ትህነግ አፋር ጋሊኮማ የፈጸመው ጭፍጨፋ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ይፋ ሊሆን ነው

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋር ክልል ጋሊኮማ መጠለያ ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ የፈፀመውን ጭፍጨፋ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ እየሰራ መሆኑን የሰመራ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በጋሊኮማ ጭፍጨፋ ዙሪያ ባካሄደው ጥናት ላይ ትናንት ውይይት አካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡመር ሁሴን በውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ምክንያት በአርብቶ አደሩ ላይ የተፈጸሙ አስከፊ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶችና ውድመቶች ላይ መፍትሄ ሊያመነጭ የሚችል ጥናት እያካሄደ ይገኛል።

አሸባሪው ህወሃት በክልሉ ወረራ በፈጸመበት ወቅት በጋሊኮማ ከ240 በላይ እናቶችና ህጻናትን ጨምሮ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ዜጎች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ታሪክ እንደማይረሳው ገልጸዋል።

ከዚህ የጥፋት ድርጊት ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ በአግባቡ ተሰንዶ መቀመጥ እንደሚገባው ገልጸው፤ ከጥቅምት 2014 ዓ.ም ጀምሮ የምሁራን ምሁራን ቡድን ተዋቅሮ ወንጀሉን በተጨባጭ ማስረጃዎች ማረጋገጥ የሚያስችል ጥናት መካሄዱን አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ጥናቱን በማጠናከርና በመሰነድ አሸባሪው ህወሃት ያደረሰውን ጭፍጨፋ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያሳውቅ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

የጥናት ቡድኑ መሪ አቶ ሃቢብ መሀመድ በበኩላቸው ጥናቱ በዋናነት ከጉሊና፣ ያሎና ቴሩ ወረዳዎች በተውጣጡ የጉዳቱ ሰለባና የአይን እማኞች የሆኑ 42 ሰዎችን ያካተተ የቃለመጠይቅና የቡድን ውይይት መነሻ በማድረግ የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመና የወንጀሉን ደረጃ ከተቀመጡ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች አንጻር መለየት የጥናቱ አላማ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዚሁ መሰረት በአሸባሪው ህወሃት ጥቃቱ የተፈጸመና የወንጀል ደረጃውም የዘር ማጥፋት መሆኑ መረጋገጡን አስታውቀዋል። የጥናት ሰነዱ ወደ ህብረተሰቡና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።

ጥናቱ በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቀት ያለው ምርምርና ጥናት ለማድረግ ፍላጎት ላላቸው አካላት በመነሻነት እንደሚያገለግል ቡድን መሪው አስታውቀዋል። በአፋር ክልል ከያሎ እና ጎሊና ወረዳዎች ተፈናቅለው “ጋሊኮማ ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት” ተጠልለው በነበሩ ዜጎች ላይ አሸባሪው ህወሓት ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል። ዘገባው የኢዜአ ነው

Leave a Reply