ተክሎ ሲመራው የነበረውና የአገሪቱ የጸጥታ መዋቅር ቀድሞውኑ እሱ ከሌለ እንዲነትብና እንዲከስም ተደርጎ የተሰራ መሆኑ ሳያንስ፣ አድፍጦ በተረፈው የመከላከያ ሃይላችን ላይ የወሰደው እርምጃ ባስከተለው መዘዝ ባዶ ቤት ሆን። እሱ ሁሉ በጁ፣ ሁሉ በደጁ እያለ በመንታ እሳቤው የአገሪቱን መከላከያ እያኮሰሰ ግዙፍ ሃይል ገነባ። አገር የሚመራ መስሎ ያለከላካይ ራሱን አደራጅቶብን ነበርና በቅጽበት ወረረን። ከላይ የተገለጹት ክፍሎች ነዳጅ እየረጩለት “አዲስ አበባ ደረስኩ” እያለ አሽካካ። ወዳጆቹና ላኪዎቹ የማደናበሪያ ዜና፣ መመሪያና እቅድ እያሰራጩ አሩን በየስፍራው ማዕድ ላይ የሚያራ፣ ሊጥ የሚጠጣ፣ አሻሮ የሚቅም፣ እንኩሮ ኬክ የሆነለት፣ ያገኘውን ከሚያግበሰበስ፣ ወሮ በላ፣ ሃይማኖትና ባህል የሚያረክስ፣ ሳይመርጥ አያቱ የሚሆኑትን ሳይቀር በደቦ የሚደፍር፣ ለሃጢያቱና በቀሉ ቃላት ያልተዘጋጁለት ወራዳ ቡድን ኢትዮጵያ ላይ ሊጭኑ ያደረጉት ዘመቻ ከሸፈ። ህዝብ አንድ ሆኖ አገሩን ከውርደትና ከጉግማንጉግ ጠበቀ። ይህ ታሪክ የሚዘክረው ሃቅ ነው። በዚያው መጠን ነገሮች ተገልብጠው ዛሬ ላይ ጠንካራ መከላከያ ተገነባ። ገና ይገነባል። እንድ እውነት ቢኖር ግን ባዶ ቤትነታችን አክትሟል። ስጋት የለም። ሕዝብ ልጆቹን መርቆ መከላከያውን ገንብቷል።

ይህን ካልኩ ወደ ዋና አሳቤ ልመለስ። ሰባት የቅድሞ የትህነግ አመራሮች እነ አቶ ስብሃትን ጨምሮ በምህረት ተፈተዋል። ዕድሜና በሽታ ግምት ውስጥ ገብተው ክሳቸው ተቋርጦ ከተለቀቁት ውጭ በተቀሩት የትህነግ አመራሮችና በአገር መካለከያ ሰራዊት ላይ በክህደት እጃቸውን ባነሱት ላይ የተከፈተው ክስ ይቀጥላል። እንደ ዜናው ከሆነ በእነ ጃዋርና እስክንድር ነጋ መዘገብ የተከሰሱ በሙሉ ክሳቸው ተቋርጧል።

ይህ ዜና ይፋ የሆነው አገራዊ መግባባት ለመጀመርና ምክክሩ አገሪቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናጠ ያለውን ልዩነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ሲባል መሆኑ ተነግሯል። እዚህ ላይ ልብ እንበል። ኢትዮጵያ ከታመመች ቆይቷል። ምን ያማያውቅ አዲስ ትውልድ ” አያትህ፣ቅድመ አያትህ ሰራው” በሚባል ጥፋት መከራውን እያየ ነው። አንዱ ሄዶ ሌላ ሲመጣ የበቀል ሰይፍ እየመዘዘ ህዝብ ሲፈናቀል፣ ሲሰደደ፣ ሲገደል፣ ሲታሰርና ሲሰቃይ ማየት የተለመደ ነው።

