ጣናን ከእምቦጭ ለመታደግ ከ120 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚሳትፉበት ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

የጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ ከ120 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚሳትፍበት ንቅናቄ በሚቀጥለው ሳምንት በማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንደሚጀመር የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻ የ2013 ዓ.ም አፈፃጸምና የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ትግበራ ዙሪያ በጎንደር ከተማ ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ በመድረኩ እንደገለጹት፥ በጣና ሐይቅና ዙሪያው የተከሰተው የእምቦጭ አረም አሁንም በስጋትነቱ እንደቀጠለ ነው።

አረሙን ለማስወገድ ባለፉት ዓመታት በሕዝብ ተሳትፎ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም ከአረሙ የመባዛት ባህሪ ጋር ተያይዞ አሁንም ሐይቁን እንደወረረ መሆኑን ነው አቶ አያሌው ያስረዱት።

አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በከፈተው ጦርነት ሳቢያ አረሙን የማስወገድ ሥራው ተስተጓጉሎ እንደነበር አውስተው፣ በሕልውና ዘመቻው የተገኘው ድል ንቅናቄውን ለማስጀመር እንደረዳም ገልጸዋል።

በዚህም ሐይቁን በሚያዋስኑት በማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ 30 ቀበሌዎች የሕዝብ ተሳትፎ ንቅናቄ በመጪው ሳምንት በይፋ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግሥት በመደበው 20 ሚሊዮን ብር ወጪ በሚካሄደው ይህ ዘመቻ ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ የሸፈነ የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ታቅዷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

See also  የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ዓላማ ለዜጎች የምትመች ሰላማዊት ኢትዮጵያን ማየት

Leave a Reply