ዳያስፖራው ያሰባሰበውን ገንዘብ በማጭበርበር ወደ ሌላ አካውንት ያዘዋወሩ የንግድ ባንክ ሰራተኞች ተያዙ

ለተፈናቀሉ ወገኖች የተሰበሰበን ገንዘብ በማጭበርበር የተጠረጠሩ የንግድ ባንክ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አሰታወቀ

ዳያስፖራው ሀገራዊ ጥሪውን መሰረት በማድረግ በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ያሰባሰቡትን ገንዘብ በማጭበርበር ወደ ሌላ የግለሰብ አካውንት እንዲገባ ያደረጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ። በተመሳሳይ እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎችን እያጣራ እንደሚገኝም አስታውቋል።

በአሜሪካና በጀርመን ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ጥሪውን መሰረት በማድረግ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ይዉል ዘንድ ከራሳቸው፤ ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ያሰባሰቡትን የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶችን በማጭበርበር በግለሰብ አካውንት ውስጥ በማስገባት የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የዲያስፖራ አባላቱ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ለገሀር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲያስፖራ ቅርንጫፍ ያሰባሰቡትን ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ሲሞክሩ የባንኩ ሰራተኞች በተባለው አካውንት ያስገቡ በማስመሰል ወደ ሌላ ግለሰብ አካውንት ገቢ በማድረግ ደረሰኙን ለዲያስፖራ አባላቱ ሰጥተዋል።

በዚህ መሰረት የዲያስፖራ አባላቱ ገንዘቡ ገቢ የተደረገው ወደ ግለሰብ አካውንት መሆኑን በማረጋገጣቸው ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጋቸውንና ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የወንጀል ምርመራ ቢሮው ገልጿል፡፡ በተያያዘም በሌሎች ባንኮች በተመሳሳይ እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎችን እያጣራ እንደሚገኝም ፖሊስ አስታውቋል።

የተሰበሰበውን ገንዘብ በማጭበርበር ለራሳቸው ጥቅም ሊያውሉ ሲሞክሩ የተደረሰባቸውን ተጠርጣሪዎች መያዝ የተቻለው የዲያስፖራ አባላቱ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ በመሆኑ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል። ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት የተለመደውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን ማስተላለፉን ኢፕ ድ አመልክቷል።

Leave a Reply