የፋኖ ሚና እና የወደፊት እጣ ፈንታ…(ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ)

«ለምን ቢባል በፋኖ ስም ከባለሀብቶችና ዲያስፖራው ገንዘብ እየሰበሰቡ ከተማ ውስጥ ሆነው ቀዝቃዛ ቢራና አረቄ እየጠጡ መንጎባለልን ያስቀርባቸዋልና ነው»

” የፋኖ አደረጃጀት እንዴት ክልላዊ መልክ ይኑረው በሚለው ላይ የመፍትሄ ሀሳብ ይዞ እንደሚቀርብም የሚጠበቅ ሲሆን እውነተኛ ፋኖዎችን በሚገባ ለይቶ ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸውና በፋኖ ስም የሚነግዱትን ደግሞ በትክክል በመለየት ከመንግስት ህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር ስርአት የማስያዝ ስራ ይሰራል ተብሎ ይታመናል”

ፋኖ የሚለው ስያሜ ሲነሳ በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የአማራ ክልልና ሕዝብ ቀድሞ ሊታሰበው ይችላል። እውነት ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ስም አዘውትሮ የሚጠቀመው የአማራ ክልልና ሕዝብ እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም ፋኖ የሚላው ስያሜ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴት እንደሆነ ማስረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም ውስጥ የቅርቡን የ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ዋነኛ መዝሙር:- ፋኖ ተሰማራ፣ ፋኖ ተሰማራ፣ እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼጉቬራ።

የሚል የነበረ መሆኑን በግንባርቀደምነት ማንሳት ይቻላል። ሆቺሚኒ የኤዥያዋ ቬትናም አርበኛ ሲሆን ቼጉቬራ ደግሞ የላቲን አሜሪካዋ አርጀንቲና የነጻነት ታጋይ መሆኑ ይታወቃል። የ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ደግሞ የዛሬን አያድርገውና የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ታጋዮች ያካተተ እንደነበር ይታወሳል። ስለሆነም ፋኖን የአንድ አካባቢ አድርጎ መረዳት ከመነሻውም ትክክል አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

እንደመግቢያ ይህን ካልሁ ወደ ዋናው ጉዳዬ ልምጣ፣ ቀደም ሲል የአማራ ክልል ባለስልጣናት፣ ሰሞኑን ደግሞ የብሔራዊ ጸጥታ ም/ቤት ባካሄዷቸው ተከታታይ ስብሰባዎች የአማራን ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ነው ብለው በመፈረጅ ሊመቷቸው ነው የሚሉ መረጃዎች ወጥተው የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል። ይህን ተከትሎ የብሔራዊ ደህንነት መ/ቤት ሀላፊ የሰጡት መግለጫም ያላስደሰታቸው ወገኖች አሉ።

እኔ ባለኝ መረጃና ግንዛቤ መሰረት ይኸ የሚባለው ነገር ሁሉ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተና ትንሽ ነገርን በመያዝ በእጅጉ አጋኖና አዛብቶ የማቅረብ አባዜ የተጠናወተው የመረጃ አቀራረብ ይመስለኛል። ምናልባትም የተወሰኑ ፋኖ ያልሆኑ ነገር ግን እንደ ፋኖ መታየትና መጫወት የሚፈልጉ እና ይህን ሁኔታ በማራገብ ገንዘብ መሰብሰብ የሚሹ ወገኖች የሚያራግቡት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ለምን ቢባል ከሳምንት በፊት የአማራ ክልል ባለስልጣናት በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የፋኖ መሪዎችን ሰብስበው ያወያዩ ሲሆን ፋኖዎች የተጫወቱትን ጉልህ ሚና በማድነቅና እውቅና በመስጠትም ጭምር ሸልመዋቸዋልና። ከዛም አልፎ ለወደፊቱ እንዴት መቀጠል እንዳለባቸውና ከመንግስት የህግ አስከባሪና የጸጥታ አካላት ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ግንኙነት ለማመቻቸት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ይኸ ኮሚቴ የፋኖ አደረጃጀት እንዴት ክልላዊ መልክ ይኑረው በሚለው ላይ የመፍትሄ ሀሳብ ይዞ እንደሚቀርብም የሚጠበቅ ሲሆን እውነተኛ ፋኖዎችን በሚገባ ለይቶ ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸውና በፋኖ ስም የሚነግዱትን ደግሞ በትክክል በመለየት ከመንግስት ህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር ስርአት የማስያዝ ስራ ይሰራል ተብሎ ይታመናል።

እንግዲህ ይኸ ሁኔታ ያስፈራቸውና ጭር ሲል አልወድም የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ይህንን የጋራ ውሳኔ አጥብቀው ቢቃወሙና አዛብተውም በመተርጎም ቢያቀርቡ የሚገርም አይሆንም። ለምን ቢባል በፋኖ ስም ከባለሀብቶችና ዲያስፖራው ገንዘብ እየሰበሰቡ ከተማ ውስጥ ሆነው ቀዝቃዛ ቢራና አረቄ እየጠጡ መንጎባለልን ያስቀርባቸዋልና ነው።

እናም ቀደም ሲል ጀምሮ ኢ-ፍትሀዊነትን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአሸባሪ ቡድኑን ወረራ በመቃወም የአማራን ሕዝብ ነጻ በማውጣት ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ለማድረግ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ፋኖ ተተኳሽም ሆነ ደረቅ ሬሽን መከላከያና የአማራ ልዩ ሀይል እያቀረበላቸው እንደሆነ አይተናል። ከዚህ ጎን ለጎን ህብረተሰቡም እንዳቅሙ እየደገፋቸው መሆኑንም በቅርብ የምናውቀው ጉዳይ ነው።

Leave a Reply