(ዮሐንስ መኮንን)

የመስቀል አደባባይ ላይ የሚነሣውን የባለቤትነት ጥያቄ በሕግ፣ በታሪክ እና በትውፊታዊ ዳራ አገናዝቦ አስታርቆ ከመመለስ ይልቅ በጉልበት በመደፍጠጥ ወይንም ከዐውዱ ውጪ የሆኑ የሞራል እና የክስተቶች ማሳያ በመደርደር ማጣጣል ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እና አማኙን ሕዝብ ከማስከፋት አልፎ ችግሩን ያወሳስበው ይሆናል እንጂ በዘላቂነት አይፈታውም። ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት እንዲያመቸን ጉዳዩን ትንሽ አፍታትን እንመልከተው !

1) መስቀል አደባባይ በታሪክ ዐውድ

በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት የመስቀል ደመራ በዓል ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በስተደቡብ ወረድ ብሎ በሚገኘው ክፍት ቦታ ላይ ይከበር ነበር። (መርስኤ ኀዘን ወልደቂርቆስ በዘመን ትውስታ)

በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ከቤተመንግሥቱ በስተደቡብ መኖሪያቸውን ያደረጉት (የአሁኑ አዲስ አበባ ሙዝየም) ራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ከግል ርስታቸው ከፍለው ቀድሞ በነበረው የእንጦጦ ኪዳነ ምህረት ይዞታ ላይ ጨምረውበት ለመስቀል ደመራ ማክበሪያ አደባባይ እንዲሆን ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሰጡት መሠረት የደመራው አደባባይ ከጊዮርጊስ አደባባይ ወደ አሁኑ መስቀል አደባባይ ተዛወረ።

የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ በጉልበት ከወረሳቸው የቤተክርስቲያኒቱ አደባባዮች እና ይዞታዎች አንዱ ይኸው መስቀል አደባባይ ሲሆን ስያሜውን ወደ “አብዮት አደባባይ”ነት በመቀየር የደመራውን ሥርዓት ከአደባባዩ ነጥሎ ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መለሰው።

ኢህአዴግ አዲስ አበባን ለመቆጣጠር አንድ ሳምንት ሲቀረው ሀገሪቱን ለ6ቀናት ብቻ በማስተዳደር የሚታወቁት ጀነራል ተሥፋዬ ገብረኪዳን አብዮት አደባባይ የሚለውን ስያሜ በመሠረዝ ወደቀደመ ስያሜው (መስቀል አደባባይ) መለሱት።

ኢህአዴግ ሀገሪቱን ግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. ላይ ሲቆጣጠር ከአራት ወራት በኋላ የመስቀል ደመራ በዓል በጥንታዊ ይዞታው በአሁኑ መስቀል አደባባይ ተከብሯል። እስከ አሁንም በዚሁ ቦታ ላይ እየተከበረ ይገኛል።

2) መስቀል አደባባይ በሕግ ዐውድ

በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚቀባበሉት ከታች ያያዝኩት የዲዛይን ሠነድ የተዘጋጀው ለቦሌ መንገድ ግንባታ ሆኖ በንድፉ ላይ የተቀመጠው መግለጫ በግልጽ እንዲሚነበበው መስቀል አደባባይ አስቀድሞ የእንጦጦ ኪዳነምሕረት ገዳም ይዞታ መሆኑን ያመለክታል። ቅንነቱ ካለ መዘጋጃ ቤት ያሚገኙትን ነባር ሠነዶች ገልበጥ ገልበጥ ቢደረግ በርካታ ተጨማሪ ሰነዶች እንደሚገኙ ጥርጥር የለውም።

በአደባባዩ ላይ ግንባታ ሥራ ከዓመት በፊት ሲጀመር የቦታው ሕጋዊ፣ ታሪካዊ እና ትውፊታዊ ባለቤት የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የወቅቱ ከንቲባ የነበሩት ኢንጂነር ታከለ ኡማ የከተማ አስተዳደሩ ቦታውን እንዴት ሊገነባ እንዳሰበ ሐሳብ እንድትሰጥበት የዲዛይን ሰነዶቹንም ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በማቅረብ ቤተክርስቲያኒቱ ምክሯን ማካተቷ ይታወሳል።

በተጨማሪም ቤተክርስቲያኒቱ የዲዛይን እና የግንባታ ሥራው ከትውፊቱ የተቃረነ እንዳይሆን ባለሙያዎች መድባ እንድትከታተል ተጠይቃ ነበር። በዚህም መሠረት እኔን ጨምሮ አምስት ያህል ባለሙያዎች ሥራውን እስከፍጻሜ ስንከታተል ቆይተናል።

ቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ የባለቤትነት መብት ባይኖራት በዚህ ርቀት ከዲዛይን እስከ ግንባታ ክትትል ባለሙያ መድባ የመሳተፍ መብት ፈጽሞ ሊኖራት አይችልም ነበር።

