ኢትዮጵያ – የከፋ ድርቅ ሚሊዮኖችን ለችግር መዳረጉ ተገለጸ “ሸሽተው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙም ነው”

በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና እና ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች የከፋ ድርቅ በማጋጠሙ ሚሊዮኖች ለችግር መጋለጣቸውን ዩኒሴፍ ገለጸ።

በአራት አስርት ዓመታት ውስጥ ለከፋ ድርቅ መጋለጣቸው የተገለጸው ደቡብ፣ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በአራቱ ክልልሎች 7 ሚሊዮን በሚሆኑ ነዋሪዎች ላይ አስከፊ ችግር በመደቀኑ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ሊደርስላቸው እንደሚገባ ተገልጿል።

በአራቱ ክልሎች ባጋጠመው ሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች መጨናገፍ የተነሳም በተከሰተ ድርቅ በርካታ እንስሳት ሞተዋል፣ ሰብሎች ወድመዋል፣ የውሃና የምግብ እጥረት በርካቶችንም እያፈናቀለ መሆኑን በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጂያንፍራንኮ ሮቲግሊያኖ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የድርቁ ተጽእኖ እጅግ አስከፊ ነው። ሚሊዮኖች መተዳደሪያቸው እና ከብቶቻቸውን በማጣታቸው ሕፃናት እና ቤተሰቦቻቸው በሕይወት ለመትረፍ እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ” በማለት ሮቲግሊያኖ ተናግረዋል።

ተወካዩ ለቢቢሲ እንዳስረዱት 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን በርካቶችም ቀያቸውን ሸሽተው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙም ነው።

የዓለም አቀፉ ነፍስ አድን ኮሚቴም በደቡበ ምሥራቅ ኢትዮጵያና በሶማሊያ ያሉ ሰዎች በአርባ ዓመት ውስጥ ከታዩት የከፋ ድርቅ እንዳጋጠማቸውና በእነዚህ አካካቢዎች ለሰብዓዊ ቀውስ መባባስ ምክንያት መሆኑንም በቅርብ ጊዜ ባደረገው ግምገማ መመልከቱን በሪፖርቱ አስታውቋል።

በደቡብ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በእንስሳት መኖ እና ውሃ እጥረት ቢያንስ 267 ሺህ ከብቶች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ ታኅሣሥ ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በተጨማሪም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለአደጋ መጋለጣቸውንና ከብቶቹ አስቸኳይ መኖ፣ ውሃ እና ክትባትም ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።

በድርቁ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቁት የደቡብ እና ምሥራቅ ኦሮሚያ እንዲሁም የሶማሌ ክልሎች ቆላማ አካባቢዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ተወካዩ፣ በድርቅ በተጠቁት አካባቢዎች ከፍተኛ የውሃና የምግብ እጥረት በማጋጠሙት በርካቶችን ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

“በድርቅ በተጠቁ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ውስጥ፤ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ 225 ሺህ ገደማ ሕፃናት እና ከ100 ሺህ የሚልቁ ነፍሰ-ጡር እና የሚያጠቡ ሴቶች አስቸኳይ የተመጣጠነ ምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ሮቲግሊያኖ አሳስበዋል።

እስካሁን ድረስ ድርቅ በተከሰተባቸው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች 4.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለከፋ የውሃ እጥረት ተጋልጠዋል።

See also 
"የከፋ የስብዓዊ መብት ጥሰትና ወንጀል የፈፀሙ አካላትን በሽግግር ፍትሕ የመዳኘት ዕቅድ አለ ተብሏል"

በተለይም የንጹህ መጠጥ ውሃ አለመኖር የሕፃናት እና የሴቶች ሁኔታን ይበልጥ እያባባሰው እንደሚገኙም ገልጸው፤ “ሕፃናት የተበከለ ውሃ እንዲጠጡ ከተገደዱ ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት ዘንድ ዋነኛ የሞት ምክንያት ለሚሆነው ተቅማጥን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች የሚጋለጡ ይሆናል” በማለት ያስረዳሉ።

በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በድርቁ ምክንያት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በእጥፍ የጨመረ ሲሆን ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ህጻናት ላይ የተቅማጥ በሽታ ተጠቂዎች እየተመዘገቡ መሆኑም የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ ጠቅሷል።

በድርቁ ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እና የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር ባለመኖሩ በሶማሌ 99 ሺህ ተማሪዎች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ 56 ሺህ ተማሪዎች በአጠቃላይ 155 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

ድርቁ ለበርካታ ህፃናትም ከትምህርት ገበታቸው መራቅ ምክንያት መሆኑንም ዩኒሴፍ ገልጿል።

በዩኒሴፍ መረጃ መሰረት በቆላማ የሶማሌ እና የኦሮሚያ አካባቢዎች ከ155,000 በላይ ህጻናት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል።

በርካቶች ውሃ ለመቅዳት ረዥም ርቀት ይጓዛሉ አሊያም ተንከባካቢዎቻቸው ለቤተሰባቸው እና ለእንስሶቻቸው የሚሆን ውሃ ፍለጋ ሲሄዱ ሌሎችን ሕፃናት ለመጠበቅ ከቤት የሚውሉ በመሆኑ ነው ብሏል።

ከትምህርት ቤት ውጪ የሆኑ ልጆች የብዝበዛ ስጋት እንደተጋረጠባቸውና ወይም ወደ አደገኛ ወደሆኑ የችግር የመቋቋሚያ ዘዴዎች እንዲከተሉም ይገፋፋሉ ሲልም ዩኒሴፍ አሳስቧል።

በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2022 በአራቱም ክልሎች በግጭት፣ በድርቅ እና በኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በመሳሰሉ ምክንያቶች 850 ሺህ ያህል የሚገመቱ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጡም እንደሚችሉም ተጠቁሟል።

ዩኒሴፍ በአሁኑ ወቅት ለቀውሱ ምላሽ ለመስጠት ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በቅርብ በመቀናጀት፤ ነፍስ-አድን ዕርዳታዎችን ለተጎጂዎች ለማቅረብ እየተረባረበ እንደሚገኝም አስታውቋል።

ከነዚህም መካከል የውሃ ጉድጓዶችን እና የውሃ አካላትን መልሶ ማቋቋምን፣ አስቸኳይ የቦቴ ውሃ ዕደላን፣ የከፋ የምግብ እጥረት የደረሰባቸው ሕፃናትን መንከባከብን፣ እንዲሁም አስቸኳይ የትምህርት አቅርቦትን እና የሕፃናት ጥበቃ ድጋፍን ይገኝበታል።

የውሃ ማጓጓዣ፣ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች አቅርቦት፣ የህጻናት እና ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ ሴቶች የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ቅድመ ዝግጅት፣ የሞባይል ጤና እና የሥነ ምግብ ክሊኒኮችን ወደሚደረስባቸው አካባቢዎች ማሰማራት፣ የእንስሳት መኖ እና የእንስሳት ሐኪሞች ማሰማራትን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግም ኦቻ መግለጹ የሚታወስ ነው።

See also  በሳምንት ሶስት ቀናት በኦሮሚያ ባለስልጣኖች የህዝብ ጥያቄ አድምጠው ምላሽ እንዲሰጡ ታዘዘ፤ተቆጣጣሪ ግብረሃይል ይመደባል

ዩኒሴፍ በአራቱ ክልል በድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎችን ምላሽ ለመስጠት 31 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጠይቋል፤ በዚህም በአራቱ ክልሎች ውስጥ ያሉ ከሁለት ሚሊዮን የላቁ የችግሩ ተጠቂዎችንም ለመደገፍ ያስችላል ብሏል።

source – bbc

Leave a Reply