የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር በዞኑ ተደራጅተውና ታጥቀው በድንገት ተኩስ በመክፈት ማረሚያ ቤት ወረው በህግ ጠለላ ስር ያሉ እስረኞችን ለማስፈታት በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ አስራስድስት ሽፍቶች መገደላቸውንና ሃያ መማረካቸውን አስታወቀ።
“በፋኖ ስም የሚነግድ የተደራጀ ቡድን ድንገተኛ ተኩስ ከፍቶ የሕግ ታራሚዎችን አስመልጧል። ከፍተኛ ዝርፊያ ፈጽሟል” ሲሉ የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት በጋራ መግለጫ መስጠታቸው ይታውሳል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ ለሬድዮ ጣቢያው እንዳሉት ትናንት ሌሊት ስምንት ሰዓት ነፋስ መውጫ ማረሚያ ቤትና ሌሎች ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች እስረኛ ለማስፈታት ከሞከሩት ዘራፊ ታጣቂዎች መካከል አስራስድቱ ሲገደሉ ሃያ ተማርከዋል። ከመንግስት በኩል ደግሞ ሶስት የፀጥታ አካላት መቁሰላቸውን ገልጸዋል።
አቶ ጥላሁን ተደራጅተውና ታጥቀው የመጡት ዘራፊዎች ከተለያዩ አጎራባች ዞኖች የተሰባሰቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።ከማረሚያ ቤት እንዲወጡ ከተደረጉት ታራሚዎች መካከል ስልሳአምስቱ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳና በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳ በተውጣጡ ጥምር የፀጥታ አካላት ቅንጅት ባካሄዱት ኦፕሬሽን በያሉበት ተይዘው ወደማረሚያ ቤት እንዲመለሱ መደረጋቸውን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።
