በአማራ እና አፋር ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከ36 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል

በአማራ እና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከ36 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንደኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባው የጤና ሚኒስቴርን ግማሽ በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም የም/ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ የተቋሙን የስድስት ወራት የስራ ክንውን ካቀረቡ በኋላ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየት ተነስተዋል።

በጦርነቱ የተጉዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት መልካም ቢሆንም ከደረሰው ጉዳት አንፃር በቂ አለመሆኑ በምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል።

ጦርነቱ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች ባሻገር በዙሪያው የነበሩ የጤና ተቋማት ሙሉ ትኩረታቸው ከጦርነቱ ጋር በተያያዙ አገልግሎቶች ላይ ተጠምደው ስለነበር ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋልም ብለዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በሰጡት ማብራሪያ በአማራና አፋር ክልሎች 42 ሆስፒታሎች፣ 523 ጤና ጣቢያዎች፣ 2 ሺህ 359 ጤና ኬላዎች በአሸባሪው ህወሃት ዘረፋና ውድመት ተፈፅሞባቸዋል ብለዋል።

በዚህም ምክንያት በአካባቢው ለማህበረሰቡ ይሰጥ የነበረው የጤና አገልግሎት መስተጓጎሉን ገልጸዋል።

የጤና ተቋማቱን ዳግም ስራ ለማስጀመር በተደረገው ርብርብ የጤና ሚኒስቴርና የተለያዩ ተቋማት ከ772 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድሃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎችና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የደብረብርሃን ጠቅላላ ሆስፒታልና ሌሎችም የጤና ተቋማት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በማከም በጫና ላይ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በመሆኑም የመድሃኒት፣ የህክምና መሳሪያና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት የወሊድ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች መደበኛ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

እንደ አጠቃላይ በአማራ እና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከ36 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ፤ በአማራ እና አፋር ክልሎች በጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት ተከትሎ ዳግም ስራ ለማስጀመር በልዩ ሁኔታ አቅዶ መንቀሳቀሱ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

የወደሙ የጤና ተቋማትን በመንግስት በጀት ብቻ መልሶ ማቋቋም የማይቻል በመሆኑ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ገንዘብ ማሰባሰብ መጀመሩንም አድንቀዋል።

ይሁን እንጂ በጦርነቱ ምክንያት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው በተለይም ሴቶችና ህጻናት ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ሚኒስቴሩ ሰፊ ክፍተት አለበት ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች በእቅድ የተመራ ሁለንተናዊ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መድሃኒቶችና የህክምና ግብዓቶችን እያሰባሰቡ በመደገፍ ገንቢ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነም ተገልፂል፡፡

Via -parliament (ዜና ፓርላማ ) ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም፤ አዲስ

Leave a Reply