”ባለፈ ታሪክ እየተጣላን ለባሰ ችግር ከምንዳረግ በይቅርታ ማለፍ ተመራጭ ነው» – መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ

አዲስ አበባ፡- ባለፈ ታሪክ እየተነታረክንና እየተጣላን ለባሰ ችግር ከምንዳረግ ያለፈውን ጠባሳ በይቅርታ ማለፍ ተመራጭ መሆኑን መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ ገለጹ፡፡

መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ አገራችን ውስጥ ያለው ንትርክና ፀብ የወንድማማች ፀብ ነው፤ ወንድማማች ደግሞ የሆነ ግዜ ይጣላል ፤የሆነ ጊዜ ይታረቃል፤ ከዚህ አኳያ ባለፈ ታሪክ እየተጣላን ለባሰ ችግር ከምንዳረግ በይቅርታ ማለፍ ተመራጭ ነው፡፡

ባለፈ ታሪክ እየተነታረክና እየተጣላን ለባሰ ችግር መዳረግ የለብንም ያሉት መጋቤ ሀዲስ፤ ያለፈ ታሪክ ሊያባላን አይገባም፤ ይህ ያደረ ቂምም የነገውን ትውልድ ችግር ውስጥ ሊከተው አይገባም፤ በዘመን ተሻጋሪው የይቅርታ እሴታችን ልንፈታው እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡ 

እንደ መጋቤ ሀዲስ እሸቱ ገለጻ፤ ችግሮችን በእርቅ በመፍታት ሁለት ጥቅሞች አሉት፤ የእርቅ ትልቁ ጠቀሜታ ትኩስ ቁስልን በመፈወስ ፤ያለፈውንም ቁርሾ ማስረሳት ነው፡፡ ከዚህ መነሻነት በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ወገኖች በኩል እርቅና አገራዊ መግባባትን ፈጥሮ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ሁሉ ምሳሌ መሆን ይኖርብናል ብለዋል፡፡ 

ታሪክ በልኩ እንዲሰፋን ልንፈቅድለት አይገባም ያሉት መጋቤ ሀዲስ እሸቱ፤ ታሪካችን ውስጥ የማያስማሙን ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም የሚያስማሙንን ነገሮች ይዞ በይቅርታ ማለፍ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ 

እንደ መጋቤ ሀዲስ እሸቱ ገለጻ፤ አሁን ያለንበት ዘመን ደግሞ ተቀራርቦና ተነጋግሮ የሚሰራበት እንጂ ለፀብ የሚዳርግ አይደለም፤ ችግር አለ የሚሉ አካላት ሁሉ ጉዳያቸውን ወደ ጠረጴዛ አምጥተው ሊነጋገሩበትና ሊፈቱት ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ንትርክና ፀብ የልሂቃኑ እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ አይደለም ያሉት መጋቤ ሀዲስ፤ የማዕከላዊ መንግሥትና ትግራይ አካባቢ ላይ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ልዩነታቸውን በንግግርና በውይይት መፍታት ከቻሉ ሕዝቡ መሀል የሚቀር ቁርሾ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ 

ብዙ የአፍሪካ አገራት ታሪካቸው የቅኝ ግዛት ነው ፤ ኢትዮጵያውያን ግን የመለያየትን ችግር መፍቻ የሦስት ሺህ ዘመን እርሾ አለን ያሉት መጋቤ ሀዲስ ፣ባረጀው ችግር ላይ ይቅር መባባልን በተግባር ተርጎሞ ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ መሻገር እንደሚገባም መክረዋል፡፡

መጋቤ ሀዲስ እንደገለፁት፤ገለልተኛ ተቋማት በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መሀል የሚታየውን ንትርክ በሰላማዊና ይቅር በመባባል እንዲፈቱ ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በተለይ የሀይማኖት ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶችና መገናኛ ብዙሃን የአሸማጋይነት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ጥር 22 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply