የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋር ህዝብ ጉዳይ በ”ግፋ በለው” አይቋጭም!እናቶች ልጆቻቸውን…

” የትግራይ ሕዝብ፣ የትግራይ ሕጻናት፣ የትግራይ ምስኪን አዛውንቶች፣ በጥላቻ እየተኮተኮተ ያደገው የትግራይ ታዳጊና የትህነግ አመራሮች አንድ አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም። እናም እይታን በማስተካከል ለጦርነት ከሚከፈለው ዋጋ በላይ ይህን የተዛባ አካሄድ ለማረቅ መስራቱ ያዋጣል። የትግራይ ልሂቃንም ሆኑ ፖለቲከኞች ለህዝባችሁ ስትሉ ከግትርነትና ከማይሆነው የወጣችሁበት የጥጋብ መሰላል በመውረድ ለሰላም መፍትሄ ሃሳብ አቅርቡ። ከወንድሞቻችሁ ጋር በውጭም በአገር ቤትም አንድ ላይ ምከሩ። የመሬትና የርስት ጉዳይ ከቀናነትና ከልብ ከመነጨ ዕርቅ በሚቀዳ ተስፋ የጋራ መተቀሚያ እንጂ መዋጊያ እንዳይሆኑ ማድረግ ያቻላል”

( በሞገስ አያሌው ቢራራ)

በየአቅጣጫው የሚወጡ ሪፖርቶች አስደንጋጭ ናቸው። ኮቪድ፣ የኑሮ ውድነት፣ ረሃብ፣ ድርቅ፣ የመድሃኒት እጥረት፣ መፈናቀል፣ የንጹሃን ስቃይ ወዘተ ልክ አጥቷል። መቆሚያው የት እና እንዴት እንደሆነ መገመትም፣ ማለምም የማይቻልበት ደረጃ ደርሷል። የዚህ ሁሉ ክምር ችግር ዋና መነሻ ደግሞ ሕዝብ “እምቢ” ብሎ ያመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሴራና የገሃድ ጦርነት፣ እንዲሁም ለሶስት አስርት ዓመታት የተዘራው ጥላቻና የታፈነው የህዝብ ጥያቄዎች ናቸው።

ከለውጡ ቀደም ሲል ጀምሮ የነበረው አለመረጋጋት አስከትሎት ከነበረው ጣጣ ጋር አንድ ላይ አገሪቱን መምራት የጀመረው የለውጡ መንግስት በጅምላ ወደ አገር ቤት የጋበዛቸው፣ በአገር ቤት ያሉ፣ የተፈጠረውን ዕድል ተጠቅመው አዲስ የተደራጁ፣ ቀደም ሲል “ጥያቄያችን ታፍኖ ኖራል” ያሉ ሁሉም “ዛሬውኑ” ስልጣን ሲሉ መንግስትን ወጠሩ። አኩሩፎ መቀለ የገባው ትህነግም ሃብቱንና የቀድሞ ሰንሰለቱን፣ እንዲሁም በስፋት የፈለፈላቸውን ሚዲያዎች ተጠቅሞ መንግስትን ማዛል ከጀመሩት ጋር አበረ። የአንዳንዶቹም ፈጣሪያቸው ነበርና ይመራቸው ጀመር። የራሳቸውን ሚዲያ ያደራጁ የዘር ፖለቲካ በቅጽበት ክንዳቸውንና ኪሳቸውን አደልቦት ” ሁለት መንግስት አለ … አንተ አምጽ እኛ እናወራርዳለን” የሚል የጥጋብ ፖለቲካ ውስጥ ተዘፈቁ።

በዚህ የተጀመረው “ዛሬውን” የሚል ጥያቄ በየአቅጣጫው የግጭት ቀተናዎችን ፈለፍለ። ጀነራል አበባው እንዳሉት አንድ መቶ አስራ ሶስት የብጥብጥ ጣቢያዎች ተመረቱ። ሕዝብ ተፈናቀለ፣ ንጹሃን ታረዱ፣ ተገደሉ የተሰቀሉ አሉ። ሆድ ተሰነተቀ። የመኖሪያ ጎጆ ነደደ። ይህን ሁሉ የሚፈጽሙት ድርጊታቸውን በቪዲዮ እየቀረጹ በኩራት ለሚለጥፉላቸው አለቆቻቸው በመላክ ድርጊቱ ተመልሶ መንግስትን መውቀሻና ማጥላያ ይሆን ጀመር። የጥፋት ሩጫው እየተባባሰ ከተማ፣ ኢንቨስትመንት፣ መሰረተ ልማት አወደመ። ሰዎች በዘራቸው እየተለዩ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ ሆነ። የተረፉም ንብረታቸው ተዘረፈ። ወደመ። ይህንን ሁሉ መከራ አዛኝ መስለው አቀጣጣይ ነዳጅ የሚረጩት “ዛሬውኑ ስልጣን” የሚሉት ክፍሎች ነገዱበት። አተረፉበት። መንግስት “ሃይ” እንዳይል የትሰበረ ፖሊስ፣ ደህነት፣ በየአቅጣጫው የተበተነ መከላከያ ይዞ በጥቅሉ”ባዶ ቤት” ነበርና አልቻለም። ይህን የተረዱት ዋና ቀውስ ተማቂዎችና እድሉን ተጠቅመው የመንግስት መዋቅር ውስጥ የፈነጩ ችግሩን ከቤተ መንግስት ውጪ ያሉ መንግስታት ሆኑ። ህዝብ ግራ ተጋባ። ማንባት ጀመረ። በየዕለቱ አሳዛኝ ዜናዎች መስማት ተለመደ። የጎበዝ አለቃዎች ግን የሆኑት ኩራት ነፋቸው።

See also  ከባድ ውንብድና የፈጸሙ የፖሊስ አባላት ተፈረደባቸው

የአዞ ቆዳ የለበስችው ኢትዮጵያና በዚሁ ቆዳዋ የተከፈነው ሕዝብ በዚህ ሂደት እየነፈረ ከርሞ ከሰሜን፣ የሰሜን ዕዝ መወጋት ተሰማ። መከላከያ ላይ የተፈጸመው ግፍና ጭፍጨፋ በትህነግ ሰዎች አንደበት በጅግንነት ” መብረቃዊ ጥቃት” ተብሎ ሰበር ዜና ሆነ። ዕድሜውን በትግራይ በረሃ፣ ድንበር ሲጥብቅና ትግራይን ሲያለማ የኖረ ወታደር ለማመን በሚከብድ ክህደት በጥይት ብቻ ሳይሆን ስለት አረፈበት። በተሽከርካሪ ዳመጡት። አስከሬኑንን እርቃን አድርገው ለጅብ አስበሉት። የኢትዮጵያ መከላከያ በዚህ መልኩ ትግራይ ላይ ታሪኩ በክህደትና ክህደቱን ” ጅግንነት” ብለው ባወደሱ የትህነግ የመዋቅር “ሰዎች” ተዘጋ። ይህ እብሪት ከተቀለበሰ በሁዋላም ዳግም መከላከያ ትግራይ ምድር የሆነውን አባላቱ ተናገረውታል። ታሪክ ወደፊት ለመጪው ትውልድ ይዘግበዋል። ይህ ሁሉ የተፈጸመው በሁሉም ብሄሮች መሆኑ ደግሞ ክህደቱ አድራሻ እንደሌለው፣ ሲፈልግ አድራሻ የሚቀያይር፣ ሲፈለግ …. ወደ ፍቅር፣ ሲፈለግ ወደ አሽክርነት …

የኢትዮጵያ መከላከያ በቁጥር አነስተኛና ለአንድ መከላከያ ሃይል የሚያስፈልጉ ዩኒቶች ተጓድለውበት ስለነበር፣ ቀድሞም አፈጣጣሩ ሚዛን የጠበቀ ባለመሆኑ ትህነግ አማራና አፋር ክልልን ለመውረር ቻለ። ያደረገውን ሁሉ አድርጎ፣ የከሰረውንም ከስሮ በሃይል ከያዛቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች ሲባረር መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ መታዘዙ በርካቶችን ቢያስቆጣም፣ ለሰላም አንድ ታላቅ ተስፋ ሆኖ ነበር። ግን ተስፋው ብዙም አልቆየም።

አሁን ምክንያቱ ግልጽ ባልሆን መልኩ ትህነግ አፋርን ዳግም ወሯል። መውረሩ ብቻ ሳይሆን ንጹሃንን በከባድ መሳሪያ በመኖሪያቸው እያሉ አግይቷቸዋል። ሕጻናት የመሳሪያ እሳት እንድዷቸዋል። ከአፋር የሚወጡ ምስሎች ህሊናን የሚፈታተኑ ናቸው። ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ወረራው መጨረሻው ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ ያሰበውን ያሳካ አይሳካ የሚታወቅ ጉዳይ ባይኖርም፣ ዕልቂቱ ከዚህም ከዚያም ቀጥሏል። አሁንም በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚታዩ የትግራይ ልጆች አስከሬን ልክ እንደ አፋር ህጻናት ጉዳይ ያማል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ለምንድን ነው? አፋር የትግራይን ሕዝብ ምን አድርጎ ነው እንዲህ የሚጨፈጨፈው? ጭፍራን ዘልቆ ገብቶ የነበረው የትህነግ ሰራዊት ለቆ ሲወጣ የአልጃዚራ የስፍራው ዘጋቢ ” መተዛዘን ብሎ ነገር የቀረ የመስላል። አስከሬን በአስከሬን ነው” ሲል ስሜቱ እየተናነቀው ዘግቦ ነበር። ምን አለበት በዚያ ቢያበቃ!!

በአፋር ክልልም መጋሌ፣ ኢሬብቲ፣ በራህሌ፣ ዳሎልና አብዓላ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ምዕራብ ሽራሮ ከተማ፣ በወልቃይት ፀገዴ፣ በምዕራብ ዞን ሁመራ አቅጣጫና፣በሰሜን ጎንደር በዋግ ኸምራ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞኖች ውጊያ እንዳለ ሪፖርት ቀርቧል። የትግራይ ሚዲያዎችም ተጨማሪ ወታደሮች አሰልጥነው እንዳስመረቁ እየተናገሩ ነው። “ዳግም ወረራ እንዳይፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ” የሚል ዜናቸው እየተከታተለ እየተሰማ ነው። በዚያው መጠን አውሮፓ ሆነው ” ግብጽን፣ ሱዳንን፣ ያገኘነውን ሁሉ በመጠቀም …” እያሉ ውጊያውን የማስፋትና ዳግም ወደ መሃል አገር የመመለስ ዕቅዳቸውን እያስተጋቡ ነው። ሰላም እንዲወርድ መስበክ የሚገባቸው ዕድሜ ጠገብ የቀድሞ ባለስልጣናት ግጭት እንዲስፋፋ እየወተወቱ ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን ከትግራይ የሚወጣው ዜና ዕረፍት የሚነሳ ቢሆንም ሲጨነቁ አይታይም። የትግራይ ንጹሃን እስከመቼ ይሰቃያሉ? ለምንድንስ ነው ይህን ሁሉ ዋጋ እንዲከፍሉ የሚደረገው? የትግራይ ህዝብ በሰላም በድህነቱ እንዳይኖር ከራሱ አብራክ የወጡ የሚፈርዱበት በምን ምክንያት ነው? ሃያ ሰባት ዓመታት ስልታን ላይ እያሉ አገር መሆን፣ መገንጠል፣ ታይዋንን መተካት፣ በሃብት መጥለቅለቅ፣ “ልዩ ነን” እንደሚሉት ልዩ መሆን እየቻሉ ዛሬ ሁሉም ነገር ከእጅ ሲወጣ ሕዝብን አግቶ ቁማር መጫወት ምኑ ነው የሚያረካቸው? ሌሎችስ እንዴት ይህን አይጠይቁም?

See also  ላይቤሪያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ ፣ሶማሊያ፣ በችግራቸው ወቅት ስለደረስክላቸው ውለታህን አልረሱም ከአማፂያን አብረው ደምህን አላፈሰሱም

በሌላውም ወገን እንዲሁ ነው። “በለው፣ ምታው፣ ደምስሰው፣ አስወግደው፣ ንቀለው…” የሚሉ ይበዛሉ። ለመነጋገርና ችግሩን “እስካሁን የሆነው ይብቃ” በሚል ለማስወገድ ሙከራ ሲደረግ ” የወዮልህ” ቀረርቶ ያሰማሉ። ከቀውስና ከችግር ለማትረፍ ሌት ተቀን መርዛቸውን ይረጫሉ። አማራ ክልልም ሆነ አፋር ክልል የሆነውን በመዘንጋት ሌላ የጦርነት ዙር እንዲካሄድ ይወተውታሉ። የሰው ልጅ እንዲረግፍ፣ ተጨማሪ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ( እየተፈናቀሉ ነው)  “ከአፋርና አማራ ክልሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ ተፈናቃዮች ወደ ውቅሮ አፅቢና አጉላዕ ወረዳዎች ደርሰዋል፤ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደርም እንዲሁ የተፈናቃይ ዜጎች ሪፖርቶች እየደረሰኝ ነው” ሲል ኦቻ ሪፖርት አድርጓል። “ይህ የዜጎች ስቃይ እንዴት አይሰማንም? እስከመቼ ነው በዚህ ደረጃ ደንቁረን ጦርነትን ብቻ አማራጭ የምናደርገው? ትህነግን በሌላ አማራጭ ማሸነፍ የሚቻልበት መንገድ ለምን አይፈለግም…” ብለው የሚጠይቁና የሚተነፍሱ የቀውስ ንግዱን ስለሚያዳፍኑት ይረገማሉ። በደቦ ይወነጀላሉ። ጎበዝ ምን እስክንሆን ነው የሚጠበቀው? እስከመቼስ ነው የሌባና ፖሊስ ኑሮ የሚኖረው? በህዝብ ስቃይና ደም ውስጥ ትርፍን ማሰብ ምን የሚሉት፣ እንዴት አድርገው የሚጠሩት ተግባር ይሆን?

የትግራይ ሕዝብ፣ የትግራይ ሕጻናት፣ የትግራይ ምስኪን አዛውንቶች፣ በጥላቻ እየተኮተኮተ ያደገው የትግራይ ታዳጊና የትህነግ አመራሮች አንድ አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም። እናም እይታን በማስተካከል ለጦርነት ከሚከፈለው ዋጋ በላይ ይህን የተዛባ አካሄድ ለማረቅ መስራቱ ያዋጣል። የትግራይ ልሂቃንም ሆኑ ፖለቲከኞች ለህዝባችሁ ስትሉ ከግትርነትና ከማይሆነው የወጣችሁበት የጥጋብ መሰላል በመውረድ ለሰላም መፍትሄ ሃሳብ አቅርቡ። ከወንድሞቻችሁ ጋር በውጭም በአገር ቤትም አንድ ላይ ምከሩ። የመሬትና የርስት ጉዳይ ከቀናነትና ከልብ ከመነጨ ዕርቅ በሚቀዳ ተስፋ የጋራ መተቀሚያ እንጂ መዋጊያ እንዳይሆኑ ማድረግ ያቻላል።

ዛሬ እናቶች ሜዳ ላይ እየወለዱ ነው። የሚሞቱትን ቤቱና በረሃው ይቁጠረው። ህጻናት ትምህርት አልባ ሆነዋል። ባማያውቁት ምክንያት በአባቶቻቸውና ታላቆቻቸው ክፋት ተስፋቸው ተሟጧል። ረሃብ እየገረፋቸው አይናቸው ጎድጉዷል። ቅስማቸው ተሰብሯል። ይህንኑ ምስል እያንጠለጠሉ የሚነገዱ ክፉዎች፣ ከዚህ አሳዛኝ ምስል ስር አሁን መርዝ ይረጫሉ … እዛም እዚህም ቀናዎች ድምጻችሁን አሰሙ። ሚዲያዎችም ከሳንቲም ለቀማ በመውጣት እርቅን የሚያበረታቱ መድረኮችን ክፈቱ። ይህ መከራ ያበቃ ዘንዳ ካልተጋን አያይዙ ሁላችንንም አመድ የሚያደርግ ነውና እንፍጠን። ሰላም የሚያመጣ ከሆነ እገሌ ከገሌ ሳይባል ምክክር ይደረግ። በንግግር መፍትሄ እንዲመጣ እንሟሟት።ጫና እንፍጠር። ከታች ያለው የአማራና የአፋር የቀውስ መረጃ በድንብ ያልተካተተበት የጀርመን ድምጽ ትርጉም ሪፖርት ነው። ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ ድርቅ እያመሰው ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች ሞተዋል። ይህን ጉድ ተሸክመን ነው ” ግፋ በለው” የምንለው። ሰበር ዜና ተያዘና ተለቀቀ እያልን እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ሪፖርት የምናደርገው። በየ ሞሉ ልብስ ሲሰርቅ የተያዘ ሌባ አክቲቪስት መነገጃ የምንሆነው እስከመቼ ይሆን?

See also  የምርጫውን ሂደት ለማወክ የሞከሩ 123 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ! ፀረ ሰላም ሃይሎች ተመደምስሰዋል

በሰሜን ኢትዮጵያ በሚታየዉ ጦርነት ምክንያት በትግራይ ላይ እገዳ ከተጣለ ወዲህ ወደ 40 ከመቶ የሚጠጋ የትግራይ ነዋሪ «ከፍተኛ የምግብ እጥረት» አጋጥሞታል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዛሬ አስታወቀ።

የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበዉ የመንግስታቱ የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) ባወጣው መግለጫ “አዲስ በተካሄደዉ የምግብ ዋስትና ግምገማ መሰረት 40 በመቶ የሚሆኑ የትግራይ ነዋሪዎች ከ15 ወራት ግጭት በኋላ በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን አስታውቋል ።

ይህን ያህል ሕዝብ በትግራይ ለምግብ እጥረት የተጋለጠዉ የዕርዳታ ቡድኖች በነዳጅ እና በአቅርቦት እጥረት የተነሳ እንቅስቃሴያቸውን ለመግታት እየተገደዱ በመሆናቸውና በሰሜን ኢትዮጵያ በሚታየዉ አዲስ ጦርነት ምክንያት ዕርዳታ የሚገቡባቸዉ መንገዶች በመገደባቸዉ መሆኑን የፈረንሳዩ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

እንደ ዓለሙ የምግብ ድርጅት 83 በመቶ የትግራይ ነዋሪዎች የምግብ ዋስትና እጦት ዉስጥ ናቸዉ። ዛሬ አርብ ከቀትር በፊት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ማስተባበሪያ ጽ/ ቤት እንዳስታወቀዉ፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁሉም የዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ነዳጅ የላቸዉም፤ በእግር ለተቸገሩ ነዋሪዎች እያደረሱ ያሉትም የተመጣጠነ ምግብ ርዳታ ቀንሷል።

«ቤተሰቦች እራሳቸውን ለመመገብ ሁሉንም ዘዴዎች እያሟጠጡ ነው፤ ሦስት አራተኛ የሚሆነዉ የትግራይ ነዋሪ ህይወቱን ለመትረፍ የመቋቋም ስልቶችን ሁሉ ይጠቀማል»” ሲል የፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የዓለም የምግብ ድርጅት አክሎ እንደዘገበዉ ከቅርብ ወራት ወዲህ በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን የትግራይ አጎራባች የሆኑት የአማራ እና የአፋር ክልሎች ዉስጥ እየጨመረ ያለዉ ረሃብ አደጋ ትልቅ የማስጠንቀቅያ ደወል ነዉ።

Leave a Reply