[ሰላም እንዴት] የድብረጽዮ የድርድር ዜና በእንግሊዝኛ

አሁን ላይ ችግር የሆነው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ “ መንግስት የፖለቲካ ሚስጢሩን ሁሉ ይነገረን” የሚለውና ሆን ተብሎ አጀንዳ የሚሰፈርላቸው ቡድኖች፣ ሳያውቁ የነዚህን ቡድኖች ጭራ ይዘው የሚኖጉዱት እንደሆኑ በተደጋጋሚ ቢገለጽም ሰሚ ያለ አይመስልም። ዛሬም ድሮ ሲነገር የኖረውን አሳብ በእንግሊዘኛ በመባሉ ብቻ ተሸክሞ ከማላዘን በዚህ መንገድ ” ሰላም እንዴት?” ብሎ መጠየቁ በቀለለ ነበር።

ፖለቲካ በባህሪው ሙሉ በሙሉ በግልጽ የሚጫወቱት ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያውቁት ሳይቀሩ መንግስትን ከዚህ ቀደም በየትኛውም ዓለም ታይቶ በማይታውቅ ደረጃ “ ሁሉንም ግልጽ አድርግና እንደተረት ንገረን፤ አለያ ወዮልህ” ይሉታል። ሕዝቡን ወደ ከፋ አቅጣጫ ለመንዳት በተተነፈሰ ቁጥር “ትንተናና፣ ዛሬ ምን ተባለ፣ወቅታዊ” በሚሉ ርዕሶች ለማሰብ እንኳን ጊዜ ሳይወስዱ ሁሉንም ጉዳይ ሲያቦኩ ውለው ያመሻሉ። አሁንም ያልገባቸው እነዚህኑ ወገኖች በመከተል “ ፈረደብን” ሲሉ ፎቶ እየተሸከሙ ይህንኑ ቅጥ አንባሩ የጠፋ ዝባዝንኬ ያራባሉ። በገንዘብ ይደጉማሉ። በወሬ የፈረሰ ተመልሶ የተሰራ አገር ያለ ይመስል አገራቸውን ለማፍረስ ይጣደፋሉ።

ሁል ተንታኝ። ሁሉ ተቺ። ማህበራዊ አውድ ያለው ሁሉ አስተባባሪ፣ አንቂ፣ አዋቂ … ሆነና የሚያረጋጋ ጠፋ። ውብ የሆኑ በጥናትና በእውቀት የተገነቡ አሳቦች ያሉዋቸውን ማዳመጥ፣ መከተል፣ ሃሳባቸውን መግዛት እርም ሆኑ ለቧልት፣ ለነቀፌታ፣ ትርጉም ለሌለው ዘምቻ፣ ለጎበዝ አለቃ፣ ለዱርዬ፣ ለተገዙ … እንዲህ መሰሎቹ ስር መዋል ምርጫ ሆነ። ስራቸው መዋል ብቻ ሳይሆን ለእንደዚህ አይነቶች ማጨብጨብ ተወደደ።ከዛም አልፎ “እኔም እንትናን ነኝ” የሚል መፍክር ሁሉ የወረደላቸው አሉ። ነብሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ” ጭብጨባ ጭንቅላት ያሳብታል” እንዳሉት፣ ጭንቅላታቸው አብጦ ሁሉም ራሳቸውን አዋቂ አደረጉ። እንዲህ ነው እየኖርን ያለነው። ደግ ስራ የምሰሩና በምክንያት ደርዛቸውን ጠብቀው የሚንቀሳቀሱትን አይመለከትም።

እንግዲህ ይህን የሚረዱና የሚያውቁ የሴራ አጀንዳ ሰፋሪዎች፣ ጊዜ ጠብቀው፣ አየሩን አይተው መተሬ እንደጎረበጠው አሜባ ተኮማትረው ከተሸሸጉበት እየወጡ በስልት ሲተነፍሱ ጩኸቱ ከዳር እስከዳር ይዳረሳል። አጀንዳ ሲሸጡ፣ በፈረደበት ባንዲራና አገር ወዳድ ሕዝብ ስም የሚምሉ በተቆርቋሪነት ስም ይህንኑ አጀንዳ እያራቡ፣ ቀንድና ጭራ እያበጁለት፣ ያልተባለውን እየጨመሩ ህዝብ ላይ ያራግፉታል።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ከቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም ጋር ስለ ድርድር አወሩ በሚል፣ በቅጽበት ለትንተናና ለትችት የሚሯሯጡት ወገኖችና፣ አንዳንዶቹም በቅጡ እንኳን ሳያነቡት ወሬውን ለማራባት ካላቸው እሽቅድምድም በመነሳት የማህበራዊ ሚዲያውን ሳያውቁት በተላላኪነት ያጥኑታል።

See also  የዶ/ር አረጋዊ ስልታዊ አቀራረብና የአብርሃ ደስታ የፊት ለፊት ግትር አቋማቸው ሲፈተሽ!

