ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተነፈሱትን እየበጣጠሱ በየቀኑና ሰዓቱ የአገሪቱን ፖለቲካ ማጦዝ ስራ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ጭልጥ ባለ የተገዢነት መንፈስ አይኑን በጨው አጥቦ የሃሰት ዘገባ ሲዘግብ የኖረው ኤፒ አድበስብሶ የዘገበው ዘገባ ዛሬ አየር ምድሩን አጡዞት ውሏል። ዜናውን ሰጡ የተባሉት ሰው ” ሃሳቤ ተንጋዶ፣ ጋዜተኛዋ ለምትፈልገው ጉዳይ እንዲሆን ሆኖ ቀርቧል። ማስተባበያ እንዲደረግ” ብለዋል። ለነገሩ ዕርቅ ቢደረግና ሰላም የናፈቀው ምስኪን ሕዝብ “እፎይ” ቢል ጥሩ ነበር ግን ኤፒ ራሱ እንዳለው “ዕርቅ በአንድ ወገን ፍላጎት አይሆንም”።

በኤፒ ድንግዝግዝ በቀጥታና እየተጠቀሱና ሳይጠቀሱ እንደማጣፈጫ ሆነው የቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለአምስት ሰዓታት እንዳነጋገሯቸው ገለጹ የተባሉት አቶ መስፍን ተገኑ በአሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቲ ሊቀመንበር /chairman of the American Ethiopian Public Affairs Committee ናቸው።

ዘግይትው በቲውተር ገጻቸው ” የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ስለ ኢትዮጵያ ያለውን አመለካከት ለመቀየር የምናደርገውን ጥረት ለማስቀጠል እንደ ኤፒ ካሉ ተቃዋሚ ሚዲያዎች ጋር መገናኘቱ ወሳኝ ነው። ትግሉን ወደ እነርሱ መውሰድ አለብን። ከሚዲያ መራቅ የለብንም. በሚል እሳቤ የሰጡት ቃል መበረዙንና ጋዜጠኛዋ ስለ ጦርነቱ ባላት አቋም ሳቢያ አንሻፋ አቅርበዋለች” ሲሉ አቶ መስፍን ተናግረዋል።

አቶ መስፍን ምንም እንኳን ከኤፒ ጋር ላደረጉት ውይይት የሰጡት ምክንያት ባያሳምንም ሃሳባቸው ተዛብቶ መቅረቡን አመልክተዋል። ዜናውና እሳቸው ያሉት አንድ አይደለም። ድርጅታቸው መግለጫ እንደሚያወጣ አመላክተዋል።

በስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በቃል በትምህረት ጥቅስ ተጠቅሰው ተናገሩ የተባለው አንዱ  “a very earnest desire to stop this thing. … Of course, the other side must be willing.” “ይህን ጦርነቱን ለማቆም በጽኑ ፍላጎት አለ፤ ይህ የሚሆነው (እውን እንዲሆን) ሌላኛው ወገንም ፍቃደኛ መሆን አለበት” የሚለው ሃረግ ነው።

ሌላው የተጠቀሰው የዜናው ማጋጋያ ” The prime minister “said that there will be negotiations, reasonable negotiations, that will keep the interest of the integrity of the nation first,” የሚለው ነው። “ድርድር ይኖራል። ድርድሩም የአገሪቱን ጥቅም የሚያስቀድ ምክንያታዊ ድርድ ይኖራል” ተብሎ ተተርጉሟል። ይህን እንግዲህ ሕዝብ ፊት ” እመኑን የአገር ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም። እዚህ መናገር አልችልም። ግን መልካም ነገር አለ” ብለው በይፋ ነግረውናል። ምንም አዲስ ነገር የለም።

እዚህ ላይ በተለይ ተጠቅሶ ስለትህነግ የተባለ ነገር የለም። ቢኖርም ከየትኛው ትህነግ ጋር? ታስሮ ከተፈታው? በውጭ አገር ካለው? መቀለ ሆኖ በሁለት ሃሳብ እንዳለ ከሚገለጽለት አንዱ ወገን? ወይስ “እኛ የሌለንበት ንግግር አይሆንምና ድርድር ካለ እኛም አለንበት ካሉት ፓርቲዎች፣ ከባይቶና፣ ንጻነት፣ አረና ፣ ሳልሳይ ወያኔና፣ የራዕይ ፓርቲ ከየትኞቹ ሃይሎች? ዜናው ከአናቱ “አብይ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ድርድር እንደሚኖር ተናገሩ” ከሚለው የወሬው ዕርቃነ አጥንት ውጭ ማስረገጫ ጭብጡ የጸዳ እንዳልሆነ ዜናውን የመረመሩ፣ ኤፒ በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምደውን አቋም የሚረዱ እየገለጹ ነው።

አቶ መስፍን ከሰሩት ስህተት ባያድናቸውም ባሰራጩት ጽሁፍ ” ማንኛውም ድርድር ከህወሀት እጅ መስጠት ጋር በተገናኘ ብቻ መሆን አለበት ፣ መንግስት በሰላሙ ላይ ትልቅ እመርታ አድርጓል፣ አሁን ጉዳዩ ያለው ህወሃት እጅ እንደሆነ ይህም ወረራውን ማቆም እንደሆነ፣  ህወሀት ጥሪውን እምቢ እምቢ ብሎ አዲስ ጥቃት ሲጀምር ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ፈጽሞ ማድረስ እንደማይቻል ፣ በተባበረች ኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ ወደፊት ተስፋ እንደሌለው” የሚሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች ማንሳታቸውን ያትታሉ።

ዘግይተውም ቢሆን ማስተባበያ የጠየቁበትን አሳባቸውን “እባካችሁ አራቡልኝ” ብለው ቢበትኑም፣ በአገር ጉዳይ ተከብረው ለውይይት የተጋበዙት አቶ መስፍን ተገኑ “ምን ኤፒ ሰፈር ወሰዳቸው? ትርፋቸውስ ምንድን ነው? ማናገር ከፈለጉስ ለአገር ውስጥ መገናናዎች ለምን አይናገሩም? ይህን በማለት ማስደሰት የፈለጉት ማንን ነው? ዓላማቸው ሲጨመቅ ምንድን ነው?…” ወዘተ የተሰኙ ጥያቄዎች እንዲሰነዘርባቸው አድርጓል። አቶ መስፍን በምን ስሜትና በተለየ ኤፒን መርጠው የተድበሰበሰ መረጃ ለመንሾካሾክ ሲወስኑ፣ ዜናውን የጉዳይ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማድረስ ከፈለጉ ለምን በገሃድ ወጥተው በአማርኛ አልተናገሩም ሲሉ የሚያሳንሷቸውም አሉ። ዜናው እሳቸው ካሉበት፣ ወይም ተቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቡበት አውድ ስቶ ከሆነም ወጥቶ ማስተካከል ሲገባቸው ዝም ማለታቸው፣ ወይም ” ተድበስብሷል ላብራራ” ብለው አለመቀረባቸው “ዳተኛ” ብቻ ሳይሆን ” አውቆ የተኛን” እንዲሉ እንዳደረጋቸውም ተተቁሟል። ድርጅታቸው ከዚህ አይነት የሹክሹክታ ዜና ምን እንደሚያተርፍ አባላቱ ከገባቸው በፊናቸው የሚሉትን ሊሉም የገባል።

አቶ ኤሊያስ አያልነህ የተባሉ ” ድርጅታቸውንና እሳቸውን ብቻ ሳይሆን መንግስት ካለበት አጣብቂኝ አንጻር ሳይመርጥ ማግበስበሱ ጎድቶታ” ሲሉ በሆነው ማዘናቸውን፣ እንደ አንድ ኤትዮጵያዊ ለኤፒ እንዲህ ያለ የግል ንግግርን ( ትክክል ከሆነ) አሳልፎ መስጠት ከሰነፎች ልብ የሚወጣ፣ ከተሰበረ ሚዛን የሚሰፈር ማንነት ውጤት እንደሆነም አምለክተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን እንደሰማ በአንድና ሁለት ሃረግ አስታውቆ በአቶ መስፍን እየተሟሟቀ ” በመርዝ የተለውሰ” ዘገባ የረጨው ኤፒን ተከትሎ ቢቢሲ በሩጫ ተርጉሞ ካቀረበው በሁዋላ ” ዕርቅ የሚደረግ ከሆነ ሞት ለምን አስፈለገ” የሚል አስተያየት ተሰምቷል። እንዲህ ያሉት ክፍሎች ሞት ሳይኖር ግን የትህነግ ወራሪ እንዴትና በምን ዓይነት አስማት ከደብረሲና ተገፍትሮ ሊወጣ ይችል እንደነበር አላመላከቱም።

ዛሬ “የድርድር ያለህ” ሲሉ የሚወተውተው ትህነግ በወቅቱ በመሪዎቹ አማካይነት ስለ ድርድር ሲጠየቅ “ከማን ጋር? ጦርነቱ አልቋል። ባለቀ ነገር ድርድር የለም። ሰብስበን እናስገባቸዋለን” በሚል ዕብለት እንዳልተናገሩ፣ ዛሬ ወደ ደብዳቤና የድረ ገጽ ለቅሶ የተቀየሩት በመስዋዕት ስለመሆኑ መዘንጋት አግባብ እንዳልሆነ በቅሬታ የሚገልጹ አሉ።

“አንድ አጀንዳ በተለኮሰ ቁጥር እሱ ላይ እየተንተለጥሉ ትላንትን መዘንጋት አንዳንዴም እንደሚያሳፍር ሊታወቅ ይገባል” የሚሉ ተወደደም ተጠላም የኢትዮጵያ ችግር በሰላማዊ ድርድር እንጂ በጠብመንጃ ሊሳካ እንደማይችል ይናገራሉ። ጥያቄው መሆን ያለበት ድርድሩ እንዴት ፍትሃዊ ይሁን? ታማኝ ይሁን? ሕዝብን ይጥቀም? ዘላቂ ሰላም ያምጣ? የሚሉትና ከምንም በላይ አገሪቱን ባለችበት ሳትበተን ያስቀጥል የሚሉት መሰረታዊ አሳቦች ሊሆኑ ይገባል።

አቶ መስፍንም መነሻሸውና መድረሻቸው “ድርድር ሊደረግ እንደሆነ ሰማሁ” ከሚለው የማሳበቅ ዓይነት ዜና ይልቅ፣ ሰላም የተማው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ሰላሙን ሊያገኝ ይችላል? በሚለው መመርመሪያ ሚዛን መሆን ነበረበት። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሸፍጥ፣ ሴራ፣ ክህደትና ሕዝብን የሚያዋርድ ተግባር እንዳይፈጸም አስቀድሞ መከላከል የሁሉም ዜጋ ሊተጋ ይገባል። መንግስትም ይህንኑ ለዲያስፖራና ለሕዝብ በተለያዩ አውዶች አመልክቷል።

እስረኞችን ሲፈታ የርቅ ስራ ስለመጀመሩና ሚስጢሩ በተወሰነ ደረጃ መገፈፉ እየታወቀ፣ ከተቻለና አቅም ካለ የድርድሩን ይዘትና መዳረሻ ለማሳመር ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት አለያም ሰላም ለናፈቀው ምስኪን ህዝብ ሲባል ቢያንስ ከመንሾካሾክ መቆጠብ የዜጎች ሁሉ ድርሻ ሊሆን እነደሚገባ በርካቶች ይስማማሉ። በተለይ በተለይ እንደ ኤፒ አይነት በኢትዮጵያ ጉዳይ ሚዛኑ ከወላለቀ መገናኛ ደጅ ወሬ ይዞ መሄድ በየትናውም መስፈርት ክብርን አያስገኝም። የከፍታ ስነልቦና ባለቤትም አያሰኝም። መናገር ካስፈለገ ለኢትዮጵያዊያና በሚገባቸው ቋንቋ በአገራቸው ሚዲያ መናገር ይቻላል። ሚስጢር ለነጭ አሳብቆ፣ በአስተርጓሚ መስማት ዛሬን አይመጥንም። ሰላም በማጣታችን ኢኮኖሚያችን ተናግቷል። ረሃብ እያረገፈን ነው። ከብቶች እያለቁ ነው። በሺህ ሞተዋል። ንብረት ወድሟል። ህጻናት ትምህርት አልባ ሆነዋል። ህክምና እየለም። በጅምላ የሞቱትን፣ የተሰውትን ወላድና ቤቱ ይቁጠራቸው። ይህ እንዳይቀጥል የሚወሰደው ሁሉ ሪስክ መወሰድ አለበት። ዳሩ ምን ያደርጋል ትህነግ ሰላም አይፍልግም። ዜናው መሆን የነበረበት እንደዚህ ነበር።

Leave a Reply