በኢትዮጵያ ደርግ የኢትዮጵያን ችግር በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊዘጋው ሲገባ ስሙን እየቀያየረ ሲንፈራገጥ ኖሮ ተዋርዶ አዋረደን። ለውሮ በላዎች አሳልፎ ሰጠን። ኢህአዴግ የሚባለው የተላላኪዎች ሕብረት የወሮ በላዎች መጠቀሚያ ሆኖ አገሪቱን በጎሳ በጣጥሶና ቂም ረጭቶ ሞተ። ከደርግ በላይ ጥፋት ሰርቶ ቢሞቱም አስኳሉ ትህነግ ከነ ሙሉ ትጥቁና ሃብቱ ምሽግ በመያዙ መከራችን መቋጫ አጣ። ከመሃሉ በተነሱበት የሕዝብ ልጆችና በሕዝብ አመጽ የወደቀው ትህነግ በመጨረሻ ከላይ እንደተባለው ዘመተበን። አዲሱ የለውጥ ሃይል ከዜሮ ጀምሮ እየተላላጠ፣ የማሰቢያና የመረጋጊያ ጊዜ ተነፍጎት በህዝብ ድጋፍ ዛሬ ላይ ደረሰ። እናም በደረግ፣ በኢህአዴግ፣ በ1997 ምርጫ ወቅት አገሪቱን ወደ መልካም ጎዳና መሄድ የሚያስችላትን የባከኑ ዕድሎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጠቀም መወሰኑ ድንቅ የሚያስብል እንጂ የሚያስወቅስ አይሆንም።

ዛሬ አንድ ድሮን ተነስቶ የተሸከመውን ጥሎ ሲመለስ ሰባ አምስት ሺህ ዶላር ገደማ ነው የሚያከስረን። የሚወረወረው መሳሪያ ደግሞ መሬት ደርሶ የሰው ልጅ፣ ንብረት፣ መሳሪያ … ያወድማል። ይህቺ ደሃ አገር ከላይ ዶላር እየረጨች፣ ከስርም ሃብቷን እያወደመች ስንት ዓመት ትቀጥል? ለሚለው ጥያቄ ረጋ ብሎ በማሰብ መልስ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በዚህ አግባባስ መፈናቀልን መግታት፣ የንጹሃንን ሞት ማስቆም ፣ የአገር ሰላምን በአስተማማኝ መንገድ ማስከበር ይቻላል? ማን በዚህ መልኩ ሰላምን አሰፈነ? ደርግ? ኢህአዴግ? ማን? ለዚህ ነው ስለ ሰላምና ስለ ሰለጠነ ፖለቲካ ስናስብ ወደንም ጠላንም የሚያስከፍለውን ዋጋ መቀበል የሚገባን።

ትህነግ የሰራት ኢትዮጵያ የጎሳ ቫይረስ የወረሳት ናት። መንግስት ምንም ቢወስን ውሳኔው የሚመዘነውና የሚታየው በጎሳ መነጽር በመሆኑ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት ይከብዳል። ለምሳሌ እስክንድር ሲፈታ ያጨበጨቡ በጃውርና በቀለ ገርባ መፈታት ቅሬታቸውን ወዲያው ነው ያሰሙት። በጃዋርና በቀለ ገርባ መፈታት የሚደሰቱ በእነ እስክንድር ምህረት ይነዳሉ። ይህ የሰከረውና ምክንያታዊነት የራቀውን ቆሻሻ ፖለቲካችንን ማሳያ አንዱ ነው። መንግስት እንግዲህ ያለው በዚህ አጣብቂኝ አመልከካከት ውስጥ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። በፓርቲ ደረጃ የተወሰነ ውሳኔን የአንድ ወገን ውሳኔ በማስመሰል እዚህ ውስጥ ግብተው ልዩነት ለመዝራትና ወደ ቀደመው መተራመስ ሊመሩን የሚጣደፉ ሲቅበዘበዙ እየታየ ነው።

ውሳኔው በተለይ የአማራ ህዝብና ክልል ላይ ክህደት እንደተፈጸመ ተደርጎ እየቀረበ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በመላው አገሪቱ፣ በተለይም በኦሮሚያ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ አገራዊ የምክክር መድረኩ ታላቅ ሚና እንደሚኖረው ማመኑ በቀደመ ነበር። በስመ አማራ ስም አንድም ጥቅም ለማይሰጡት በስሙ እየተደራጁ የሚለፈልፉ ሌሎችን እያነሳሱበት መከራውን ከማብዛት የዘለለ የሚያመጡት ውጤት የለምና እንዲህ ያለው አካሄድ ቢታሰብበት ለማለት እወዳለሁ።

