የአብኣላ ፖለቲካ – አዲሱ የቅውስ እምብርት

አብዓላ አዲስ የፓለቲካ ትኩሳት ሆናለች። የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የትግራይ ሕዝብ ተዘግቶበት እየተሰቃየ እንደሆነ ሲገልጹ፣ የአፋር ክልል በበኩሉ ” ያውቁታል” ሲል ክሳቸው የተንኮል መሆኑንን አመልክቷል። ከሁሉም አቅጣጫ የሚወጣው መረጃ ግን ለድሃውና ለምስኪኑ ህዝብ የሚጠቅም እንዳልሆነ ያነጋገርናቸው ሰፊ አስተያየት ሰጥተውናል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም  ” ሰባት ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርበት የትግራ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ ሙሉ በሙሉ ከበባ ውስጥ እየኖረ ነው” ማለታቸውን ጠቅሰው በርካታ የውጭ አገር መገናኛዎች ዘግበዋል። ይህንኑ ተከትሎ የአፋር ክልል አዳአር ወረዳ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዶ አሊ ምላሽ ሰጥተዋል።

በከበባው ምክንያት የትግራይ ሕዝብ የምግብ አቅርቦት፣ የህክምና ፣ ኤሌክትሪክ፣ የስልክ ፣ የመገናኛ አገልግሎት እንደማያገኝ ዶክተር ቴዎድሮስ አመልክተዋል። ይህ ከበባ እንዲሰበር የሚጠይቅ አቤቱታም አሰምተዋል። ይህን ሲሉ በአባልነትና በስራ አስፈጻሚነት ሲመሩት የነበረው ትህነግ ስለፈጸመውና እያፈጸመው ስላለው ተግባር ያሉት ነገር የለም።

በመድሃኒት አቅርቦት እጥረት ምክንያት ሰዎች እየሞቱ መሆኑንን። በምግብ እጥረት ምክንያት እንደዚሁ ብዙዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ፣ በተጨማሪም በየቀኑ የሚሰነዘረው የድሮን ጥቃት የሰው ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑንን ጠቅሰዋል። ዶክተሩ ከዚህ ቀደም አንድም ቀን በአፋርና በአማራ ክልል ለደረሰው ውድመትና በደል፣ በተለይም ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች አመድ ሲሆኑ ከሚመሩት ድርጅት መርህ አንጻር ዝም ማለታቸው ክፉኛ አስወቅሷቸዋል። በዚሁም ሳቢያ ለሚመሩት ተቋም አቤቱታ መቅረቡ አይዘነጋም። አሁንም በድጋሚ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ እንዲገመግማቸው ተጠይቋል።

በርካቶች በትግራይ ሕዝብ ችግር ላይ መውደቁን፣ በስልክም ሆነ በተለያዩ አገልግሎቶች ተጎጂ መሆኑና እርዳታ እንደሚስተጓጎልበት ቢያምኑም፣ ዶክተሩ አንድም ቀን ትህነግ ስለሚዘርፈው እርዳታ፣ የእርዳታ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ሲወቅሱ አለመሰማታቸው ሃላፊነታቸውን ከምግባር ውጪ በመጠቀም እንዲከሰሱ አድርጓቸዋል። ” ዓለምን እየመሩ ወረዳና ጎጥ ስር የተወተፉ” በሚል ያጣጥሏቸዋል። እነዚህ ግለሰቦች እንደሚሉት ዶክተር ቴዎድሮስ በተቀመጡበት መቀመጫ ሁሉንም እኩል በማየት የመፍትሄ አካል ሊሆኑ ይገባ እንደነበር ይናገራሉ።

ለዚህ ይመስላል የአፋር ክልል አዳአር ወረዳ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዶ አሊ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ዕርዳታ ወደ ትግራይ የሚያልፈው በአፋር  አብዓላ በኩል እንደሆነ ጠንቀቀው እንደሚያውቁ አስታውቀው ትችት የሰነዘሩት። እሳቸው እንደሚሉት በአብዓላ በኩል በቅርብ ጊዜ ምን፣ ለምንና እንዴት እንደተጀመረ ለዓለምም ለዶክተሩም ግልጽ ነው።

