“ወይብላ ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ሚካኤል የሆነው ገለልተኛ እይታ ይፈለጋል”

  • timqet
በኮልፌ የቡራዩና አዲስ አበባ መዳረሻ እስከ ስጋ ሜዳ በወጉ ሊፈተሽ የሚገባው አካባቢ ነው። ነዋሪዎች እንደሚሉት እጅግ ሰላማዊ የነበረው በዓል እንዴት ሊበጠበጥ ቻለ? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው። ፖሊስ ጥይት ተኩሶ ጉዳት ማድረሱ ብቻ ሳይሆን ለምን ተኮሰ? ማን እንዲተኩስ አደረገው? የሚለው ጭምር በውል እዲጣራ በግል መረጃ መስጠትና ማን ጉዳዩን እንዳባባሰው መናገር የሚፈልጉ ስላሉ በግል መረጃ መሰብሰቢያ አግባብ እንዲዘረጋ ጠይቀዋል። ጉዳዩ እጅግ በመሆኑ መረጃዎችን ለመጻፍ ሰለሚያስቸግር ከህጋዊ አካላት ሪፖርቱን መጠባበቅ ግድ ነው። ሶስት ሰዎች በቀስቃሾች ሞተዋል።

በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና በቡራዩ አዋሳኝ ወይ ብላ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በተፈጠረው ችግር በዓሉ መስተጓጎሉና በሰዎች ላይም ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ችግር ፈጣሪዎቹ ለህግ ይቅረራባሉ ተባለ። ሁኔታውን የታዘበቡ በተጠቀሰው ቦታ ተደጋጋሚ ከባድ ወንጀልና ሀግወጥ ተግባራት መፈጸም የተለመደ በመሆኑ ይህን አጋጣሚ ተንተርሶ መንግስት ከባድ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የተፈጽመው አስነዋሪና በቅንጅት የተፈጸመ ውንብድና ከጀርባው ምን ዓላማ እንዳዘለ ግልጽ ባይሆንም ባለፈው ዓመት እንደሆነው ዓይነት መደገሙ ጉዳዩ ተቀጽላ ዓላማ እንዳለው አመላካች መሆኑ ተመልክቷል። ” … በድርጊቱ በቀጥታ የተሳተፉና ትዕዛዝ በመስጠት ያስፈጸሙ አካላትን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁና ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ እንዲያደርግ ” ሲል የሀገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በይፋ ጠይቋል። መንግስትም እገሌ ከገሌ ሳይባል ለግህ እንደሚያቀርብ ቃል ገብቶ ድርጊቱ ከተፈጸመበት ሰዓት ጀምሮ የህግ ማስከበር ስራውን መጀመሩን አመልክቷል። በቁጥጥር ስር የዋሉ አመራሮችና ጀሌዎቻቸው ይገኙበታል።

የአንድነት ማህበሩ እንዳለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን የጥምቀት በዓልና የቃና ዘገሊላ በዓልን በመላ ሃገሪቱ በሚባል ደረጃ በሠላም መከበሩን አመክቶ፣ ለዚህም ምስጋና አቅርቧል። አያይዞም “በየሺ ደበሌ አካባቢ በምትገኘው የወይብላ ማርያም ታቦትን አክብረው በሚመለሱ ካህናት ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አዛውንት ፣ ጎልማሳና ወጣት ምዕመናን ላይ ለጸጥታ ማስከበር ስራ በተሰማራ የጸጥታ አካል ኃይል የተሞላበት ጥቃት ምክንያት የደረሰው ችግር በተደጋጋሚ አንድ አካባቢ ሆን ተብሎ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የሚፈጽሙ ክርስቲያኖችን ከማወክ አልፎ ለሞት መዳረጉ በቤተክርስቲያናችን ላይ የሚድረስውን በደል የሚያሳይ ኢሰብአዊ እና ኢፍትሃዊ ድርጊት በመሆኑ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በጽኑ ይቃወማል።” ብሏል። ፍትህ እንዲበየንም ጠይቋል።

“ድርጊቱ ባለፈው ዓመትም የተከናወነ በመሆኑ ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ በመነሳት ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን እና የጸጥታ አካላት ጋር በዓሉ በሰላም ለማክበር ሰፊ ውይይት በማድረግ ሁሉም ድርሻውን ለመወጣት ኃላፊነት ተወስዶ በዚያ መልኩ ተግባራዊ ሆኗል” ያለው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት፣ ችግሩ በተመሳሳይ በቦታው ዘንድሮም በድጋሚ የተፈጠረ መሆኑ በአጋጣሚ የሆነ ክስተት አድርጎ መመልከት እንደማይቻል አስታውቋል።

ድርጊቱ የመንግሥትን ስልጣን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያጠቁ አካላት ተግባራቸውን ማሳያ በመሆኑ መንግሥት አስቸኳይ ማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም በድርጊቱ በቀጥታ የተሳተፉና ትዕዛዝ በመስጠት ያስፈጸሙ አካላትን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁና ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ እንዲያደርግ አሳስቧል።

ወይብላ ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ሚካኤል ታቦታት በክብራቸው ወደ መነራቸው ገቡ

የማኅደረ ስብሐት ወይብላ ቅድስት ማርያምና የቅዱስ ሚካኤል ታቦታት ትላንት ካደሩበት ቀራንዮ መድኅኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በብጹእ አቡነ መልከጼዴቅ ፣ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ፣በአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ በብዙ መቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ምእመናን ታጅቦ ወደ መንበረ ክብሩ ገብቷል።

በትላንትናው ዕለት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታትም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ መልአከ ህይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ክፍል ኃላፊ ፤ ከደብሩ ኃላፊ፣ ከወጣቶች ተወካዮች እንዲሁም ከምእመናን ተወካዮች ጋር ከምሽቱ 4:00 ሰዓት ጀምሮ 6 ሰዓታትን የፈጀ ውይይት በማድረግ በቀጣይ ቀናት አሉ የተባሉ ጥያቄዎችን በተመለከተ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር በኩል እንዲቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ከካህናት ፣ ከሰንበት ትምህርት ቤትና ከምዕመናን ተወካዮች ተውጣጥቶ ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር በጋራ ለመስራትና ጥያቄዎቹ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ተቋማዊ የሆነ አሰራርን ተከትሎ በቅድሚያ ለአ/አ ሀገረ ስብከት እንዲቀርብ ስምምነት ላይ መደረሱ መታወቁን የኢኦተቤ ህዝብ ግንኙነት ገልጿል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሰጥቷል። መንግስት ጉዳዩን በቀላሉ እንደማያይና አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አመልክቷል። ሙሉ መግለጫው ከታች ይነበባል።

❝የኢትዮጵያን ገጽታ ማበላሸት የፈለጉ አካላት የጥምቀትን በዓል በመረበሽ ተልዕኳቸውን ለማሳካት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካላቸውም

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ

ኢትዮጵያ በዓለም ደምቃ እንድትታይ ከሚያደርጓት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ አልፏል። በበዓለ ጥምቀቱ የታዩት ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ማኅበራዊ ዕሴቶች በዓሉ የኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቀ ውብ አብሮነትንም ለዓለም ያሳየ ሆኗል። በዓሉ በመላ ሀገሪቱ በሰላም እንዲከበር ኅብረተሰቡና የጸጥታ አካላት ላደረጉት አስተዋጽዖ መንግሥት ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል። በዓሉ የኢትዮጵያውያንን መፋቀር፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም በሚገልጽ መንገድ እንዳይከበር የተለያዩ አካላት የሸረቧቸውን ሴራዎች ሕዝቡና የጸጥታ አካላት ተናብበውና ተቀናጅተው አክሽፈውታል። ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ክንውኖች ከፊታችን አሉ።

እነዚህ ክንውኖች እንዳይሳኩ የኢትዮጵያን ገጽታ ማበላሸት የፈለጉ አካላት የጥምቀትን በዓል በመረበሽ ተልኳቸውን ለማሳካት ሞክረው ነበር። ነገር ግን አልተሳካላቸውም። የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው የመጡት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የማኅበራዊ መስተጋብሩ አካል በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ተገኝተው በዓሉን አድምቀዋል።

የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ባሻገር ለኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግንኙነት፣ ለቱሪዝም መስህብነትና ኢትዮጵያን ለዓለም በማሳየት ታላቅ ሚና አለው። በዚህም የተነሣ ከበዓሉ ቀደም ብሎ በተደረገ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት የሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው መሥተዳድር አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና ወጣቶች በጋራ በመሥራት በዓሉ በአብዛኛው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ተችሏል።

የጥምቀት በዓል በመላ ኢትዮጵያ በደመቀና በሰላማዊ መንገድ ቢከበርም በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና በቡራዩ አዋሳኝ ወይ ብላ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በተፈጠረው ችግር በዓሉ መስተጓጎሉና በሰዎች ላይም ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።በዓሉ በተገቢው መንገድ ባለመከበሩ፣ እንዲሁም በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልፃል። መንግሥት በስፍራው የተፈጠረውን ክስተት በማጣራት ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለሕግ እንደሚያቀርብ ያስታውቃል። ለዘመናት የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብራችን ማሳያ በሆኑ እንደ ጥምቀት በዓል ያሉ ሀብቶቻችንን ለማደብዘዝ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር ይከሽፋል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት


ይርዱ፣ የድርሻዎትን ያበርክቱ ከአንድ ብር ይጀምሩ – DONAT OUR ONLINE NEWSPAPER FROM 1 US$

Donate Button with Credit Cards

You may also like...

Leave a Reply