ደብረጽዮን ምን አሉ? በእንግሊዝና ተናገሩ ከመባሉ ውጪ ምን አዲስ ነገር ተናገሩና ነው ጫጫታው?

በዋናነት ሲጨመቅ የአማራና የኤርትራ ሃይሎች ከትግራይ ይውጡ። መሰረታዊ አገልግሎት እንዲጀመር፣ ብሄራዊ ውይይት እንዲደረግ፣ ጦርነት እንዲቆምና የተኩስ አቁም በስምምነት እንዲታወጅ ነው። ይህ በፊትም ሲባል የነበረ ነው።

“ወልቃይት ጠገዴን ልቀቁና ውጡ” የሚለው ጥያቄና ኤርትራን ከድንበር ለቀቂ፣ እንዲሁም የተቋረጠ አገልግሎት እንዲጀመር በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረው ጥያቄ መደገሙ ምን ያስገርማልና ነው አገር ይያዝ የሚባለው? አዲስ የተነሳው ጉዳይ “በተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ተደርጓል” ማለታቸው ነው? ይህን ነጮቹ አልነገሩንም? እኛስ አናውቅም ነበር። ትግራይ ሲደረግ የነበረው ምልልስ ለሽርሽር?

ኦባሳንጆ ትግራይ ተመላልሰዋል። የአሜሪካ ባልስልጣናትም ሄደዋል። ፌልትማንም ሲያነግሩዋቸው ነበር። ሁሉም በየፊናቸው፣ የተባበሩት መንግስትም ድርድር እንዳለ፣ ድርድሩ ጥሩ ተስፋ ማሳየቱን ሲናገሩ ተሰምቷል። ዶክተር ደብረጽዮንም ይህንኑ ነው የደገሙት። “ መሻሻል አለ” ብለዋል። ይህንን ኦባሳንጆ “ከሁሉም ወገን በጎ ምላሽ አለ” ሲሉ ገልጸውት ነበር። አንቶኒ ጉተሬዝም “ በሰማሁት ተደስቻለሁ” ሲሉ ተስፋ ያለው ዜና መናገራቸውን ገልጸዋል።አሜሪካም ” መልካም ጅምር” ብላለች። እንግሊዝና ጀርመንም “እሰየው” ብለዋል። ዛሬ ደብረጽዮን ድሮ በአማርኛና በትግርኛ ያሉትን በንግሊዝና ስለተናገሩ ምን አዲስ ነገር አለው?

አቶ መስፍን ምንም እንኳን ከኤፒ ጋር ላደረጉት ውይይት የሰጡት ምክንያት ባያሳምንም ሃሳባቸው ተዛብቶ መቅረቡን አመልክተዋል። ዜናውና እሳቸው ያሉት አንድ አይደለም። ድርጅታቸው መግለጫ እንደሚያወጣ አመላክተዋል።

ይልቁኑ “ መሻሻል ካለ ዳግም ጦርነት ለምን ተፈለገ?” የሚለውን ጉዳይ መመልከት እርፋና ይሆን ነበር። ከዚያም በላይ በተዘዋዋሪ ለሚያነጋግሯቸው አካላት የኢትዮጵያ መንግስት በዋናነት ምን ጥያቄ እንዳቀረበ? ይህ አሳብ ለምን በጠያቂው ቢቢሲ በኩል አልተነሳም? የሚለውን ሰርስሮ ሪፖርቱን ሙሉ ማድረግ በተቻለ ነበር።

በአሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ መስፍን ተገኑን ጠቅሶ የተወላገደ ዜና የጻፈው ኤፒ እንዳለው ሳይሆን፣ አቶ መስፍን ዜናው በጋዜጠኛዋ ፍላጎት ተገልብጦ መሰራቱን በገለጹበት ጽሁፍ እንዳሉት። ከሌሎችም ምንጮች እንደተሰማው መንግስት የትህነግ ሃይል ትጥቅ እንዲፈታና ሃይሉን እንዲበትን ቅድሚያ ጥያቄ ቀርቦላታል። ይህን እውነት ቢቢሲም ደበረጽዮንም፣ በትንተና ስም የሚያደነቁሩንም ያውቃሉ። ግን ሃሳቡ ለመንግስት መልካም ስም የሚያሰጥ በመሆኑ ይጠየፉታል። ሊያነሱት አይወዱም። እንዲያከፋፍሉት ለተሰጣቸው አጀንዳ ስለማይመች ያጨልሙታል።

