በጥምቀት በዓል ጥፋተኛ በተባሉት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ተገለጸ

ከጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተፈጠተሩ ጠብ አጫሪ ደረጊቶችና ጥፋቶች ጋር በተያያዘ የእርምት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ዝርዝሩን ሳያካትት በቁጥትር ስር የዋሉ መኖራቸውን ይፋ ያደረገው መግለጫው መንግስት አጥፊ ሆነው በተገኙት ላይ ሁሉ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አመልክቷል።

ከከተማ አስተዳደሩ የከንቲብ ፅ/ቤት ያሰራቸው መግለጫ ሙሉ ቃል ከታች ታትሟል።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

የመንግስት አካላት ጥፋት የሆነውን ለይተን እርምጃ መውሰድ የጀመርን ሲሆን በቀረውም አጥፊዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ሃላፊነታችንን የምንወጣ መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን፡፡

የተከበራችሁ ውድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ፤ የጥምቀት በዓል በሀገራችን ብሎም በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ከሚክበሩ በዓላት መካከል በናፍቆት የሚጠበቅ ነው:: በዓሉ በሀገራችን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ለዓለም ያበረከተችው ድንቅ ቅርስ ሲሆን ለእኛ ለኢትዮጵያዋን ደግሞ የኩራታችን ምንጭ ጭምር ነው::

በዘንድሮ የከተራ ፣ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በአላት ላይ የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውን ፣ ዳያስፖራዎች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያለው የእምነቱ ተከታዮች ታድመውበታል፡፡

የጥምቀት በዓል የበዓሉን ትውፊታዊ ገፅታውን ጠብቆ በሰላምና በፍቅር: በድምቀትና በአብሮነት መንፈስ በማክበር በአዲስ አበባ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች 266 ታቦታት ከመንበራቸው በመዉጣት በ72 ልዩ ልዩ የጥምቀተ ባህር ስፍራዎች አድረው በሰላም ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

በዓላት በመጡ ቁጥር ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ሃይሎች በኢትዮጵያ ሰላም የለም ለማስባልና የአሸባሪውን ቡድን ተቀጥላ ፍላጎቶች ለማስፈፀም፤ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በአመፅና ግርግር ለማውረድ ፤ በህዝቦች መሃከል ጥርጣሬና ግጭት ለመፍጠር፤ ብሎም ህዝባዊ በአሉን ወደለየለት ትርምስ ለመክተት፤ ህዝብን የሚሸብሩ ድርጊቶችን ለመፈፀም አቅደው ቢንቀሳቀሱም ሀገሩን እምነቱንና ባህሉን አክባሪ የሆነው ህዝባችን ባደረገው ርብርብ በዓሉ ጠላት በተመኘው ልክ ሳይሆን በሰላም ተጀምሮ በሰላም ተጠናቋል::

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአራዳ ክ/ከተማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ፀብ አጫሪና አሳፋሪ ድርጊት እንዲሁም ከባህረ ጥምቀቱ ወደ ደብሯ በመመለስ ላይ በነበረችው በወይ ብላ ማርያም ታቦት በቡራዩ ከተማ አዋሳኝ አካባቢ የገጠማት መስተጓጎል እና ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው አለመግባባት ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን የከተማ አስተዳደሩ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል፡፡

በዚህ ረገድ እንደ መንግስት የመንግስት አካላት ጥፋት የሆነውን ለይተን እርምጃ መውሰድ የጀመርን ሲሆን በቀረውም አጥፊዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ሃላፊነታችንን የምንወጣ መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን፡፡

ከተማችን እንደወትሮዋ ሁሉ በከተማዋ ውስጥ የሚካሄዱ ሃይማኖታዊ ባህላዊ የተለያዩ ክብረ በዓላትና ኩነቶች በድምቀት በሰላም በአብሮነት መንፈስ እንዲካሄዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራቱን ይቀጥላል:;

በከተማችን የጥምቀት በዓል በድምቀትና በሰላም እንዲከበር ምዕመኑ መላው የከተማችን ነዋሪዎችና የጸጥታ ሃይሎች ላደረጋችሁት ጥረት ለከፈላችሁት ዋጋና ላስያችሁት ጨዋነት የከተማ አስተዳደሩ የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል:: ይህንኑ በቅርቡ በሚጠበቀው በአፍሪካ መሪወች ጉባኤ በሰላም ውብና ጽዱ በሆነ አካባቢ እና በማራኪ አቀባበልና አገልግሎት የበለጠ እንድትዘጋጁ አደራ እንላለን::

በመጨረሻም ህዝብ እያደረገ ላለው ጠንካራ ድጋፍ እና በአላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ኃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ ሁሉ የላቀ ምስጋናችንን እናቀርባለን!!
የከተማችንን ሰላም በማረጋገጥ የጀመርነውን የኢትዮጵያን ትንሳኤ የማረጋገጥ ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን!!
ጥር 14/2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Leave a Reply