የፌ.ጠ.ፍርድ ቤት በተቋረጡት ክሶች የአሰራር ነጻነቱ እንዳልተነካና የተጣሰ ስርዓት እንደሌለ ህግ ጠቅሶ አስታወቀ

በሶስት የተለያዩ መዝገቦች በፍርድ ሂደት ላይ የነበሩ መዘገቦች ክስ የተቋረጠው ዐቃቢ ሕግ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱን መቀጠል እንደማይፈልግ በማስታወቁ ምክንያት መሆኑንን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። በሂደቱ የህግ ጥሰትም ሆነ ክፍተት እንደሌለ በይፋ አረጋገጠ።ታህሳስ 28፣2014 ዓ.ም በሙሉ ወይንም በከፊል በተከሳሾች ላይ በሶስት መዝገቦች የቀረቡ ክሶችን እንዲቋረጡ የፍትህ ሚኒስትሩ ለሚመለከተው ችሎት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሕጋዊ ስርዓቱን ተከትለው መስተናገዳቸውን ጠቅሶ ያሰራጨው መግለጫ እንደሚክለተለው ይነበባል።

ክስ የተቋረጠባቸው ሶስት የክስ መዝገቦች የስነ-ስርዓት ሂደቶች ላይ የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ

ባለፈው ሶስት ዓመት ተኩል የፌደራል ፍ/ቤቶች በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በተገቢው ደረጃ ለማከናወን በርካታ የለውጥ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ የለውጥ እርምጃዎች ትኩረት ያደረጉት በተቋማዊ እና በግለሰብ ዳኞች ደረጃ የፍ/ቤቱን ነጻነት እና ገለልተኝነት ማስከበር ነው፡፡ በተጓዳኝም ለተጠያቂነት ተቋማዊ ስርዓቶች ተዘርግተዋል፡

በፍ/ቤቱ አመራሮች እና ዳኞች በኩል ሲደረግ የነበረው ጥረት ዋናው ግብ የሚሰጠው የዳኝነት ዘርፍ ቀልጣፋ፣ ተገማች እና ተደራሽ በማድረግ በፍ/ቤቱ አገልግሎት ላይ የሕዝብ አመኔታ እንዲጨምር ነው፡፡ በዚህ ወር መጨረሻ በሚዘጋጀው “የፍ/ቤቱ አሁናዊ ሁኔታ” ጉባዔ እንደሚገልጸው በተለያየ ደረጃ የፍ/ቤቱ አገልግሎትም ሆነ ተደራሽነት እያደገ የመጣ ለመሆኑ ፍ/ቤቱ በገለልተኛ የጥናት ተቋም የሰራው የሕዝብ አስተያየት ሰርቬይ “public perception survey” አመልክቷል፡፡

ይህም ሆኖ የዳኝነት ዘርፉ አገልግሎት በርካታ ሰብዓዊ ግብዓቶች ያሉበት የስራ ዘርፍ ከመሆኑ አኳያና እንደሌሎች ተቋሞቻችን ሁሉ ተግዳሮቶቹ በርካታ በመሆናቸው ስራችን በውሱን ዓመታት የሚጠናቀቅ ሳይሆን እያደገ የሚሄድ ውጤት እያመጣ ያለ ዘርፍ ነው፡፡ ፍ/ቤት እንደ ሶስተኛው የመንግስት ዘርፍ አገራችን በጦርነት እና በተለዋዋጭ የፖለቲካ ዓውድ በማለፍ ላይ የምትገኝ ቢሆንም በሃገራችን ዘላቂ ልማት እና ሰላም እንዲረጋገጥ የህግ የበላይነት በማክበርና በማስከበር ረገድ የሚጫወተው ሚና እየተጠናከረ እንዲሄድ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ድጋፋቸው እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለን፡፡

ለዚህ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የፕሬስ መግለጫ ምክንያት በቀን 28/4/2014ዓ.ም ዐቃቢ ሕግ ክስ እንዲነሳ ለፍ/ቤት ማመልከቻ በማቅረብ ክስ የተነሳባቸው ሶስት መዝገቦች የስነ-ስርዓት ሂደቶች አካሄድ ላይ የፍ/ቤቶች ሚና ምን እንደነበረ ሕዝቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ በማስፈለጉ ነው፡፡

ግለሰቦች መብታቸውን ለመጠየቅ ወደ ፍ/ቤት የሚያመጧቸው የፍትሐብሔር ጉዳዮችም ሆኑ በዐቃቤ ሕግ በኩል የሚቀርቡ የወንጀል ጉዳዮች ሁሉ በፍ/ቤቶቻችን እና በዳኞቻችን በልዩ ጥንቃቄ የሚታዩ ናቸው፤ መታየትም አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን የህዝብ ፍላጎት ያለባቸው ጉዳዮች “በሕዝብ እይታ ውስጥ ያሉ” በማለት በተቻለ ቅልጥፍና እንዲታዩ፣ ሂደታቸውም የስነ-ስርዓትም ሆነ ዋና ሕጎችን ተከትለው እንዲከናወኑ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የአመልካቾች የምርጫ ጥያቄን በተመለከተ፣ የተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ እና የሕክምና አገልግሎት ጥያቄ በተመለከተ፣ እንዲሁም የምስክሮችን ከመጋረጃ ጀርባ ይሰሙ/ አይሰሙ የሚሉትን እና ሌሎች አስቸጋሪ ክርክሮችን ዳኞቻችን ተገቢ ነው ያሏቸውን ብይን አሳርፈውባቸዋል፡፡ እነዚህ እና መሰል ጉዳዮች ለጥናት እና ምርምር እንዲሁም የሕግ ፍልስፍና ማደግ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ፍ/ቤቱ በነጻነት የመስራት ደረጃ ላይ ለመድረሱ አመላካች ውሳኔዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ታህሳስ 28/2014 ዓ.ም በሙሉ ወይንም በከፊል በተከሳሾች ላይ በሶስት መዝገቦች የቀረቡ ክሶችን እንዲቋረጡ የፍትህ ሚኒስትሩ ለሚመለከተው ችሎት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሕጋዊ ስርዓቱን ተከትለው ተስተናግደዋል፡፡ ጉዳዮቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡

=በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሾች እነ ጀዋር ሲራጅ መሀመድ (በድምሩ 20 ተከሳሾች)

– በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተካሾች እነ እስክንድር ነጋ (በድምሩ 7 ተከሳሾች) እንዲሁም

– በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሾች እነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (በድምሩ ስድስት ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ) የሚመለከቱ ክሶች እንዲቋረጡ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሕገ-መንግስት እና ሽብር ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት የፍትህ ሚኒስትሩን ማመልከቻ በመመርመር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3)ሠ መሰረት ክሱን ያነሱ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ተከሳሾቹ እንዲለቀቁ “ተከሳሾች በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ” ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ለማረሚያ ቤት አስተላልፏል፡፡

አሁን በስራ ላይ ባለው ሕግ መሰረት ከሳሽ ዐቃቢ ሕግ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱን መቀጠል እንደማይፈልግ ሲያመለክት ፍ/ቤቱ የክስ ይቋረጥ ጥያቄውን በመቀበል በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ የታዘዘ መሆኑ ሕጋዊ አሰራር መሆኑ ግንዛቤ እንዲፈጠር ይህ የፕሬስ መግለጫ ወጥቷል፡

የፌዴራል ጠ/ፍ/ቤትጥር 2 ቀን 2014 ዓ.ም


Leave a Reply