See also  ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ስንዴ እንድትልክ የሚያስችል ስምምነት ተደረሰ

ሌላው ዶክተር ደብረጽዮን ያነሱት አሳብ ብሄራዊ ውይይት ነው። ይህም ቀደም ሲል “የሽግግር መንግስት” ሲባል የነበረው የአቋራጭ ስልጣን መወጣጫ መንገድ ነበር። ዋናው የትህነግ ሳምባ አሜሪካም ሆነች ዓለም ትህነግ የሚባለው ድርጅት ድሮ ሲፈጽም ከነበረው ዝርፊያና የክፋት ተግባሩ በተጨማሪ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣጡትን የመከላከያ አባላት በክህደት የጨፈጨፈና ያረደ እለት ከኢትዮጵያዊያን ጋር መቆራረጡን በግልጽ ያውቃሉ። በአደባባይ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ላይ የጫኗቸው እነ ኮሎኔል ኸርማን ኮኾን ሳይቀሩ ይህን ስለሚረዱ “ መሟሟት አለበት” ማለት ደርሰዋል። ፌልትማንም “ 1991 ላይ የተቸከሉ” ሲል ዓለም ፊት በፖለቲካ ጥፊ አጩላቸዋል። ከዛ በሁዋላ አሜሪካ ቀስ እያለች መንሸራተት ጀምራለች። ጥያቄው ይህ መሆን ሲገባው የቀድሞውን ሃሳብ “ በተዘዋዋሪ ድርድር” በሚል አንድ ቁንጽል ሚስጢር ያልሆነ አሳብ ተደግፎ እንዲቀርብ ከመደረጉ ውጪ አዲስ ታሪክ የለውም።

በትግራይ ሕዝብ ላይ ከታወጀ የዘር ማጥፋት ዘመቻ መትረፋቸውን፣ “ወድማለች” ያሏትን ትግራይን አስመልክቶ በጥቅሉ ጥፋተኞች እንዲጠየቁ ለማድረግ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ተጋራዊ እንዲሆን እንደሚፈልጉ በግርድፍ የተናገሩት የትህነግ መሪ አማራና አፋር ክልልን ወረው የፈጸሙት፣ ያስፈጸሙት፣ አሁንም እያስፈጸሙ ያሉትን ይህንኑ ወረራ ህጋዊና ለነሱ ብቻ የተፈቀደ ህጋዊ ተግባር ስለመሆኑ ሲጠየቁም ሲመልሱም አልተደመጠም። ይህን ድንግዝግዝ ነው “ መሻሻል አለ” በሚል በስመ ኢትዮጵያዊነት ስም እንደ ትልቅ ጉዳይ በማንሳት ትንተናው እየወረደ ያለው። በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀስው።

ዕብደት እንዳይባል፣ የዕብደትን እንኳን ደረጃ የማያሟሉ በፈረደበት ባንዲራ እየተጠቀለሉ፣ በተቆርቋሪነት ስም፣ በማማተብና በሶስቱ ስላሴዎች ስም ቡራኬ እየጀመሩ የተጫኑትን እርባና ቢስ ሸቀጥ የሚያራግፉ እውነት የሕዝብ፣ በተለይም የህጻናትና አረጋዊያን ስቃይ ክሳዘናቸው ስለምን ሰላም እንዲሰፍን ጫና አይደርጉም? ስለምን ሰላምን የሚዘምሩ መልካም ሰዎችን እየፈለጉ ወደፊት አያመጡም?