አስር ሚሊዮን የሚገመት የአማራ ተወላጆች ትህነግ ከሰፋውና ካቀራጨው ካርታ ውጭ ይኖራሉ ተብሎ ይታሰባል። እነዚህ ወገኖች በስመ አማራ እየማሉ በሚራገሙና ሌላውን ለክፋት በሚያነሳሳ ያልተጠና፣ እንዲያውም ልዩ ተልዕኮ ያለው በሚመስልና ባለው አጉል ቀረርቶ፣ አንዳንዴም ከባዶ የተወዛዋዥንተና የአንደረቢ መንፈስ በሚወጡ ስብከቶች ሳቢያ የአማራ ሕዝብ አብሮ ሲኖር ከነበረው ሕዝብ ጋር እንዲጋጭ እየተደረገ ነው። ይህ ሲባል ዘመኑን የማይመጥኑ የጎሳ ፖለቲካ ተላላኪዎችን ጥፋትና ክፋት ለመሸፈን አይደለም። እነዚህ ቅጥረኞች የሚፈጽሙት ጭካኔና ክፋት ላይ ተጨማሪዎች በተቆርቋሪ ነን ባዮችም እንዴት እንደሚከወን ለማሳየት ነው።

በጥቅሉ ዛሬ አገራችን በኢኮኖሚ ታማለች። በማህበራዊ ወጎቿ ላይ ቀውስ ደርሶባታል። ንብረቷ ወድሟል። አሳዛኝ ግፍ በሕዝቧ ላይ ተፈጽሟል። የተካሄደው ወረራና ውጊያ አቅሟን አዝሎታል። ከውጪ የሚደረገው ጫናም የዋዛ አይደለም። ስለሆነም የውስጡን ችግር መቅረፍ ግድ ነው። የውስጡን ችግር ለመቀረፍ በተዘጋጀው አገራዊ የምክክርና የድርድር አውድ ላይ ሁነኛ መፍትሄ ለማበጀት የሚመለከታቸው ሁሉ መሳተፍ አለባቸው። አንዱ የሚጠላው፣ ሌላው የሚወደው ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ሳይለይ ለሁሉም በሩ ክፍት ሊሆን ይገባል። የኢትዮጵያን መሰረታዊ የፖለቲካ ቀውስ ለመቸረሻ ጊዜ በስምምነት እንደ አግባቡ ዘግቶ በአዲስ ፍኖተ ካርታ ወደ ተግባር ለመግባት ልጅና የእንጀራ ልጅ ብሎ ነገር አይሰራም። ለኢትዮጵያ ሰላም ያመጣ ዘንዳ፣ ይህ በፖለቲከኞቻችን ደባና ክፋት እየደማ የሚኖር ደሃ ሕዝብ ሰላም እንዲያገኝ ሁላችንም ልክ ወረራውን ለመቀልበስ እንደተነሳነው ሁሉ በህብረት ልንነሳ ይገባል።

ኢትዮጵያ እጅግ በከባድ ህመም ውስጥ ናት። እናስብ። ረጋ ብለን እንመርመር። መፍትሄው ተነጋግሮ መቋጫ ማበጀት ብቻ ነው። ከዚህ በላይ በጦርነት መኖር እያደር ተዋጊውንም ይሰለቸዋል። ደጀኑም ክንዱ ይዝላል። ኢኮኖሚውም ጀማምሮታል ዘጭ ማለቱ አይቀርም። ከዛ ጠላት እንደሚመኘው በየስፍራው አሁን ብቅ ብቅ እያሉ እንደሚያናፉትና ዝርፊያ እንደሚፈጽሙት ተላላኪዎች በሁሉም አቅጣጫ የጎበዝ አለቃ ይወረናል። ራሳቸውን “ማናምን ነን” እያሉ የሚሾሙና በጎንዮሽ በኪራይ ሚዲያዎችን የሚያስጮሁ ይበሉናል። በማህበራዊ ገጾቻቸው በሰበሰቡት ሃይል ያሳድሙብናል።

ሰላማዊ የንግግርና የምክክር መድረኩ አይናቸውን የሚያቀላቸውና ዘወትር ካልተሳደቡ የማይመሽላቸው አጀንዳ “ተሸካሚዎች” ጩኸታቸው ከፋዮቻቸው እንደሚመኙት ለዚህ ወግ ሳንበቃ ሊያወላልቁን ነውና እንጠንቀቅ። “መንግስት ጭራ ሕዝብ ቀንድ ይሁን” የሚሉን ወገኖች ትናንት “መንግስት ለምን መቀለ ይገባል” በሚል ሲያወግዙ የነበሩ የክህደትና ፖለቲካ መቀንዘሪያው ዋናው ብልቱ ናቸው። እነሱ መንግስት ጭራ ሆኖ ከመሪነት ይልቅ ወደ ተመሪነት ወርዶ ቅንጅት የሰራውን ስህተት እንዲደግምና ቦኖ አገሪቱም እንድትቦን ነው የሚሰሩት።። የዛኔ ቅንጅት ሲሳሳት መንግስትን ወክለው አፈቀላጤ የነበሩና በቅንጅት ስህተት የፖለቲካ ቅንዝራቸውን ሲያሳዩ የነበሩ፣ ዛሬም አይናቸውን በቢጫ በረኪና አጥበው ያንን ስህተት ሊያስደግሙ እየባተቱ ነው። በ”ታሰርኩ” ሰበብ የኋልዮሽ ይህ የክህደት ቅንዝር የሸነቆራቸውና በአንደርቢ መንፈስ ሆነው እያማተቡ ዘመቻ የሚያካሂዱብን እንግዴዎች ጥድፊያቸው ተመሳሳይና የተናበበ ነው።

