አየር ሃይል ዒላማውን እንዳይስት ሆኖ ታጥቋል

jeneral yelma merdasa

“የታጠቅነው መሳሪያ” አሉ ሌተናል ጄነራል ይልማ፣ ማን ምን እንደያዘ፣ የትና እምን ጋር እንዳለ ፊትለፊት እያየን ጥቃት እንድንሰነዝር የሚያስችለን በመሆኑ ዒላማችንን አንስትም። ጠላት መለዮ የሌለው በመሆኑ ሲመታ ሲቪል ሞተ እያለ ያታልላል” አክለውም ቀደም ሲል አገሪቱ አየር ሃይል አላት ማለት እንደማይቻል አመልክተው “ዛሬ አየር ሃይል ማንኛውንም አገር ላይ የሚቃጣ፣ ታላቅ አገርና ሕዝብን የሚወክል ቁመና ተላብሷል” ሲሉ ኢትዮጵያዊያን በተቋሙ ሊመኩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የትህነግ ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከርቀት ጽድት አድርጎ ማየት የሚችል ከፍተኛ ሪዞሉሽን ያላቸው ካሜራ የተገጠመላቸው ድሮኖችን እየገዛ መሆኑንን ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

“የታጠቅነው ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ ዒላማውን ለይቶ የሚመታ በመሆኑ ሠላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ አይሆኑም” በማለት ማብራሪያ የሰጡት ጀነራሉ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የታጠቀው መሳሪያና የሚጠቀምበት ቴክኖሎጂ ዒላማውን ለይቶ የሚመታና ያሰበውን ብቻ የማድረግ አቅም እንዳለው በስፋት አስረድተዋል።

በዚሁ መነሻ ትህነግ “የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው” ሲል የሚያቀርበውን ውንጀላና ክስ ከእውነት የራቀ መሆኑንን ጠቁመዋል። አየር ሃይሉ የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ አቤቱታው የሚቀርብላቸው እንደሚያውቁት ከዚህ ቀደም አንድ አብራሪ መናገራቸው አይዘነጋም። በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ ደማቅ መርሃ-ግብር በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ በመመከት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እውቅናና ሽልማት መበርከቱ ይታወሳል።

በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አቢይ አህመድ የላቀ አመራርነት ላስመዘገቡ የጦር መኮንኖች የ’አድዋ ጀግና ሜዳይ’ የሸለሙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አንዱ ናቸው፡፡

ሌተናል ጄኔራል ይልማ ከጦር መኮንንነት በተጨማሪ ምርጥ አብራሪ መሆናቸውም በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል። ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአየር ኃይሉን ዝግጁነትና ብቃት የሚያጎለብቱ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህም አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ በብቃት በመመከት ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲያበረክት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት፡፡ አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ከየትኛውም ወገን የሚቃጣን ጥቃት ለመመከትና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ኃይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየተደራጀ ነው ያሉት ዋና አዛዡ፤ ‘የታጠቅነው ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ የተሰጠውን ዒላማ በብቃት የሚመታ በመሆኑ በምንም መልኩ ሠላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይችሉም’ ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የአሸባሪው ህወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል “በትግራይ ክልል በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው” በሚል የሚያሰራጩት መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አየር ኃይሉ ሕዝባዊ መሰረት ያለውና በጠንካራ ስነ ምግባር የተገነባ በመሆኑ የትኛውም አይነት ኦፕሬሽኖች ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

የአየር ኃይሉ ዘመናዊ ትጥቆች ማንን እና ምን መምታት እንዳለብን በዓይናችን አይተን እንድንወስን የሚያደርጉ በመሆናቸው በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈጸም አይችልም ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት ህጻናትን የያዙ እናቶችን ጭምር አስገድዶ በጦር ካምፕ ውስጥ በማስገባትና የጥቃት ዒላማ እንደሆኑ አስመስሎ ፊልም በመቅረጽ እንደሚያሰራጭ ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎችም የራሳቸው የሆነ መለዮ የሌላቸው በመሆኑ የቡድኑ አመራሮች በጦርነቱ የሞቱባቸውን ታጣቂዎች አስከሬን በመሰብሰብ ሠላማዊ ዜጎች እንደተገደሉ አስመስለው ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር እየጣሩ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

የአየር ኃይሉ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያን በሚመጥንና ኢትዮጵያዊያንን በሚመስል መልኩ የተገነባ እንዳልነበረ፤ በአንድ አካባቢ ሰዎች ታጥሮ ለአንድ ፓርቲ ህልውና ሲሰራ እንደቆየም አንስተዋል።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በአጭር ጊዜ ለታላቅ አገር የሚመጥንና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሆነ ተቋም መገንባት መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ይህን ተከትሎ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ወጣቶች ተቋሙን በመቀላቀል ስልጠና እየወሰዱ መሆኑንም ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተናግረዋል፡፡

የአየር ኃይሉ የኢትዮጵያ የአየር ክልል ከደህንነት ስጋት ነጻ እንዲሆን በመጠበቅ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያለምንም ችግር የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply