ከፍተኛ ደረጃ ድርቅና ሰው ሰራሽ ቀውስ የሚያምሳት ኢትዮጵያ የዘንድሮው የእንቁላል ቀን እንቁላልን በመመገብ የተሻለ እንኑር /Eat more egg live better/ በሚል መሪቃል ማክበሯን የግብርና ሚኒስቴር በፌስ ቡክ ገጹ አመልክቷል። የግብርና አመራሮች፣ በዘርፉ የሚመለከታቸው ተቋማት እንዲሁም በዶሮ ሀብት ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዓሉን “በድምቀት አከበርኩ” ያለው።

የበዓሉ መከበር ዋና አላማ እንቁላልን ማምረትና መመገብ ያለውን ጠቀሜታ ለህብረተሰቡም ሆነ ለሀገሪቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ግንዛቤን ለማስፋፋትና በዚህም ረገድ የዶሮ አርቢዎችን ለማበረታታት እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን በመወያየት የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ እንደሆነ በግብርና ሚኒስቴር የዶሮ ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ጽጌረዳ ፍቃዱ የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የዶሮ ሀብት ልማት ነባራዊ ሁኔታ እና የምግብና የተመጣጠነ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የዶሮ ምርቶች ያላቸዉ አስተዋጽኦ በሚል ርእስ የመወያያ ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡ እንቁላል ከፍተኛ ፕሮቲን ካላቸው ምግቦች አንዱ እንደመሆኑ መጠን በሀገራችን ያለዉን የህፃናት መቀንቸርና መቀጨጭ ችግርን ለመቅረፍ እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ የተስተካከለ የምግብ ስርዓት እንዲኖር እንቁላልን መመገብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለዉ አቶ ቴዎድሮስ ግርማ በግብርና ሚኒስቴር የምግብና ስርአተምግብ አማካሪ ባቀረቡት ፅሁፍ ገልጸዋል፡፡

በዉይይቱ ላይ በፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለዉን ልዩነት ለማስተካከል የመኖ አቅርቦት፣ የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ማቅረብ እና በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ወጣቶች በስራ ዉስጥ በስፋት እንዲሳተፉ ነባር እንዲሁም የዶሮ እርባታ ተቋማትን አቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የዶሮ ስጋና እንቁላል አቅርቦት እና ፍላጎት መካከል ከፍተኛ ክፍተት ስላለና አጠቃቀማችን እያደገ ካለዉ የህዝብ ቁጥር ጋር የማይጣጣም ስለሆነ ያሉትን ክፍተቶች እንደ እድል በመጠቀም የዘርፉን ምርታማነትና አጠቃቀም ለማሻሻል ግብርና ሚኒስቴር በትኩረት እየሰራ መሆኑን እና የዘርፉ ተዋናዮች የድርሻቸዉን መወጣት እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ ጽጌረዳ ፍቃዱ ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply