ጥር 30 ለየካቲት 1 አጥቢያ ሌሊት 7 ሰዓት ጀምሮ በላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ በሚገኙ የወረዳ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ እና ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ላይ ጥቃት መድረሱ ተገልጿል። ጉዳዩን አስመልክቶ የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም በፋኖ ስም የሚነግድ የተደራጀ ቡድን ድንገተኛ ተኩስ ከፍቶ የሕግ ታራሚዎችን ማስመለጡን እና ከፍተኛ ዝርፊያ መፈጸሙ ተመላክቷል።

የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን መረጃው እንደደረሰው ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የጸጥታ ኀይሎች ስምሪት በመስጠት ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ ተናግረዋል። የችግሩን መንስኤ እና ውጤት በማጣራት በአጥፊዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ “ድርጊቱን የፈጸሙት ፋኖ ያልሆኑ ነገር ግን ፋኖ ነን የሚሉና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ናቸው” ብለዋል። እነዚህ አካላት ታራሚዎች እንዲያመልጡ ማድረጋቸውን እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ እና በሚሊሻ ጽሕፈት ቤት የነበረን ትጥቅ ዘርፈው መውሰዳቸውን አመላክተዋል።

ኮሚሽኑ መረጃ እንደደረሰው ከዞኑ የጸጥታ አካላትና እና የፖለቲካ መሪዎች ጋር በመተባበር የኦፕሬሽን እና የወንጀል ምርመራ ቡድን በማሰማራት የተፈጸመውን ወንጀል የማጣራትና አጥፊዎችን የመቆጣጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም ያመለጡ ታራሚዎችን መልሶ በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋልና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ነው የተናገሩት። ከተዘረፈው የጦር መሳሪያ መካከል የተወሰነውን መቆጣጠር እንደተቻለም አመላክተዋል።

የኦፕሬሽን እና የወንጀል ምርመራ ቡድኖቹ ቀሪ ሥራዎችን በትኩረት እየሠሩ ነውም ብለዋል።

በሂደቱ የዞኑ ሕዝብና የጸጥታ ኀይሉ ተቀናጅቶ አጥፊዎችን ለመቆጣጠር ርብርብ ማድረጉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የሕዝብ ብሶት የሚያንገበግበው እውነተኛ ፋኖም አጥፊዎችን ከገቡበት ገብቶ ለመያዝ እየተረባረበ ነው ብለዋል። ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ በዘለለ የሚናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ በሌሎች የግልና የመንግሥት ተቋማት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን አረጋግጠዋል።

በሌሎች አካባቢዎች መሰል ችግር እንዳይከሰት ሁሉም በንቃት አካባቢውን እንዲጠብቅም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሕዝቡም ከመላው የጸጥታ ኀይል ጋር በመሆን የክልሉ ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

(አሚኮ)

Leave a Reply