“በቀለ [ገርባ] በተለይ የጸሎታችን መሪ እርሱ ከሆነ ከእንባ ጋር ነው የሚጸልየው” አንዷለም አራጌ

በቀለ [ገርባ] በተለይ የጸሎታችን መሪ እርሱ ከሆነ ከእንባ ጋር ነው የሚጸልየው። ቀደም ብዬ እንደ ጠቀስሁት በሕዝብ ላይ እንዲሁም በእኛም ላይ ስለሚፈጸመው ግፍ በእንባ ይጸልያል። የበቀለ ጸሎት ይዘት የሰቆቃወ ኤርምያስን ይመስላል። በእውነት ለመናገር በበቀለ፣ በዶ/ር ፈንታሁን፣ በሀዋስና በኦልባና ምክንያት በጣም የተጠቀመ ሰው ካለ እኔ ነኝ። በሳምንት ሦስት ቀን የኅብረት ትምህርትና ጸሎት የምናደርግ ሲሆን፣ ሁላችንም በዙር የማስተማርና ጸሎትንም የመምራት ኀላፊነት ነበረብን።

ሁልጊዜም ማታ ማታ ወደ መኝታ ከመሄዳችን በፊት እንዲሁ ተራ ገብተን እንጸልያለን። የእኔ ትምህርት ግን እየረዘመባቸው ይማረሩ ነበር። በሕይወት ዘመኔ፣ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሁበት ጊዜ ካለ ከእነርሱ ጋር የነበርሁበት ጊዜ ነው። ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ያለፈ ታሪካችንን በጥሞና ለማየት የቻልንበት ጊዜም ነበር። ምንም እንኳን ሁሉም በኦሮምኛ ማስተማርም ሆነ መጸለይ የሚቀልላቸው ቢሆኑም፣ ለእኔ ሲሉ ትምህርቱንም ሆን ጸሎቱን በአማርኛ በማድረግ ከትምህርትና ከጸሎታቸው ብዙ እንድጠቀም አስችለውኛል። …

[…] ወደ ኦልባና እንመለስ። … በእስር ቤት ቆይታዬ የኦልባና ዐይነት መንፈሳዊ ሰው አላየሁም። በእስር ቤት ብቻ ሳይሆን፣ ከእስር ቤት ውጭም አልገጠመኝም። በቀኑ ውስጥ 90 በመቶ ኦልባናን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተጣብቆ ያገኙታል። ጸሎቱን ጨርሶ ወደ እርስዎ ክፍል ከመጣና እየጸለዩ ካገኘዎት ከእርስዎ ጋር ለመጸለይ ቅጽበት ብቻ ነው የሚያስፈልገው። ከአጠገብዎ ተንበርክኮ ያገኙታል። ጸልዮ አይጠግብም። ጊዜዎ የማይገደብ ከሆን ኦልባና ጸሎቱን ማቆም አይፈልግም። ሕይወቱ ጸሎቱ ነው።

ሁልጊዜም ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ ችግር ይፈጠራል። ከእንቅልፋችን የምንነቃው እርሱ ከፖሊሶች ጋር በሚፈጥረው አተካሮ ነው። ችግሩ እንደሌሎቻችን አይደለም። ይልቅስ አንድ ብቻ ሳይሆን አራት መጽሐፍ ቅዱሶችን ይዞ ለመውጣት ሲሞክር፣ “ይዘህ መውጣት አትችልም፤ አስቀምጠህ ለፍተሻ ቅረብ።” የሚል የፖሊሶች ትእዛዝ ስለሚኖር ሁልጊዜም በጠዋት ኦልባና ከፖሊሶች ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገባ ምን እንደሆን ይገባናል፤ እናም በተኛንበት እንስቃለን። ዓላማው ለዳኞቹ መጽሐፍ ቅዱስ ማደልና የሚሰሩትን ኢፍትሐዊ ተግባር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አያይዘው /አገናዝበው/ እንዲያዩት ለመርዳት ነበር። ዛሬ ቢከለከል በሌላ ቀጠሮም ውዝግቡ ይፈጠራል።

ከብዙ ሙከራ በኋላ አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱሶቹን ይዞ ለመውጣት የተሳካለት ይመስለኛል። ሆኖም ዳኞቹ ፈቃደኞች ሆነው ሊቀበሉት የቻሉ አይመስለኝም። ለማንኛውም ኦልባና ላይ 13 ዓመት ፈረዱበት።

ምስባከ ጳውሎስ ገጽ – አንዱዓለም አራጌ፤ 3000 ሌሊቶች፤ ገጽ 309፣ 312-3።

Leave a Reply