ኢትዮጵያን የሚሽከረከራት የመጫረስ አዙሪት እንዳይመክን በልቦናቸው መካከል ላይ የተተከለው የክፋት ዕቅድ ስለሚነዳቸው እነሱን እየተከተሉ መንጎድ ሌላ ማለቅያ አልባ ጣጣ እንጂ የተሻለ ውጤት ስለማይጎናጽፈን፣ አገራዊ ምክክሩ ተግባራዊ እንዲሆን ምክክሩ ለሚጠይቀው ማንኛውም መሰዋዕት ከወዲሁ መዘጋጀት፣ ተግባሩ ዋጋ እንደሚያስከፍል መረዳት፣ በፖለቲካ መሰለጠን በማይወዱትና በማይፈልጉት ጭምር የመመራት አማራጭ ሁሉ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ በማመን፣ መዘጋጀት ሲገባ ዝም ብሎ በተቀደደ የክፋትና የወሬ ሰንጣቂዎች ሃሜት መነዳት ዋጋው አድሮ በቁጭት መላላጥ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።

ሲንከባለል የመጣውን ይህን መከራችንን ማን መቋጫ ያበጅለት? ማን ደፍሮ ዋጋ ይክፈልና ያካሂደው? በየትኛው ትውልድ ይጀመር? መቼና እንዴትስ ይጀመር? የሚሉት ጉዳዮችን ባባከናቸው እድሎች ብዛት እያሰላን ስንቆጭ ኖረን ዘሬ ህልማችንን እውን ለማድረግ የተነሱ ሲጀምሩት “እገሌ ለምን ተፈታ፣ እገሌ ለምን ያሳተፋል” በሚል ጉዳይ መንግስትን ጭራ ለማድረግ መሽቀዳደም በየትኛው መስፈርት ትክክል እንደሚሆን ለዚህ ጸሃፊ ግልጽ ግልጽ ነው። የአፈጻጸም፣ የህግ መጣስና ክፍተት ካለ የሽግግር ፍትህ አስፈጻሚ ስለሚቋቋም፣ ይህ አካል ከመንግስት ውጭ ሆኖ በጋራ ምክክሩ የሚሰየም በመሆኑ ማንም በወንጀል የተጨማለቀ አያመልጥምና ለተግባራዊነቱ እገዛ እናዳርግ። ከዚህ ውጭ የመንግስትን ሚና ከቀንድነት ወደ ጭራነት ለመቀየር መታተር አደጋው የከፋ እንደሚሆን ከወዲሁ እንረዳ።

ፎቶ – የመተራመስ ጣጣው ይህ እነደሆነ ለማሳየትና እንደልጅቷ ላሉት ምስኪን ዜጎች፣ በምያውቁት ቤተሰባቸውን ለሚነጠቁ ሁሉ እንድንራራ በማሰብ ነው

በሰለሞ ተፈራ –

ዝግጅት ክፍሉ ይህ አስተአየት የጸሃፊው ብቻ ነው


2 thoughts on ““መንግስት ጭራ ሕዝብ ቀንድ ይሁን!! የመጫረስ አዙሪት ይቀጥል!!””
  1. በጣም የሚመቸኝ ገፅ ነዉ ይህ የናንተዉ ገፅ፤ከልብ ተከታያቹ ነኝ፤ይሁን እንጂ ብዙን ጊዜ የቃላት ግድፈት/ስህተት/ አይበታለዉ፡፡ ብታስተካክሉት ይበልጥ ተወዳጅ ይሆናል፡፡

    አመሰግናለዉ !!

    1. አቶ ልደቱ ትክክለኛ ሃሳብና ጥቆማ ነው። አመስግናለሁ። የትርፍ ሰዓት ስራ ከስደት ሩጫ ጋር ተጋጥሞ ነው አስተካክላለሁ። ክብረት ይስጥልኝ

Leave a Reply to Lidetu Girma Cancel reply