3) መስቀል አደባባይ በትውፊት ዐውድ

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ መንፈሳዊና ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና ክብካቤ ላይ የሚሠራው ኮሚቴ ስምንተኛውን ጉባኤ የአዘርባጃኗ ባኩ ከተማ ሲያሒድ መስቀልን በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት መዝግቦታል፡፡

በኮሚቴ የውሳኔ ሐሳብ ላይ እንደተመለከተው የመስቀል ክብረ በዓል የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን የያዘ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ መምጣቱና በአገሪቱ ማኅበራዊ አንድነትንና የእርስ በርስ ትስስርን፣ ብዝኃነትን የሚያንፀባርቅ፣ በበርካታ ብሔረሰቦች ባህሎች መካከል ትስስርን የፈጠረ በመሆኑ ዓለም አቀፍ መስፈርቱን አሟልቷል ብሎታል፡፡ በዚህ ዐውድ (Context) በዓሉ ከአደባባዩ እና ከባለቤቱ የማይነጣጠል ሆኖ እናገኘዋለን።

4) የችግሩ ምንጭ ምንድነው?

አንዳንዶች በቅንነት ሌሎች ደግሞ በሸፍጥ የሚያቀርቡት አንደኛው መከራከሪያ “በአደባባዩ ሲዘፈንበት ዝም ብለው ለአምልኮ ሲሆን ከለከሉ” የሚለው ነው። በመሠረቱ ቤተክርስቲያኒቱ ለጭፈራው ፈቃድ ተጠይቃ ሰጥታ ታውቃለች ወይ? በፍጹም። ፈቃጁም ከልካዩም የከተማ አስተዳድሩ ነው። በእኔ እምነት ችግሩ የከተማ መስተዳድሩ እንጂ የቤተክርስቲያኒቲ አይደለም።

ከተማ አስተዳደሩ ጉዳዩን በውይይት ለመፍታት ሲጠየቅ ዳተኛ ነበር። እንደ ባለድርሻ አካል ቤተክርስቲያኒቱን ሲጠራትም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሳይሆን በለበጣ መሆኑን የሚያሳይ ነው። የመስቀል አደባባይን ጨምሮ በተለያዩ የእምነት እና የማኅበረሰብ ክፍሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን የህዝብ አደባባዮች በዘላቂነት መፍታት ውዝፍ የቤት ሥራውቸን ያልሠሩት ፖለቲከኞቹ ናቸው።

5) መፍትሔው ምንድነው?

ቅንነቱ ቢኖር በመከባበር እና በመተባበር የመስቀል አደባባይን ለሃይማኖታዊ፣ ለማኅበራዊ፣ ለባህላዊም ሆነ ለፖለቲካዊ የአደባባይ ሁነቶችን ማከናወኛነት በጋራ ለመጠቀም አደባባዩ የሚጠብበን አልነበረም። የእምነት ተቋማቱ መሪዎችም ከመበሻሸቅ እና ከ “ሠራንላቸው፣ አሳየናቸው” ዓይነት መናናቅ ይልቅ መገናዘቡ እና መከባበሩ ቢኖር ለሁሉም በተገቢው መንገድ በጋራ ለመገልገል ቤተክርስቲያኒቱ የምትቃወም አይመስለኝም።

ሌላኛው ችግር ባለሥልጣኖቻችን በአንድ እግራቸው ፖለቲካ በሌላኛው እግራቸው የአንደኛው ቤተ እምነት አጋፋሪ እና ጠበቃ ከመሆናቸው የሚመነጭ ነው። አሁንም #መፍትሔው የቤተክርስቲያኒቱን ሕጋዊ፣ ታሪካዊ እና ትውፊታዊ ባለቤትነት በመቀበል በጋራ አጠቃቀም አማራጮች ላይ የሰከነ ውይይት ማድረግ ብቻ ነው እላለሁ።

ማጠቃለያ

በየዓመቱ በመላ ሀገሪቱ በአደባባይ የሚከበረው የመስቀል ክብረ በዓል የማክበር ትውፊት የቤተክርስቲያኒቱ መሆኑን የሚያጠያይቅ አይደለም። ይህንን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከትሎ ከቱሪዝሙ እና ከእውቅናውን የሚገኘውን የተትረፈረፈ በረከት እያፈሱ ቢያንስ የባለቤትነት መብትን መግፈፍ ባለጊዜነት የተጠናወተው አምባገነንነት ብቻ ሳይሆን ህሊናቢስነት ነው እላለሁ።


ማሳሰቢያ፡

ይኽ ጽሑፍ የሚያንጸባርቀው የግል እምነቴን እና አመለካከቴን ብቻ ነው።

Leave a Reply