“አሁን ላይ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባበት አማራጭ መንገድ የለም፤ ለምን ? በአፋር አብአላ በኩል ያለውን ጦርነት እራሳቸው ከፍተው በአብአላ በኩል ጦርነት እያካሄዱ ነው፤ በቆቦም በኩል ጦርነት እየተካሄደ ነው” ሲሉ አቶ አብዶ አሊ ያስረዳሉ።

ወደ ትግራይ እርዳታ ማስገቢያ በሮቹ በአፋር በኩል መሆናቸውን ያመከቱት አቶ አብዶ፣ “እራሳቸው ጦርነት ከፍተው፣ ወረራ አድርገው፣ አብዓላ ከተማን እስካሁን ድረስ በመድፍ እየደበደቡ ስለሆነ እርዳታ የሚገባበት አማራጭ የለም” በማለት ለዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም አቤቱታ ምላሽ ይሰጣሉ።

“እሱ” ሲሉ የጠሯቸውን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን፣  ለህወሓት ፕሮፖጋንዳ ብለው እንጂ የመግቢያ መንገዶቹ በሙሉ ማን ለምን የጦርነት ቀጠና እንዳደረጋቸው ያውቃሉ ” ባይ ናቸው።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጅዓለም ” ህወሓት ቀበሌ ከምትገኝ የጤና ኬላ ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሆስፒታሎች ድረስ የሚችለውን ዘርፎ መውሰድ የማይችለውን አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጎ አውድሟል” ሲሉ ያስታውሱና “ይሄ እንግዲህ መላው የዓለም አቀፍ ተቋማት በግላጭ የሚያውቁት ነው። ይህን እንኳን ሲያወግዙ አይሰማም” ሲሉ ይከሳሉ።

“በተመሳሳይ ጠላት ከወጣ በኃላ እነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የመድሃኒት ችግር ፣ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችል ቁመና ላይ አይደሉም፣ ጤና ተቋማቱ መልሶ ለማቋቋም የዓለም ጤና ድርጅት አንድም አስተዋጽዖ እያበረከተ አይደለም ” በማለት የድርጅቱን መሪ ሚዛን አልባነት ያመለክታሉ።

“የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነታቸውን ለግል ፖለቲካ መጠቀሚያነት አውለውታል።የሽብር ቡድኑ ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ሽብር በግልፅ እንሚደግፉም በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ካወጧቸው ፅሁፎች መረዳት ይቻላል ” 

ትግራይ በሰቆቃ ውስጥ መኖሯ ምንም የሚያከራክር እንዳልሆነ የገለጹልን እንደሚሉት ከሆነ የአብኣላ ውጊያ አዲስ ግንባር እንዲሆን የተፈለገው በወልቃይት በኩል ኮሪዶር እንዲከፈት ለተጀመረው ትንቅንቅ አጋዥ እንዲሆን እንጂ ትህነግ በዚህች አነስተኛ ከተማ ላይ ውጊያ የሚከፍትበት ምንም ትርፍ የለውም። አጀንዳው ዕርዳት እንዳይገባ አንድ ያለው ብቸኛ መንገድ ተዘጋ በሚል ለሱዳን ድንበር መከፈት የሚከናወን ነው። ይህን አጀንዳ ለማስፈጸም ግን የትግራይ ሕዝብ በማንኛውም ሰው ሰራሽ ችግር የሚያልቅበትና መከራ የሚከፍልበት ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነላቸው፣ እስከመቼስ የትግራይ ሕዝብ በዚህ መልኩ የፖልቲካ ቁማር ሰለባ ሆኖ እንደሚኖር ሲያስቡት ሃዘን እንደሚሰማቸው ያስታውቃሉ።

Leave a Reply