ኢትዮጵያ ቴዎድሮስ አድሃኖም በስነምግባር ደንብ ጥሰት እንዲመረመሩ ጠየቀች

ኢትዮጵያ የአሸባሪው ህወሓት አባልና የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም የድርጅቱን የአሰራር መርህ እና የስነምግባር ደንብ በመጣስ እየፈፀሙት ያለውን አድሎ እንዲመረምርላት የድርጅቱን ስራ አስፈፃሚ ቦርድ ጠየቀች።

ኢትዮጵያ ለድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ በላከችው ደብዳቤ ፣ዳይሬክተሩን ለቦታው በማጨቷ ደስተኛ ብትሆንም ሌሎች ሃገራትና የድርጅቱ ሰራተኞች ድጋፋቸውን በመግለፃቸው ምስጋና ያቀረበች ቢሆንም ዳይሬክተሩ ግን የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ግዴታ እየተወጡ አይደለም ብላለች።

ዶክተር ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ መሆኑ በደብዳቤው ተገልጿል፡፡ እንዲሁም ሽብርተኛ ተብሎ በኢትዮጵያ ፓርላማ ለተፈረጀው የሽብር ቡድኑ ህወሃት አባል እና ደጋፊ መሆናቸውን ቀጥለውበታል ብሏል፡፡

የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነታቸውንም ለግል ፖለቲካ መጠቀሚያነት አውለውታልም ነው ያለው ደብዳቤው፡፡ የሽብር ቡድኑ ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ሽብር በግልፅ እንሚደግፉም በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ካወጧቸው ፅሁፎች መረዳት ይቻላል ነው ያለው ደብዳቤው ።

ዋና ዳይሬክተሩ ጥፋታቸውን ያቆማሉ ተብሎ ተስፋ ቢደረግም ከድርጊታቸው እንዳልተቆጠቡ ገልጿል። የድርጅቱ ዳይሬክተርነትን በመጠቀምም የተመድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ በጠላትነት እንዲንቀሳቀሱም መሥራታቸውን አስረድቷል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ ጉዳይ በተመለከተ ሲያነሡም አድሎ በማድረግ የፈለጉትን ብቻ እንደሚመርጡም ነው የተመለከተው።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዓለም ጤና ድርጅት የዳይሬክተሮች ቦርድ በላከው በዚህ ደብዳቤ ግለሰቡ ለዚህ ወንጀላቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ህጋዊ ሂደት መጀመሩን አስታውቋል። በመሆኑም ዋና ዳይሬክተሩ የሙያ ስነምግባር እና ከዓለም ጤና ድርጅት የአሰራር እና ስነምግባር መመሪያን የጣሰውን ተግባራቸውን እንዲመረምር እና የሚወስደውን እርምጃ እንዲያሳውቅ ጠይቋል ደብዳቤው።(ኤፍ ቢሲ)

Leave a Reply