በተተነፈሰ ቁጥር ቀንድና ጭራ እየቀጠሉ የሚጮሁ በቀቅኖች የአገሪቱን መከራ በማብዛት፣ በስቃይ ውስጥ መነገድና ማትረፍን እንጂ የሰላም መንገድ አይመቻቸውም። ቢሳካና ሰላም ቢወርድ ጨርቃቸውን የሚጥሉት እነሱ ናቸው።


  • ከትግራይ የሚወጣው ዜና የሚያም ነው።
  • ከአፋር የሚወጣው ዜና የሚያም ነው
  • ከአማራ ክልል የሚወጣው ዜና የሚያም ነው
  • ቦረናና ሶማኤ ክልል ድርቅ ያደረሰው ጉዳት ይጨንቃል።
  • ኦሮሚያ ሞትና መፈናቀል አለ .... ምን ቀረንና ነው የሰላም አሳብን የምናወግዘው? ይልቁኑ ከልብ ከሆነ ብሎ መመኘት አይቀልም? ዛሬም ምግብፈላጊው ዘጠኝ ሚሊዮን ደርሷል። መድረሻው የት ነው? የተመቸ ኑሮ እየኖሩ አገር ማወክ አይበቃም?
See also  ምክራችን አንድ ነው!

የተባበሩት መንግሥታት፣ በኬንያ፣ የአፍሪካ ህብረት በተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር የማስማማት ስራ መጀመራቸው ምንም ድብቅ የሌለው ጉዳይ ነው። ቢሳካ ሰላም ቢወርድና ችግር ላይ ያሉ ዜጎች ሁሉ ወደ መደበኛ ህይወታቸው ቢመለሱ እሰዬው ነው። ይህንን ለማድረግ ለጦርነቱ ከወታው በላይ በሁሉም መስክ ትብብር ቢደረግ ያማረ ነው። አስራ አምስት ወር በሚታወቅ የእብሪት ጦርነት፣ ከዛ ቀደም በድምሩ አራት ዓመት በሴራና በተላላኪዎች ተሳትፎ ኢትዮጵያዊያን ያልደረሰባቸው ግፍና ስቃይ የለም። ይህን ሁሉ የሆነች አገር፣ መከራው እንዳላንገፈገፋት ተቆትሮ፣ በየአቅጣጫው አጋጣሚውን ተጠቅመው የተደራጁ “የጎበዝ አለቆች” እያናፉባት ነው። ታላቁን ጀግና ሕዝብ “ፋኖ” መወሸቂያቸው አድርገው በመከራ የተሰፋውን ክፈተት መልስው ሊበረግዱትና የክልሉን ሕዝብ ሊያዋርዱት እየሰሩ ነው። ሚዲያ ካለ ይህንን ነው አወላልቆና አንጋሎ ሳያድር ዛሬውኑ ለአየር መስተት የነበረበት።

በየጎጡ የሚከፈላቸውና ቃል የተገባላቸው፣ ሌላባ ባለሃብቶች ሳይቀሩ እያካሄዱ ያሉት ተግባር ጭምብሉ ወልቆ እየታየ ዝምታ ተመርጦ ደብረጽዮን የድሮውን አሳብ “ተዘዋዋሪ ድርድር” በሚል አጅቦ በፈረንጅ ሚዲያ ሆን ብሎ መናገሩ ላይ መረባረብ አይነፋም። የአፍሪካ ጉባኤ ካለቀ በሁውላ ሁሉም ነገር እንደሚከስም እየታወቀ “ አለን” ለሚለው የታሰበበት ጩኸት ይህን ያህል ቦታ መስጠት ….

በኢትዮጵያ የተዋጣላቸው አምባሳደሮች ከጦር ሰራዊቱ የወጡ ናቸው። ይህን ዘንግተው ገና ምድቡ ደቡብ ሱዳን የሁን ሰሜን፣ ግብጽ ይሁን ሩሲያ ሳይረዱ በግርድፍ ሲሳደቡ የነበሩ፣ ዛሬም ተመልሰው ይህንኑ እየደገሙ ነው።

ለማንኛውም ደብረጽዮንም ሆነ መንግስት ቢስማሙና ይህ መከራ የሰፈረበት መከረኛ ሕዝብ ቢገላገል ምንኛ ባማረ ነበር። አይሆንም እንጂ። ትህነግ አሁን ባለው ቁመናው ከጦርነት ውጭ ማንም ዓይነት መንገድ አይመቸውም። ምክንያቱም ሰላም ያጠፋዋልና። ሰላም ከመጣ የሚጮህበት ጉዳይ ሁሉ ይቀራል። ጠላት ካልፈጠረ፣ ግጭት ካላመረተና የሴራ ትርምስ ካልፈጠረ መኖር የሚያስችል ሴል የለውምና። ሲጀመርስ ትግራይ ሄዶ ማን ነካው? ዝም ብሎ አይኖርም ነበር? ለምስኪኑ ሕዝብ ሲባል ቀና አሳቢዎች ተረባረቡ። አሳዛኙን የማህበራዊ ሚዲያ ገበያ ታገሉት።

Leave a Reply