• የምድር ድሮኖቹ አሁንም ቢሆን ጁንታውን በሚገባው ቋንቋ እያናገሩት ሲሆን ያደረጋቸውን ተደጋጋሚ ሙከራዎች በማክሸፍ ቡድኑ ወደ አፋር ክልል ዘልቆ እንዳይገባ ብርቱ ተጋድሎ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

የህወሓት የሽብር ቡድን በሰላም ወዳዱ የአፋር ህዝብ ላይ በድጋሚ እያካሄደ ያለውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በአስቸኳይ ሊያቆም እንደሚገባ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አሳሰበ፡፡ ክልሉ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ መግለጫ አውጥቷል፡፡

አሸባሪው ህወሀት በኪልበቲ ረሱ /ዞን ሁለት/ በአብአላ በኩል ከታህሳስ 10/2014 ጀምሮ በከፈተው አዲስ ግንባር በተከታታይ እየተኮሰ ባለው ከባድ መሳሪያ ንፁሀን ዜጎችን መጨፍጨፍ መቀጠሉን መግለጫው ያትታል፡፡

በአፋር አካባቢ ጋሊኮማን ጨምሮ በአራት ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ወረዳዎች የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በድጋሚ በኪልበቲ ረሱ ዞን በአብአላና በመጋሌ በድጋሚ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ እያደረሰ እንደሚገኝም ተገልጿል።  አሸባሪው ህወሀት ካሁን በፊት በከፈታቸው ግንባሮች በምድር ድሮኖቹ ሽንፈት ገጥሞት ቢወጣም ቡድኑ በኪልበቲ ረሱ አብአላ እና መጋሌ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ድብደባ በንፁሃን ላይ በመፈፀም በርካቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገለዋል፣ ቆስለዋል፣ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በጥቃቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል ይላል መግለጫው።

  የትግራይን ህዝብ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር ለማናከስ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆነው በዚሁ አካባቢ የትግራይን ህዝብ ከጎረቤቱ ጋር በማናከስ፣ ጉርብትና እንዲሻክር እና ጎረቤቶችን በማጣላት የራሳቸውን እድሜ ለማራዘም አፋር እና ትግራይ ጎረቤት ህዝቦችን እያናከሰ እንደሚገኝም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

  ጎረቤታሞች በሰላም ውለው እንዳያድሩ እያደረገ ነው፤ የትግራይ ህዝብ ይሄንን የሽብር ቡድኑን እብደት ሊቃወም ይገባል ሲል የክልሉ መንግስት አሳስቧል፡፡

  ቡድኑ በንፁሀን የአፋር ህዝብ ላይ በተለይም በኪልበቲ ረሲ ዞን አብአላ እና መጋሌ በኩል የከፈተውን ጦርነት በጥብቅ ሊያወግዝ ይገባልም ይላል መግለጫው።

  ጁንታው ተደጋጋሚ የሆነ ሙከራ በኪልበቱ ረሱ በተለይም በአብአላና መጋሌ በኩል እያደረገ ሲሆን ያለ የሌለ ሀይሉን በመጠቀም ወደ ፊት ገፍቶ ለመሄድና የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስ ብሎም፣ በሌሎች ግንባሮች ያልተሳካለትን በዚህ ግንባር አጠናክሮ በመሄድ ዳግም ወረራ ለማካሄድ ትልቅ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

  በትናንትናው እና በዛሬው ዕለትም በተለየ መልኩ ተደራጅቶ በመምጣት ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ በርካታ ንፁሀን ላይ ጉዳት አድርሷል፣ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እና የግለሰብ የንግድ ተቋማት እና መኖሪያ ቤቶችን አውድሟልነው የተባለው፡፡

  አሸባሪው ህወሀት ካሁን በፊት ጦርነት በከፈተባቸው የአፋር አካባቢዎች በጣም በተደራጀ ሁኔታ ተደጋጋሚ እና ፋታ የማይሰጥ ጥቃት በመክፈት ወደ ፊት ገፍቶ ለመሄድ የሞት ሽረት ትግሉን እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

  የምድር ድሮኖቹ አሁንም ቢሆን ጁንታውን በሚገባው ቋንቋ እያናገሩት ሲሆን ያደረጋቸውን ተደጋጋሚ ሙከራዎች በማክሸፍ ቡድኑ ወደ አፋር ክልል ዘልቆ እንዳይገባ ብርቱ ተጋድሎ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

  ህወሓት በከባድ መሳሪያ ንፁሀንን የመግደልና የመጨፍጨፍ ተግባሩን አሁንም አላቆመም፣ ንፁሀን ፣ ሴት፣ ህፃናት እና አዛውንት አሁንም ሰለባ እየሆኑ ነው፤ የአለም ህብረተሰብ ጁንታው በድጋሚ በንፁሀን አፋሮች ላይ እያደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እና ሰላም ወዳዱ የአፋር ህዝብ በቤቱ በሰላም እንዳያድር እያደረገ ያለውንም የሽብር ተግባር ሊያወግዝ እና ቡድኑ እያደረገ ያለውን ዳግም ወረራ በአስቸኳይ ማቆም ይገባል መባሉን ከአፋር መገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ሲል ፋና መግለጫውን ጠቅሶ ዘግቧል።


  Leave a Reply