ከ46 ሀገራት የተውጣጡ 80 ታዋቂ የመረጃ አንጣሪ ተቋማት ለዩትዩብ ያስገቡት ደብዳቤ!

  • ዩትዩብ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ለሚያሰራጩ እንዲሁም ሴራ ለሚተነትኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ዋነኛ መናኸሪያ ሆኖ መቀጠሉ እንዳሳሰበው ያብራራል።

ከ46 ሀገራት የተውጣጡ 80 ታዋቂ የመረጃ አንጣሪ ተቋማት ዩትዩብ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭትን በመዋጋት ረገድ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ ለድርጅቱ ጻፉ።

ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች በማህበረሰብ ትስስር፣ በዴሞክራሲ ስርዐትና በህብረተሰብ ጤና ላይ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ሚና በመዘርዘር የሚጀምረው ደብዳቤ ዩትዩብ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ለሚያሰራጩ እንዲሁም ሴራ ለሚተነትኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ዋነኛ መናኸሪያ ሆኖ መቀጠሉ እንዳሳሰበው ያብራራል።

የደብዳቤው ጸሃፊዎች ዩትዩብ በፕላትፎርሙ የሚሰራጩ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በመከላከል ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ አለመሆኑን በመጥቀስ የወቀሱ ሲሆን ይህም “ሀላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በተጠቃሚዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያደርጉ እንዲሁም እንዲደራጁና ገንዘብ እንዲሰበስቡ ፈቅዷል’’ ብለዋል።

መረጃ አንጣሪ ተቋማቱ በጻፉት ደብዳቤ ባለፈው አንድ አመት በዩትዩብ የተሰራጩና ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ያሏቸውን ምሳሌዎች የዘረዘሩ ሲሆን ድርጅቱ ምንም አይነት የመከላከል እርምጃ አለመውሰዱን ጠቀሰዋል። በተለይም ችግሩ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ባልሆኑና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ጎላ ብሎ እንደሚታይ አንስተዋል።

ተቋማቱ ዩትዩብ በፕላትፎርሙ የሚሰራጩ ሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ለመከላከል እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት በተደጋጋሚ ያሳሰቡ ሲሆን መወሰድ አለባቸው ያሏቸውንም እርምጃዎች በዝርዝር አስቀምጠዋል።

ከተዘረዘሩት መካከል ድርጅቱ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ለመከላከል የሚጠቀምበትን አሰራር ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይም ግልጽነትን እንዲያሰፍን፣ ከህግ ጋር የተገናኙ ቪዲዮዎችን ከማስወገድ በተጨማሪ ሀሠተኛና የተዛባ ይዘት በሚታይባቸው ቪዲዮዎች ላይ አውድና ማብራሪያ እንዲጨምር፣ በተደጋጋሚ ሪፖርት የሚደረጉ ቻናሎች (በተለይም ገንዘብ የሚያስገኙትን) አለማስተዋወቅና ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ውጭ በሆኑ ይዘቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የሚሉ ይገኙበታል።

ተቋማቱ በጻፉት ደብዳቤ ዩትዩብ ከላይ የተጠቀሱትን እርምጃዎች እንደሚወስድ ተስፋ እንዳላቸው የገለጹ ሲሆን አብረው ለመስራትም ያላቸውን ዝግጁነት ጠቅሰዋል።

EthiopiaCheck Updates

See also  ትሕነግ ቡድን በአንዳንድ የአማራ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ የህዝቡን ሰላም እየነሳ እንደሆነ ተገለፀ

Leave a Reply