ልጅ እያለን የማውቀው – “መምህር ምህረተአብ አሰፋ እንዴት በእድሜ ቆይታ አይበስልም?”

«እንዴት በእድሜ ቆይታ አይበስልም? እሱ ያስተማራቸው የኛ ታላቆች ትልልቅ ሆነው አግብተው ወልደው ሰክነዋል ፣ እኛ የነሱ ታናሾች አድገን ነገሮችን አገናዝበን ከስሜታዊነት ርቀን ነገሮችን ማየት ጀምረናል። እሱግን እዛው ነው። አሁንም ” የቤተክርስቲያን የቁርጥቀን ልጅ አፄ ዮሀንስ” የሚለው ስብከቱ ላይ ነው»

ታዲዬስ አለማየሁ የተባለ ወጣት በፌስቡክ ይህን ፅሁፍ ፖስት አድርግዋል

ያደግኩት ሩፋኤል ሰፈር ነበረ። ሰፈሩ ስሙን ያገኘው በደብሩ ነው። እዛ ደብር የሰንበት ተማሪ ሆኜ ፣ ቆርቤ ፣ ዘምሬ ፣ ሰግጄ ፣ አስቀድሼ አድጌያለሁ።
.
እኛ ጩጬ እየነበርን የኛ ታላላቅ እህት ወንድሞቻችን ሀይስኩል ተማሪ በነበሩበት ሰአት ፤ አንድ አዲስ ሰባኪ ሩፋኤል ደብር መጣ ተባለ። ሀሙስ ሀሙስ ግቢዋ ሲጥ ብላ ትሞላለች። በሌሎቹ ቀናት የዛን ያህል ሰው አይታደምም። ሀሙስ ሲሆን ግን ለአዲሱ መምህር ግቢዋ በሰው ትሞላለች። አዲሱ መምህር ወጣት ፣ አዝናኝ ፣ ሀይለኛ ነበረ።
.
ያ አዲስ መምህር ምህረተአብ አሰፋ ነበረ። በዛንወቅት እሱ እራሡ አፍላ ወጣት ነበረ። እኛ ልጅ ስለሆንን የማታ ጉባኤ ለመታደም አይፈቀድልንም። እሱን የምናውቀው በታላላቆቻችን ወሬ ነበረ። ምናልባት አንዳንዴ እነሱ ይዘውን ሲሄዱ ካልሆነ በቀረ ብዙም የእሱን ስብከቶች የመታደም እድል አልነበረንም (በግሌ አልነበረኝም)
.
ያው የቸርቿ ፖለቲክስ ውስብስብ ስለሆነ በሆነ ግጭት ሳይስማማ ቀርቶ ደብር ቀየረ ተባለ። ደብር ቀይሮ አቶቢስተራ ያለው አዲሱ ሚካኤል ገባ። በሚካኤል ልጆች ቀናንባቸው። እዛም እንደ ሩፋኤሉ ሰዉ በግፊያ የሚመጣለት ሰው ሆነ።
.
ግዜ ሄዶ እኛም እያደግን ስንመጣ ምረታብን የማግኘት አጋጣሚዎቻችን እየሰፉ መጡ። አልፎ አልፎ በተጋባዥ መምህርነት እየመጣ ሩፋኤል ይሰብክ ጀመረ። እኔም ራሴንችዬ ጉባኤ አምሽቼ መመለስ የሚፈቀድልኝ እድሜላይ ደርሼ ነበርና በአካል ተገኝቼ ትምህርቱን ለማድመጥ በቃሁ።
.
ምረታብ ሲሰብክ ሰው ለምን ተጋፍቶ ይመጣል? ሌሎቹ ሲሰብኩ ለምን የዛን ያህል ሰው አይመጣም? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ምረታብ ስብከትን ሲሰብክ በግእዝ ምናምን እያወሳሰበ ሳይሆን በሚገባንና ልንረዳ በምንችለው ቋንቋ እና በሚገራርሙ ቀልዶች እያዋዛ ስለነበረ ነው። አብዛኛው ወጣት እሱን የሚወደው ሲሰብክ ስለሚያስቅ ነው። ከስብከቱ በሗላ እያስታወስን የምናወራውም ስለ ቀልዶቹ እና ያለፍራቻ ስለሚሰነዝራቸው ነቆራዎች ናቸው። ነቆራዎቹ አብዛኛውን ግዜ የሚያተኩሩት ሙስሊሞችላይ ነበሩ። በዚህ ነገሩ እንገረምበት ነበረ። ደፋር ነውኮ እንል ነበረ። ብዙ ግዜም ከስብከቱ በሗላ የምንወጣው በጣም ተሟሙቀን ነበረ።
.
ሩፋኤል ቤተክርስቲያኑ አጠገብ (ሁለትመቶ ሜትርንኳን መራቁን እንጃ ) ሼ ሁጀሌ መስጊድ አለ። የእኛ መኖሪያም ያለው ከመስጊዱ ጀርባ ነው። ወጣቱ ክፍል ሸቃዩም ፣ ረዳቱም ፣ ሹፌሩም ፣ ነጋዴውም ፣ ወንበዴውም ከሁለቱ ሀይማኖቶች የተቀላቀለ ነው። ቤተሰቦቻችን በኑሮ ደረጃ ልዩነት ምክንያት መቀራረብ ቢያቅታቸው ራሡ እኛ ልጆቹና የኛ ታላላቅ ወጣቶቹ ግን ትስስር ነበረን። እና የነ ምረታብ ስብከት እዛ ትስስር ላይ ሆነ ትኩረቱ። በእያንዳንዱ ስብከቱ የሚነግረን ሰዎቹ ሊያጠፉን ቀን እየጠበቁልን እንደሆነ ነው። አንድ የወንድሙ መዝሙር አለች እንደውም ሁሌ የሚዘምራት። ግጥሙንም እሱ ነው የሠጠው ይባላል
“የሉም ሞተዋል ሲሉን ኖረን
የሉም ጠፍተዋል ሲሉን በዝተን
አለን በእግዚአብሄር ሁሉን አልፈን
አለን በጌታ ሁሉን አልፈን….” የምትል
መዝሙሯ እንደ መቀስቀሻ ናት። በጠላት ተከበህ ነው ያለኸው እያለ ሁሌ ስለሚሠብክ ወጣቱ ደህንነት እንዳይሰማው መሆን ጀመረ። ያጠፉኝ ይሆን የሚል ስጋት በፈጠረበት ስሜት ተነስቶ ፤ መኖሩን እና ሀይለኛ መሆኑን ለማሳየት የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ ጀመረ። ለጥምቀት ፣ ለበአላት ፣ ለንግስ ሰፈሩን ማደማመቅ ፣ ሙስሊሙን ለማብሸቅ ከቤተክርስቲያኑ ቅፅር ውጪ ሞንታቮዎችን በማቆም ሰፈሩን በሰባኪው ድምፅ ማናወጥ ፣ ቲሸርት አሰርቶ በጋራ መልበስ ምናምን እንደፋሽን ሆኖ ተጀመረ። ይሄኔ ወጣቱ ወደ እምነቱ እየተመለሠ ነው ተባለ። እነ ምረታብ ተወደሱ። የዚያ አይነት ምልሰት ጥልቀት እንደሌለውና የታይታ ብቻ መሆኑን ግን ጥቂቶች ብቻ ነበሩ የሚያውቁት። አንድ የማውቀው ፓስተር ነበረ በሰአቱ በሁኔታቸው ያላገጠ “አሪፍኮነው ስራቸው ። ቀን ለታቦቱ ምንጣፍ ሲያነጥፉ ውለው ማታ ሰክረው እርስበራስ ባይነጣጠፉ ኖሮ” ብሎ እውነቱን ነበረ። ወጣቱ ሀገር ይያዝልኝ ብሎ የሚወክበው ለሁለትና ለሶስት ቀን ነበረ። ከዚያ ክብረ በአሉ ሲያልፍ ወደ ውንብድናው ፣ ወደ ሱሱ ይመለሳል አለቀ። ከዛ ደግሞ ሌላ በአል ተመልሶ ይመጣል። ይሄን እንደ ስኬት ቆጥረውት ነበረ። ወጣቱን የአውዳመት ማድመቂያና የጎረቤት መተናኮሻ ማድረግ በምን ቀመር ስኬት እንደሆነ እንጃ።
.
እየቆየሁ እያደግኩ ስመጣ ፤ ክርስትና ምን እንደሆነ እየተረዳሁ ስመጣ የብዙ ሰባኪዎቻችን ሁኔታ ያሳስበኝ ጀመር። ከሁሉ በላይ ደግሞ የምረታብ ሁኔታ የከፋ ነበረ። የሆነቀን እየሰበከ “ጀግናው የቤተክርስቲያን የቁርጥቀን ልጅ አፄ ዮሀንስ” ብሎ ስብከቱን ሲቀጥል በተቀመጥኩበት ድርቅ አልኩኝ። ኮራ ብሎ እያወራ የነበረው ስለ አፄ ዮሀንስ የሀይማኖት የማስቀየር ዘመቻ ነበረ። በሰአቱ በፍፁም ከአንድ ሰባኪ የምጠብቀው ነገር አልነበረም። እኔኮ በዛች እድሜዬ የአፄ ዮሀንስ ድርጊት ከማንም በላይ ቤተ ክርስቲያኗን እንደጎዳት ነበረ የማስበው። አንድ ኦርቶዶክስ በእሳቸው ስራ መኩራት ሳይሆን መሸማቀቅ ነበረ ያለበት ብዬ የማስብበት ሰአት ነበረ። ክርስቶስ ስለፍቅርና ስለፍቅር ብቻ ነው ያስተማረው እያልን በምን መስፈርት ነው በጦር መስፋፋትን የምናበረታታው? የወደደ ቢኖር ይምጣ ተባለ እንጂ ሳይወድ በግዱ አምጣው የሚል አስተምህሮ የለንም በሰአቱ። ምናልባት የማንቂያው ደውል ለመጀመሪያ ግዜ የሰራው ያኔ ነበረ መሰለኝ እሱም ለኔ ነው እኔ መጠራጠሬን ስጀምር የጀመርኩት ከዚህች ነበረ ማለት እችላለሁ። ከፈጣሪ ቀድሜ ሰባኪዎቹን ነው መጠራጠር የጀመርኩት።
.
ምናልባት ስለአፄው ያነሳሁት ላይ ትንሽ ውዥንብር ሊሰማዎ ከቻለ ግልፅ ላርገው። አፄውን የኮነንኩት ከክርስትና አንፃር ብቻ ነው። ክርስትና በዛ መልኩ አስፋፉኝ ስለማይል። በተረፈ ከሀገረ መንግስት ግንባታ እሳቤያቸው አንፃር ካየነውና ፖለቲካሊ ከዳኘነው ጥሩም መጥፎም ጎኖች ይኖሩታል።
.
አሁንም ግዜ ሄደ እኛም አድገን ጉርምስናውንም አልፈን ወጣትነቱላይ ዘልቀን ብዙ አስተሳሰቦቻችንን ፣ ብዙ አቋሞቻችንን ቀያይረን። አመለካከታችን ሰፍቶ ዛሬላይ ደረስን። አንድ ሳይለወጥ በነበረበት ሆኖ የቆየን ነገር ቢኖር መምህር ምረታብ ብቻ ነበረ። ያኔ ልጅ ሆኜ እንደታዘብኩት እንደዚያው ሆኖ ነው የጠበቀኝ። ለሌላው እምነት ያለው ንቀት እና ንቀቱን የሚያንፀባርቅበት መንገድ አለመቀየሩ ያስገርመኛል። እሱን እንተወውና ወጣቶቹን በለብለብ ሆይሆይታ ማንጋጋት አሁንም ትልቅ መንፈሳዊ ስኬት ሆኖ ነው የሚታየው። መንፈሳዊነት እንዲህ ነውእንዴ? ሰው እንዴት በእድሜ ቆይታ አይበስልም? እሱ ያስተማራቸው የኛ ታላቆች ትልልቅ ሆነው አግብተው ወልደው ሰክነዋል ፣ እኛ የነሱ ታናሾች አድገን ነገሮችን አገናዝበን ከስሜታዊነት ርቀን ነገሮችን ማየት ጀምረናል። እሱግን እዛው ነው። አሁንም ” የቤተክርስቲያን የቁርጥቀን ልጅ አፄ ዮሀንስ” የሚለው ስብከቱ ላይ ነው።
.
አንድ በጣም ትልቅ ጥያቄ የሚሆንብኝ ይሄንን የተጠቂነት ስነልቦና ከየት እንዳመጣው ብቻ ነው። ኦርቶዶክስ እንዲህ አይነት ስነልቦና አልነበረውምኮ።

ልጅ እያለን ነው

Via – Walya press

Leave a Reply